ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ሐዘን ውስጥ በምንገባበት ጊዜ ሁሉ ኢየሱስ አብሮን ይጓዛል” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዛሬ ሚያዝያ 18/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ሐዘን ውስጥ ለገቡ ሰዎች የጸለዩ ሲሆን በእለቱ ባደረጉት ስብከት በሐዘን እና በእርካታ እጦት ለሚሰቃዩ ሰዎች ኢየሱስ ቅርብ ነው ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

“ብቻቸውን በመሆናቸው ወይም ደግሞ ለወደፊቱ ምን እንደ ሚከሰት ባለማወቃቸው  ምክንያት ሐዘን ውስጥ ለገቡ ሰዎች ዛሬ በእዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ እንጸልይላቸዋለን” በማለት በእለቱ ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ የጀመሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በገንዘብ እና በሥራ እጦት ምክንያት በሐዘን ውስጥ የሚገኙትን ቤተሰቦች ሁሉ በጸሎት ማስታወስ ይኖርብናል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉት ስብከት ትኩረቱን አድርጎ የነበረው በሉቃስ ወንጌል (24፡13-35) ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱ በኢየሱስ ሞት ምክንያት አዝነው ወደ ኤማሁስ እየተጓዙ በነበሩበት ወቅት ኢየሱስ አብሮዋቸው መጓዙን፣ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣ ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?” ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው፣ አብሮአቸውም በማእድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው። በዚህ ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተ፤ ዐወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። እነርሱም፣ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ። በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤ “እነርሱም ጌታ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል” ይባባሉ ነበር። ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው” በማለት በሚተርከው የዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር።

ክርስቲያኖች ኢየሱስን ተገናኝተዋል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የክርስትና እምነት መገለጫ በተመለከተ ሲገልጹ “አንድ ሰው ክርስቲያን ነው የምንልበት ምክንያት እርሱ ወይም እርሷ ኢየሱስ እንዲገናኛቸው ስለፈቀዱ ነው” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን ወደ ኤማሁስ በሚወስደው መንገድ ላይ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር እንደተገናኘ ኢየሱስ ከእኛም ጋር መገናኘት ይፈልጋል ብለዋል።

እኛ እግዚአብሔርን ተጠምተናል

እግዚአብሔርን የምንጠማበት ምክንያት አብሮን የተወለደው “የጥማት ዘር” በውስጣችን ስላለ መሆኑን በማሳረዳት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ብዙ ጊዜ በነፍሳችን ውስጥ ያለውን ጥማት እንዴት እንደ ምናረካ አናውቅም ብለዋል። የነፍሳችንን ጥማት ለማርካት በማሰብ ብዙ የተሳሳቱ መንገዶችን እንከተላለን ያሉት ቅዱስነታቸው በእውነቱ በውስጣችን ያለው ጥማት “ከእግዚአብሔር ጋር የመገናኘት” ጥማት ነው ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ተናግረዋል።

እግዚአብሔር እኛን ይጠማል

በተመሳሳይ ጊዜ ​​እግዚአብሔር እኛን ለማግኘት ይጠማል፣ ለዚህም ነው እግዚአብሔር ኢየሱስን ወደ እኛ የላከው፣ ለእኛ ቅርብ ለመሆን እና ይህንን ጥማቱን ለማርካት ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ “የግል ሁኔታችንን እጅግ በጣም ያከብራል፣ እርሱ በዝግታ ይንቀሳቀሳል፣ ዝግጁ እስክንሆን ድረስ በአክብሮት ይጠብቃል፣ ወደ ፊት ለመሄድ አይጣደፍም፣ ታጋሽ ነው” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አስረድተዋል።  ኢየሱስ ከጎናችን ሆኖ ከእኛ ጋር አብሮ በመጓዝ ድንቁርና ውስጥ እስክንገባ ድረስ እንኳን የሚያስጨንቁንን ነገሮች እንድንነግረው ይጋብዘናል ብለዋል።

እኛን በሚገባ ለመረዳት እና የእርካት እጦታችንን ተጨባጭ በሆነ መልኩ ለማርካት እና ትክክለኛውን ምላሽ ለመስጠት እኛ ስንናገር ጌታ ለመስማት ይፈልጋል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነትቸው ጌታ ፍጥነቱን አይጨምርም፣ እሱ ሁልጊዜ እኛ ካለን ፍጥነት ጋር አብሮ ይሄዳል… የመጀመሪያውን እርምጃ እንድንወስድ ይጠብቀናል ብለው ከእዚያም ትክክለኛው ጊዜ ሲደርስ  ጥያቄ ያቀርብልናል… ከዚያም እሱ ይመልሳል፣ ትክክለኛው ነጥብ እስኪ ገለጽ ድረስ ያብራራልናል ብለዋል። ከዚያም የእርካታ እጦታችን ምን ያህል ጥልቅ እንደ ሆነ ለማየት ወደ ፊት እየገሰገሰ ይሄዳል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እርካታ እጦታችን ኢየሱስን በሚገናኝበት ወቅት የፀጋ እና የህይወት ሙሉነት በዚያ ይጀምራል ብለዋል።

ኢየሱስ ምን አለ?

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንዳሉት ኢየሱስ ለእነዚያ ሁለት ደቀ መዛሙርት “ያደረገውን ነገር ለእኛም እንዲያደርግ” በወቅቱ ኢየሱስ የተናገረውን ለማወቅ ሁል ጊዜ እንደሚጓጉ የገለጹ ሲሆን “እሱም ምን አልባት በጣም ደስ የሚል የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሊሆን እንደ ሚችል” ገልጸው እርሱ ከእኛ ጋር እንደ ሆነ ባንገነዘብ እንኳን ኢየሱስ በአጠቃላይ ጉዞዋችን አብሮን ይጓዛል ብለዋል።

“በጥርጣሬያችን ጨለማ ውስጥ፣ በተለይም በኃጢአታችን የተነሳ አስከፊ ጨለማ ውስጥ ብንገባም እንኳን ኢየሱስን እናገኘዋለን” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ  በጭንቀታችን ወቅት ጌታ ሁል ጊዜ ሊረዳን ዝግጁ ነው፣ እርሱ ሁል ጊዜም ከእኛ ጋር ነው ... ጌታ እኛን ሊገናኘን ስለሚፈልግ አብሮን ይሄዳል፣ የክርስትና እምነት ዋነኛው መገለጫ ይህ ነው ብለዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ጸሎት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን ያጠቃለሉት የመደምደሚያ ጸሎት በማደረግ ሲሆን “በእያንዳንዱ ቀን ከእርሱ ጋር መገናኘት እንችል ዘንድ፣ እንድናውቀው እና ከእኛ ከእያንዳንዳችን ጋር አብሮ እንደ ሚጓዝ ለይተን እንድንረዳ፣ ረጅም በሆነው በንግደት መንገድ ላይ በምናደርገው ጉዞ አብሮን እንደ ሚጓዝ እንድንገነዘብ ኢየሱስ ጸጋውን እንዲሰጠን እንለምነው” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

26 April 2020, 14:05
ሁሉንም ያንብቡ >