ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በየማረሚያ ቤቱ የሚገኙ በርካታ እስረኞችን በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

ዛሬ ሰኞ መጋቢት 28/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ከቁጥር በላይ ተጨናንቀው የሚገኙ የሕግ ታራሚዎችን በጸሎታቸው አስታውሰው በመጨረሻው ቀን ፍርድን የምንቀበለው ለድሆች ባለን አመለካከት ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዛሬ የሕግ ታራሚዎችን በማስታወስ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በበርካታ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በታራሚዎች ቁጥር መጨናነቅ የተነሳ ችግሮችን እያስከተሉ መሆኑን አስታውሰዋል። በአንድ ማረሚያ ቤት ውስጥ የሕግ ታራሚዎች ቁጥር ከመጠን በላይ በሚሆንበት ጊዜ ለቫይረስ ወረርሽኝ በማጋለጥ ከፍተኛ የሕይወት መጥፋት አደጋን ሊያስከትል ይችላል ብለው፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ፍጥነት በመዛመት ላይ ባለበት ጊዜ ሃላፊነት ያለባቸው በሙሉ ሊደርስ የሚችለውን የሕይወት መጥፋት ሊያስወግዱ የሚችሉበትን ትክክለኛ መፍትሄ እንዲያገኙ በጸሎታችን እናግዛቸው ብለዋል።       

ድኾች ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፣

ዛሬ ከዮሐ.12:1-11 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአልዓዛር እና የማርታ እህት ማርያም ዋጋው እጅግ የከበረ ከንጹህ ናርዶስ በተሠራ ሽቶ የኢየሱስን እግሮች መቀባቷን አስታውሰው፣ ኢየሱስ በዚህ ጊዜ “ለምቀበርበት ቀን ያደረገችው ዝግጅት ስለሆነ ተውአት። ድኾች ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው። እኔ ግን ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር አልሆንም”

እምነተ ቢስ መሪ፣

ይሁዳ ለደሆች የተጨነቀ መስሎ መታየቱን የገለጹት ቅዱስነታቸው በእውነት ለድሆች በመጨነቅ ሳይሆን   ገንዘብ ስለፈልገ ነው ብለዋል። በማስተዳደር ሥራ እምነተ ቢስነት የዘመናችን ችግር ነው ያሉት ቅዱስነታቸው የእርዳታ ድርጅቶችን እንደ ምሳሌነት ጠቅሰው በድርጅታቸው በርካታ ሠራተኞችን ቀጥረው የሚያሠሩ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ለድሆች ማዳረስ ካለባቸው ዕርዳታ ስልሳ ከመቶ ለሠራተኛ ደመወዝ፣ የተቀረውን አርባ ከመቶ ብቻ  ለድሆች የሚያውሉ መሆኑን ገልጸው ይህም ድሆች ላይ ከሚፈጸሙ በደሎች መካከል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።    

በስውር የሚኖር ድሃ፣

ድሆች ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር መሆናቸው ግልጽ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሆኖም በየመንገድ ዳሩ የምናያቸው ድሆች ከጠቅላላው የድሃ ቁጥር ጋር ሲስተካከል እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው ብለዋል።  

በአካል ያማናያቸው እና ከእይታችን ርቀው የሚገኙ በርካታ ድሆች መኖራቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው እነዚህን ድሆች ማየት ያልቻልንበት ምክንያት የንቀት እና የማግለል ባሕል ስለምንከተል ነው ብለዋል። በመሆኑም የሚገኙበትን የድህነት ሕይወት ከልብ ሳንገነዘብ ወይም መገንዘብ ሳንፈልግ ቀርተን ቁጥራቸውን እናሳንሳለን እንጂ በምንኖርበት አካባቢም ቢሆን በርካታ ድሆች መኖራቸውን ማየት ይቻላል ብለዋል። ከመላመድ የተነሳ በከተሞች ውስጥ በየመንገድ ዳር ለምናያቸው ድሆች ወይም የጎዳና ተዳዳሪዎች ምንም ትኩረት አንሰጣቸውም ብለዋል።    

የብልሹ ኤኮኖሚ ሥርዓት ሰለባ፣

በርካታ ድሆች ያልተስተካከለ የኤኮኖም ሥርዓት ሰለባዎች ናቸው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህ ሰዎች ድህነታቸውን በይፋ መግለጽን የሚፈሩ መሆናቸውን አስረድተው ሥራ ቢኖራቸውም እንኳን እስከ ወር መጨረሻ የሚያደርሳቸው የገንዘብ አቅም የላቸውም ብለዋል።  ይህንን ሃቅ በትውልድ አገራቸው በሆነአው አርጄንቲና ዋና ከተማ ቦይንስ አይረስ በግልጽ የተመለከቱ መሆኑን ገልጸዋል። የቤት ኪራይ መክፈል ተስኗቸው በተዘጋ ፋብሪካ ውስጥ ከልጆቻቸው ጋር የሚኖሩ አስራ አምስት ቤተሰቦችን የተመለከቱት ቅዱስነታቸው እነዚህ ቤተሰቦች የአንድ አገር ብልሹ የኤኮኖሚ ሥርዓት ሰለባዎች ናቸው ብለዋል።

ኢየሱስ በድሆች መካከል ይገኛል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ያሰሙትን ስብከት ከማጠቃለላቸው በፊት፣ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ድሆችን እንዴት እንደ ተንከባከብናቸው፣ ተርበው አይተን መግበናቸው እንደሆነ፣ የታሰሩትን ጎብኝተናቸው እንደሆነ፣ የታመሙትን ጠይቀናቸው እንደሆነ፣ ረዳት የሌላቸውን ሴቶች እና አሳዳጊ የሌላቸውን ሕጻናት ረድተናቸው እንደሆነ፣ እያንዳንዳችን ከድሆች ጋር በነበረን ግንኙነት መጠን እንጠየቃለን ብለዋል። ዛሬ ድሆችን በመናቅ አልፈናቸው የሄድን ከሆነ በመጨረሻው የፍርድ ቀን እግዚአብሔርም ዘንግቶን ያልፋል ብለው ኢየሱስ “ድኾች ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው” ባለ ጊዜ እርሱ ራሱ ድሆችን በመምሰል በመካከላችን የሚገኝ መሆኑን ተናግሯል ብለው የቅዱስ ወንጌል ዋና መልዕክትም ፍርድን የምናገኘው እንደ ሥራችን መጠን ነው በማለት ስብከታቸውን አጠቃልለዋል።         

06 April 2020, 19:19
ሁሉንም ያንብቡ >