ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ ሲያሳርጉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ ሲያሳርጉ  (ANSA)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጸጥታ ውስጥ ማዳመጥ መማር ይኖርብናል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ ዛሬ ሚያዝያ 14/2012 ዓ.ም ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባደረጉት ስብከት ምዕመናን ማዳመጥ መልመድ እንደ ሚኖርባቸው የገለጹ ሲሆን አሁን ዝም ባለው ዓለም ውስጥ የምንገኝ እንደ መሆኑ መጠን በአከባቢያችን ውስጥ የምናያቸውን ክፍፍሎች ማቢቂያ ያገኙ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንዲፈቅድ በዝምታ ማዳመጥ ይገባል ብለዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በእለቱ ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ የጀመሩት ዓለም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ባልተለመደ መልኩ ዝምታ ውስጥ በመግባቱ በእዚህ ወቅት በዝምታ ውስጥ ማዳመጥ እንችል ዘንድ ክህሎት እንዲሰጠን ልንጸልይ የገባል በማለት ነበር።

“በአሁኑ ወቅት ያለው የአየር ጠባይ በጣም ፀጥ ያለ ነው። ጸጥታውን ለማዳመጥ እንችላለን። እኛ ባልተለመደ እና አዲስ በሆነ መልኩ እየተለማመድነው የምንገኘው ጸጥታ የማዳመጥ ክህሎታችን ይዳብር ዘንድ ጸጋ እንዲሰጠን ልንጸልይ የገባል” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዕለቱ ያደረጉት ስብከት መሰረቱን አድርጎ የነበረው በወቅቱ ከሐዋርያት ሥራ (ሐዋ. 4 32-37) ላይ ተወስዶ በተነበበው የመጀመሪያው ምንባብ ላይ መሰረቱን ያደርገ ነበር። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የመጀመሪያዎቹ የክርስትያን ማኅበረሰብ አባላት በወቅቱ የነበረውን የአማኞች ማኅበራዊ አኗኗር የሚገልጽ ሲሆን “ያመኑትም ሁሉ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ነበር፤ ያላቸውም ሁሉ የጋራ ነበር እንጂ የራሱ የሆነውን ሀብት እንኳ እንደ ግሉ የሚቈጥር ማንም አልነበረም። ሐዋርያትም ስለ ጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ በታላቅ ኀይል መመስከራቸውን ቀጠሉ፤ በሁላቸውም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበር። ከመካከላቸውም አንድ ችግረኛ አልነበረም፤ ምክንያቱም መሬትም ሆነ ቤት የነበራቸውን ሁሉ እየሸጡ ዋጋውን አምጥተው፣ በሐዋርያት እግር ሥር በማስቀመጥ ለእያንዳንዱ በሚያስፈልገው መጠን ያካፍሉት ነበር” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ ነበር።

ዳግመኛ መወለድ

“ዳግመኛ መወለድ” (ዮሐንስ 3፡7) የሚለው አገላለጽ ከቅዱስ ወንጌል የተወሰደ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መወለድ ማለት ነው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መንፈስ ቅዱስን ለራሳችን መውሰድ አንችልም ፣ ነገር ግን ወደ ውስጣችን ገብቶ “እንዲለውጠን ፣ በውስጣችን የለውጥ ስሜት እንዲያነሳሳ፣ ዳግመኛ መወለድ እንችል ዘንድ እንዲረዳን” ወደ ውስጣችን እንዲገባ መፍቀድ ይኖርብናል ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል ይህ የመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ማህበረሰብ ያሳዩን መልካም አብነት ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉ ሲሆን ህብረተሰቡ “በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ መልካም የሆኑ ተግባራትን በሚያከናውንበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ ምን ማድረግ እንደሚችል የሚያሳይ አርአያ እና ጥሩ ምሳሌ ነው” ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጀመሪያዎቹ የክርስትያን ማሕበረሰቦች ዘንድ ስለነበረው ስምምነት ያብራሩ ሲሆን የመጀመርያዎቹ ክርስትያኖች ስምምነት የነበራቸው “የስምምነት ጌታ” በሆነው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ነው፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ስምምነት እንዲሰፍን የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው ብለዋል።

ሆኖም በክርስቲያን ማኅበረሰብ ውስጥ እንኳን ክፍተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ የገለጹት ቅዱስነታቸው ስምምነት ላይ መድረስ እንደ ሚገባ ገልጸው ሆኖም ግን ስምምነት መፍጠር ቀላል የሆነ ነገር አይደለም “አንድን ማህበረሰብ የሚከፋፈሉ ብዙ ነገሮች አሉ፣ እንደ እኔ አስተሳሰብ አንድ ማህበረሰብን የሚከፋፍሉ ሦስት ነገሮች አሉ ”ብለዋል።

ገንዘብ ይከፋፍላል

አንድን ማሕበረሰብ ከሚከፋፍሉ ነገሮች መካከል በቀዳሚነት የሚገለጸው ገንዘብ እንደ ሆነ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የገለጹ ሲሆን  ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ “በምትበሉበት ጊዜ አንዱ ሌላውን ሳይጠብቅ ምግቡን ይበላልና፤ አንዱ እየተራበ ሌላው ይሰክራል” (1ቆሮ. 11፡21) ብሎ መናገሩን በዋቢነት የገለጹ ሲሆን “የራሳችሁን ጉዳይ ራሳችሁ ፍቱ” በሚመስል መልኩ በእያሉበት ቦታ ሁነው መኖር እንዲቀጥሉ እንተዋቸዋለን ብለዋል። ብዙውን ጊዜ ገንዘብ በቤተክርስትያን ታሪክ ውስጥ በተፈጠሩ የዶግማ (የቤተክርስቲያን አስተምህሮ) ልዩነቶች ጀርባ ገንዘብ ይገኛል በማለት የገለጹት ቅዱስነታቸው ገንዘብ ህብረተሰቡን ይከፍፍላል ብለዋል። በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ ድህነት የህብረተሰቡ እናት ሆኖ የቀጠለው ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ድህነት ህብረተሰቡን የሚጠብቅ ግድግዳ ነው” ብለዋል። ገንዘብ ይከፋፍላል ፣ የገንዘብ ፍቅር ህብረተሰቡን ይከፋፍላል፣ ቤተክርስትያንን ይከፋፍላል፣ ቤተሰቦችም እንኳ ሳይቀር በገንዘብ ይከፋፍላል ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።

ኩራት ይከፋፍላል

አንድን ማህበረሰብ የሚከፋፍለው ሁለተኛው ነገር ኩራት መሆኑን የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እኛ “ከሌሎች የተሻልን ሁነን እንዲሰማን የሚያደርግ ፍላጎት” ነው ያሉ ሲሆን ኩራት ሁልጊዜም ማኅበረሰቡን የከፋፍላል ብለዋል።

ሐሜት ይከፋፍላል

ከዚያ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳሉት አንድ ማህበረሰብን የሚከፋፍል ሦስተኛው ነገር ሐሜት ነው ያሉ ሲሆን “ስለ ሌሎች የመናገር ፍላጎት ዲያቢሎስ በውስጣችን ያስቀመጠው ነገር ነው” ብለዋል ፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “መንፈስ ቅዱስ ግን ከዚህ ዓለም ገንዘብ ፣ ኩራት እና ሐሜት እኛን ለማዳን ሁል ጊዜ በኃይሉ ይመጣል” ብለዋል።

ለመንፈስ ቅዱስ መጸለይ

በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጌታ “ክርስቲያኖች በተገቢው ሁኔታ ኅብረት እንዲፈጥሩ፣ መንፈስ ቅዱስ ማኅበረሰቡን እንዲለውጥ፣ ኢየሱስ በሚፈልገው መልኩ ወደ ፊት እንጓዝ ዘንድ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ እንዲሰጠን ልንጸልይ ይገባል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው የዕለቱን ስብከት አጠናቀዋል።

22 April 2020, 17:44
ሁሉንም ያንብቡ >