ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣                ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ማስተዋልን እንዲሰጥ ጸሎት አቀረቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 20/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ለማድረግ የወጡ ደንቦችን በታማኝነት ማክበር እንዲችል የእግዚአብሔር እርዳታን ለምነዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በሰዎች ላይ የተሳሳተ ፍርድ እንዲሰጡ እና ስማቸውን እንዲያጠፉ የሚገፋፋቸውን መንፈስ በአጽኖት እንዲቃወሙት በማለት አሳስበዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ዛሬ ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ በቪዲዮ ምስል በቀጥታ በቀጥታ በተሰራቸው፣ ከብርሃነ ትንሳኤው መታሰቢያ በኋላ በዋለው ሦስተኛ ሳምንት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ሲባል ሕዝቡ በቤት እንዲቀመጥ የታዘዘበት ጊዜ መቃረቢያን በማስታወስ እንደተናገሩት፣ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በዝግ እንዲቆይ የተጠየቀበት ጊዜ ማብቂያ በመሆኑ ከዚህ በኋላም በሚኖሩን ከመንግሥት የሚሰጡ መመሪያዎችን በማክበር ወረርሽኙ ተመልሶ የሚመጣበት አጋጣሚ እንዳይመለስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ብርታትን እንለምን ብለዋል።

ከሐዋ. 7:51 እና ምዕ. 8:1 ተውስዶ በተነበበው የዕለቱ ንባብ ላይ ያስተነተኑት ቅዱስነታቸው፣ እስጢፋኖስ በሕዝቡ እና በሽማግሌዎች ፊት በድፍረት ቆሞ በእርሱ ላይ የሐሰት ምስክሮችን በማቆም ከከተማ ውጭ በመውሰድ በድንጋይ ተወግሮ እንደሚገደል መናገሩን አስታውሰዋል። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይም ተመሳሳይ ወንጀል እንደተፈጸመበት ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ ፍትህን ለማምጣት በሚል ሰበብ የሐሰተኛ ዜናን እና የሐሰት ምስክሮችን ማቅረብ ሕዝብን ወደ ጭካኔ ተግባር መምራት መሆኑን ቅድሱነታቸው አስረድተዋል። አንዳንድ ፖለቲከኞችን ከምርጫ ውድድር እንዲወጡ ማድረግ በዘመናችንም የሚታይ ተግባር መሆኑን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ በእስጢፋኖስ ላይ ሕዝብን በማነሳሳት ወይም በማሳመን ለሞት የዳረጉት መሆኑን አስታውሰዋል። የሰዎችን ስም የሚያጠፉ፣ የተሳሳተ ፍርድ እንዲሰጥባቸው እንዲሰጥባቸው የሚያደርጉ አሉ ባልታ ወሬዎች መኖራቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰው እውነት የማይሰውር ፣ ሁሌም በግልጽ የሚታይ ነው ብለዋል። ብዙን ጊዜ በዕለታዊ ኑሮአችን የሐሰት ወሬዎችን በማሰራጨት በሰዎች መካከል ሰላም እና ፍቅር እንዳይኖር እናደርጋለን ብለዋል። በመሆኑም እግዚአብሔር ይህን ከመሰለ የተሳሳተ መንገድ እንዲንመለስ በጸጋው ይርዳን በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።    

ኢየሱስን ወደ ጲላጦስ ዘንድ ባቀረቡት ጊዜ ጲላጦስም በኢየሱስ ላይ ምንም ጥፋት አለመገኘቱን ሲረዳ እጁን ታጥቦ ማሰናበቱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ዛሬ በዘመናችን በአንዳንድ አገሮች ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት ሲደረግን ወይም አንድ የፖለቲካ መሪ የምርጫ ቅስቀሳን በሚያደርግበት ጊዜ የሐሰት መልዕክቶችን በማሰራጨት ከውድድር እንዲወጣ የሚደረግ መሆኑን አስታውሰዋል። አስቀድሞ በሕዝቡ መካከል የሐሰት ወሬን በማሰራጨት ፍትሃዊ ያልሆነ ፍርድ እንዲሰጥ ማድረግ ሕዝቡን ማሳሳት ውይም ማታለያ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው በእስጢፋኖስ ላይ የተደረገ ሴራም ይህን የሚመስል መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

በሰዎች ላይ ፍትህን ማጉደል በዘመናችንም የሚፈጸም ተግባር ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በፓክስታን አገር የሐሰት ምስክር ቀርቦባት ለአሥር ዓመት ወደ ወሕኒ ቤት የተጣለች አሲያ ቢቢን አስታውሰው የተሰጣት የሐሰት ፍርድ የተፈረደባት የሐሰት ምስክር በመቅረቡ ነው ብለዋል። በሕዝቡ ዘንድ ትክክለኛ ያልሆነ መልዕክት ማሰራጨት ሕዝቡን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ መምራት በመሆኑ በኋላ ላይ ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለሱ አስቸጋሪ እንደሚሆን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

በአይሁዶች ላይ የተፈጸመውን የጭፍጨፋ ግድያን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህም የተከሰተው በሕዝቡ መካከል ጥላቻን የሚቀሰቅስ ሃሳብ እውነት አስመስሎ በማሰራጨት ሕዝብ እርስ በእርስ እንዲገዳደል ማድረግ መሆኑን አስረድተው፣ ይህ ተግባር ትክክል እንዳልሆን ብንገነዘብም አንዳንድ ጥቃቅን የሐሰት ንግግሮች፣ ስም የማጥፋት ስህተቶች እንደሚያጋጥሙ ገልጸውል። ነገር ግን እውነት እንደማይደበቅ እና እንደማይሰውር የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ በሕዝብ መካከል፣ በማኅበረሰብ መካከል እንዲሁም በክርስቲያን ማኅበረሰብ መካከል የሚመላለሱ ሐሰተኛ ንግግሮች ወይም ግምቶችን በዕለታዊ ኑሮአችን ውስጥ ተመልክተናል ብለው፣ በፍርድ አሰጣጣችን፣ በንግግራችን እና በአስተያየታችን ፍትሐዊ መሆን እንድንችል እግዚአብሔር ይርዳን ካሉ በኋላ የዕለቱን ስብከት አጠቃለዋል።

28 April 2020, 20:31
ሁሉንም ያንብቡ >