ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ወረርሽኙን በማሳበብ ሕዝብን መበዝበዝ አያስፈልግም”።

ዛሬ ቅዳሜ መጋቢት 26/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን የኑሮ ውድነት ምክንያት በማድረግ ሕዝብን በመበዝበዝ የራሳቸውን ጥቅም ለማሳደግ ምኞት ያላቸው ሰዎች እንዳሉ እና ወደ ፈተና የሚገቡባቸው ሂደቶች መኖራቸውን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው የጤና መቃወስ ምክንያት ችግር ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች እርዳታን በማቅረብ መልካም ተግባራቸውን ከሚያበረክቱ ሰዎች ጎን አሁን የምንገኝበት አስቸጋሪ ጊዜን በመጠቀም የግል ጥቅማቸውን ብቻ በማሰብ ሕዝቡን የሚበዘብዙ እና ተገቢ ያልሆኑ ሥራዎችን የሚፈጽሙ ሰዎች ሊኖሩ የሚችሉ መሆኑን ገልጸው፣ እነዚህ ሰዎች ወደ ሕሊናቸው ተመልሰው ትክክለኛውን መንገድ የሚጓዙበትን አእምሮ እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው እንለምን ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ባሳረጉት የመስውዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ ከዮሐ. 11:45-58 ተወስዶ የተነበበውን የዕለቱን የቅዱስ ወንጌል ንባብ መሠረት በማድረግ ባሰሙት ስብከት የሙሴ ሕግ መምህራን እና የካህናት አለቆችን በማስታወስ በፈተና ውስጥ መውደቅ ምን ያህል ቀላሉ እንደሆነ አስረድተዋል። 

ፈተና ዕረፍትን ያሳጣል፣

በፈተና መውደቅ ዕረፍትን በሚነሱ ትንንሽ ስሜቶች ይጀምራል ያሉት ቅዱስነታቸው የካህናት አለቆችን በማስታወስ ባሰሙት ስብከት የካህናት አለቆች ዕረፍት በማጣት እና በመረበሽ የነበሩበትን ሥፍራ ለቀው እንዲሄዱ ያደርጋቸው የአጥማቂው ዮሐንስ ትምህርት መሆኑን ገልጸው ከአጥማቂው ዮሐንስ ቀጥሎ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣቱን አስረድተዋል።     

አጥማቂው ዮሐንስ ሕዝቡን ማስተማር የጀመረው ምልክቶችን በመጥቀስ እና ተዓምራትን በማሳየት ስለሆነ ብዙ ተከታዮች ነበሩት ያሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ የፈሪሳዊያን እና የሕግ መምህራንን ሥርዓት ሳይጠብቅ ያስተምር ስለነበር ይህም የካህናት አለቆችን እረፍት በማሳጣት እጅግ የረበሻቸው መሆኑን አስረድተዋል። 

ኢየሱስ በጥበብ የሚሰጠው መልስ የካህናት አለቆችን እና የሙሴ ሕግ መምህራንን ያስገረማቸው መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው በማቴ. 22:23-34 ላይ እንደተጻፈው፣ ሰዱቃዊያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው “ሰባት ጊዜ ያገባች ሴት ሙታን በሚነሱበት ጊዜ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች”? ብለው በጠየቁት ጊዜ ኢየሱስ “እናንተ ቅዱሳት መጽሐፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል ባለ ማወቃችሁ ትሳሳታላችሁ። ምክንያቱም ሰዎች ከሞት በተነሱ ጊዜ በሰማይ እንዳሉ መላዕክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም” ማለቱን አስታውሰው፣ በዮሐ. 8:1-11 በተጻፈው ላይ የሙሴ ሕግ መምህራን ስታመነዝር የተገኘች ሴት ወደ ኢየሱስ አቅርበው “እንዲህ ዓይነቷ ሴት ተወግራ እንድትሞት ሙሴ በሕጋችን አዞናል፤ አንተስ ስለ እርሷ ምን ትላለህ”? ብለው በጠየቁት ጊዜ “ከእናንተ መካከል ኃጢአት የሌለበት በመጀመሪያ ድንጋይ ይወርውርባት ብሎ መመለሱን አስታውሰው፣ ፈሪሳዊያን እና የሙሴ ሕግ መምህራን በኢየሱስ መልስ እንደ ተማረኩ እና ከቁጣ የተነሳ ወታደሮችን የላኩበት መሆኑን፣ ከመካከላቸው አንዳንዶች በእርሱ ቢያምኑም ሌሎች ለባለስልጣናት ማመልከታቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።        

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያሳረጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመፈጸማቸው በፊት ባቀረቡት የቅዱስ ቁርባ ቡራኬ ጸሎትን፥

ኢየሱስ ሆይ! በቅዱስ ቁርባን ውስጥ በእውነት እንደምትገኝ አምናለሁ። ከሁሉም በላይ አብልጬ እወድሃለሁ፣ በነፍሴ ውስጥ እንድትገኝ እመኛለሁ። አሁን በምገኝበት ሁኔታ ቅዱስ ስጋህን እና ቅዱስ ደምህን መቀበል ባልችልም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በልቤ ውስጥ ግባ። ካንተ ጋር መሆንን እፈልጋለሁና ዘወትር ካንተ እንዳልለይ አድርገኝ፤ አሜን።      

ቅዱስነታቸው ቀጥለውም ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ባቀረቡት ጸሎታቸው፥ ‘የሰማያት ንግሥት፣ የመላዕክት እመቤት እና የምሕረት ምንጭ የሆንሽ እናታችን ሆይ ብርሃንሽ በዓለም ሁሉ ይብራ፤ ከሴቶች ሁሉ በላይ የምትወደጂ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ለምኚልን’ በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ይህን ዝግጅት በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ፣

 

 

04 April 2020, 15:51
ሁሉንም ያንብቡ >