ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እምነት ለስብከተ ወንጌል ምስክርነት መሰረታዊ የሆነ ነገር ነው” አሉ!

ቅዳሜ ጠዋት ሚያዝያ 17/2012 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ የጀመሩት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰፊው እየተከሰተ እና የብዙ ሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ላይ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከእዚህ አለም በሞት የተለዩትን ሰዎች ግባተ መሬት ለሚያስፈጽሙ ሰዎች እግዚአብሔር ብርታቱን ይሰጣቸው ዘንድ ጸሎት እንዳደረጉላቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በዕለቱ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የቅዱስ ማርቆስ አመታዊ በዓል ተክብሮ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን በእለቱ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከማርቆስ ወንጌል (16፡15-20) ላይ ተወስዶ በተነበበው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እንዲህም አላቸው፤“ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። የሚያምኑትን እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ልሳንም ይናገራሉ፤ እባቦችን በእጃቸው ይይዛሉ፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡ እንኳ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውንም በሕመምተኞች ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱም ይፈወሳሉ።” ጌታ ኢየሱስ ይህን ከተናገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወጥተው፣ በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፤ ትምህርታቸውንም ተከትለው በሚፈጸሙ ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር” በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ባደረገው ስብከት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “እምነት ለስብከተ ወንጌል ምስክርነት መሰረታዊ የሆነ ነገር ነው” ብለዋል።

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እምነት ለስብከተ ወንጌል ምስክርነት መሰረታዊ የሆነ ነገር ነው” አሉ!

በእዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ቀደም ሲል እንደ ገለጽነው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የቀብር ሥነ ሥርዓት አግልግሎት ለሚሰጡ ሰዎች ሁሉ ጸሎት እንዲደረግ ያሳሰቡ ሲሆን እነሱ የሚሰሩት ሥራ በጣም የሚያሠቃይ እና የሚያሳዝን ነው፣ “በዚህ ወረርሽኝ ህመም ሥቃይ በጣም ይነካሉ” ስለእዚህ ይበረቱ ዘንድ ጸሎት ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።

በእለቱ የሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ አመታዊ በዓል እየተከበረ እንደሆነ ያስታወሱት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወቅቱ ከማርቆስ ወንጌል (16፡15-20) ላይ ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ አስተንትኖ ያደረጉ ሲሆን ኢየሱስ ወደ አብ ከመሄዱ በፊት ደቀ መዛሙርቱን “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” በማለት ለሐዋርያቱ መናገሩን አስታውሰዋል።

ከራስ መውጣት

የእምነት ተልዕኮአዊ ባሕሪይን በመግለጽ “እምነት ተልዕኮ ነው፣ ተልዕኮ የሌለው እመነት በጭራሽ እምነት ሊባል አይችልም” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እምነት እንደ አንድ የመታወቂያ ካርድ ለእኛ ብቻ አገልግሎት እና እድገት ይውል ዘንድ የተሰጠን ነገር አይደለም በማለት ጨምረው ገልጸዋል። አንድ ሰው በእመንቱ ማደግ የሚችለው እመንቱን ከሌሎች ጋር ሲጋራ ብቻ እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህም ማለት “ተልዕኮ” ማለት እንደ ሆነ ገልጸው  እምነት ከሁሉም በላይ ለሌሎች መተላለፍ አለበት፣ ከሁሉም በላይ በምሥክርነት መሰጠት አለበት ”ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል ፡፡

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት በአንድ የአውሮፓ ከተማ ውስጥ የሚሠራ አንድ ካህን በክርስቲያኖች መካከል አምነትን ግላዊ በሆነ መልኩ ብቻ መጠቀም እና መለማመድ፣ እንዲሁም እምነት ማጣት እየተንሰራፋ በመምጣቱ ቅሬታ እደተሰማው ሲናገር አስታውሳለሁ ያሉ ሲሆን የእዚህ ዓይነት ስሜት ሊከሰት የቻለው ደግሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደ ተናገሩት በሚስዮናዊነት መንፈስ እጥረት ምክንያት ነው፣ እምነት ከሁሉም በላይ በምስክርነት የምናቀርበው ነገር ነው ብለዋል።

እምነት መተላለፍ አለበት

በመታወቂያ ካርድ ላይ ክርስቲያን ወይም የካቶሊክ እምነት ተከታይ መሆናችንን የሚገልጽ ጹሁፍ ማስፈር በራሱ የተለመደ የመረጃ አያያዝ ዘዴ እንደ ሆነ የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ይህ በራሱ እምነት አይደለም” ብለዋል። እምነት የግድ ከራስህ ውስጥ እንድትወጣ ያደርግኃል፣ እመነት ለሌሎች እንድትሰጥ ይመራሃል ፣ ምክንያቱም እምነት በመሠረቱ መተላለፍ አለበት እንጂ እንዲያው ለራሳችን መንፈሳዊ እድገት ብቻ የምንጠቀመው ነገር አይደለም ብለዋል።

ሚስዮናዊ መሆን ማለት ወደ ሩቅ ስፍራዎች በመሄድ ቅዱስ ወንጌልን ማብሰር ማለት አይደለም፣ ነገር ግን እምነት ካለህ የግድ ከራስህ ተለይተህ ውጥተህ እምነትህን በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ማሳየት አለብህ ማለት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ ማለት ሰዎች የነበራቸውን እምነት እንዲለውጡ ማደረግ ወይም ደግሞ ሰዎችን ለበጎ አድራጎት ተግባር መመልመል ማለት አይደለም ብለዋል።

ስለ ምስክርነት

የእምነት ሽግግር መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ውስጥ እንዲሠራ እግዚአብሔርን በምስክርነት እና በአገልግሎት መግለጥ ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው አገልግሎት  የሕይወት መንገድ ነው ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተናግረዋል። “እኔ ክርስቲያን ነኝ” ብየ እየተናገርኩኝ ነገር ግን የምኖረው እንደ አረማዊ ሰው ከሆነ ማንንም ማሳመን አልችልም፣ ይልቁንም እኔ ክርስቲያን ከሆንኩ እና እንደ ክርስቲያን የምኖር ከሆነ ሰዎች ይማርካሉ ይህ ምስክር ነው ብለዋል።

በፖላንድ የሚኖር አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ “በእግዚአብሔር የማያምኑ ብዙ ጓደኞቹን ለማሳመን ምን ማድረግ እንደሚችል” ጠይቆኝ ነበር በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ማድረግ የሚገባህ አንድ ነገር ቢኖር ከመናገርህ በፊት እምነትህን ኑር፣ እናም በእምነትህ የምታሳየውን ምስክርነት ሲያዩ  ‘እንዲህ ዓይነት ሕይወት እንዴት ትኖራለህ ‘ ብለው ይጠይቁኃል” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን  ”እምነት ሰዎችን ማሳመን ማለት ሳይሆን ለሰዎች የምናስተላልፈው ቅርስ ነው” ብለዋል።

ትህትና

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ ቅዱስ ጴጥሮስ በመጀመሪያው ንባብ ላይ እንደተናገረው “ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ” (1 ጴጥሮስ 5፡ 5) በማለት በአጽኖት እንደ ተናገረ ገልጸዋል። በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በእንቅስቃሴዎች እና በቡድኖች ውስጥ ሰዎች የነበራቸውን እምነት እንዲቀይሩ የሚያደርጉ ስብከቶች በከፍተኛ ደረጃ መደረጋቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው በእዚህ መልኩ የተከናወኑት የስብከተ ወንጌል አገልግሎቶች ብዙም ስኬታማ አልነበሩም ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሲደመድሙ ስለጌታ ስለእርሱ ለመመስከር የምንሄድ ከሆነ ፍሬያማ አንደምንሆን እና ድንቅ ስራዎችን የምንሠራ መሆናችንን ጌታ ያረጋግጥልናል ያሉ ሲሆን ርዕዮተ ዓለም በሚሸጋገርበት ወቅት አስተማሪዎች ያስፈልጋሉ፣ እመንት በሚሸጋገርበት ወቅት ግን ጌታ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእኛ ጋር እንደሚሆን ተናግሯል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለዕለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

25 April 2020, 11:52
ሁሉንም ያንብቡ >