ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣                ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “እግዚአብሔር ዓለም እንዲድን እንጂ እንዲጠፋ አይፈቅድም”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 14/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስውዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ለመቋቋም መላው አውሮፓ መተባበር እንደሚያስፈልግ ገልጸው በዕለቱ በተነበቡት ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ በማስተንተን እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ጥልቅ መሆኑንም አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመጀመሪያ በፊት ባቀረቡት ሃሳብ የኮሮና ቫይረስ ወረርኝ በማስከተል ላይ ያለውን ቀውስ ለመቋቋም መንግሥታት መተባበር እንዳለባቸው ጠይቀው አውሮፓን በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም እርስ በርሳችን እና በአገራት መካከል ሕብረት መኖር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ የአውሮፓ አገሮችም በመካከላቸው ወንድማማችነትን በማሳደግ፣ የቀድሞ አባቶች የአንድነት ፈለግ እንዲከተሉ በጸሎት መርዳት እንዳለብን አደራ ብለዋል።

እግዚአብሔር እጅግ አድርጎ ይወደናል፣

ከዮሐ. 3:16-21 ተውስዶ በተነበበው የዕለቱ ንባብ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ የተናገራቸውን አስታውሰው፣ በዚህ የወንጌል ክፍል “እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለ ወደደ አንድ ልጁን ሰጠ፤ ስለዚህ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት ይኖረዋል እንጂ አይጠፋም” የሚለው ጥቅሰው፣ ይህም ድነት ያለበት ጥልቅ ሥነ መለኮታዊ ሃብት የያዘ መሆኑን አስረድተዋል። ዛሬ ባቀረቡት ስብከት በሁለት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የመጀመሪያው በእግዚአብሔር ፍቅር መገለጥ ሲሆን ሁለተኛው በብርሃን እና በጨለማ መካከል ሊኖር የሚችል ምርጫ መሆኑ ታውቋል። “እግዚአብሔር ይወደናል” ፣ “እጅግ አድርጎ ይወደናል” በማለት አንድ ቅዱስ የተናገረውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

በመስቀሉ ላይ ክርስቲያናዊ ጥበብ በሙላት ይገኛል፣

ቅዱስ መስቀል ከፍተኛ የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጸበት መሆኑን ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅዱስ መስቀል ላይ ለሚያስተነትኑት በሙሉ ክርስቲያናዊ ጥበብ ይገለጥላቸዋል ብለዋል። በርካታ ክርስቲያኖች ለረጅም ጊዜ ቅዱስ መስቀልን በመመልከት ከሁሉ የሚበልጥ ጥበብ በእርሱ ላይ የሚገኝ መሆኑን ይገነዝወባሉ ብለዋል። ሳይንሳዊ ጥበባት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እና ክርስቲያናዊ ጥበባት በቅዱስ መስቀል ላይ የሚገኝ መሆኑን መንፈስ ቅዱስ ያስተምራቸዋል ብለዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ ሲናገር፣ የሰው ልጅ ጥበብ አስፈላጊነቱ እስከ ተወሰነ ደረጃ ድረስ መሆኑን ተናግሮ፣ እውነተኛ እና ሁሉን ነገር በትክክል ሊገልጽ የሚችል ጥበብ የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ እና እርሱ በተሰቀለበት መስቀል ላይ መሆኑን አስረድቷል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበት መንገድ መሆኑን ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ አድርጎ የወደደው በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው ነው ብለው፣ በዚህ አባታዊ ፍቅሩ እኛ ልጆቹ ከእርሱ ጋር እንድንሆን የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል።    

ብርሃን ጨለማን ያሸንፋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ባቀረቡት በሁለተኛ የስብከታቸው ክፍል፣ በብርሃን እና በጨለማ መካከል ሊደረግ የሚችለውን ምርጫ በተመለከተ ሲገልጹ፣ በብርሃን መመላለስ የማንችልበት ዋናው ምክንያት ጨለማን ስለ ተለማመድን ነው ብለዋል። ብዙ ሰዎች እንደ ሌሊት ወፍ በጨለማ ውስጥ መንቀሳቀስ ይቻላቸዋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እኛ ሁላችን በኃጢአት ውስጥ በምንገኝበት ጊዜ ከብርሃን ይልቅ በጨለማ ውስጥ መኖር ይቀለናል ብለዋል። ብርሃን ፊታችን ጋርዶን ማየት የማንፈልገውን ነገር እንድናይ ያደርገናል ብለዋል።

ሙስና ዓይነ ስውር ያደርገናል፣

በኃጢአት ውስጥ ስንገኝ ብርሃን የሚገልጣቸውን ነገሮች መመልከት ይከብዳል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የነፍሳችን ዓይን ብርሃን ማየት ካቃተው ሁሉ የከፋ ይሆናል ብለዋል። ሰብዓዊ ክፋቶችም ይህን ያስተምሩናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በመጥፎ ተግባር ላይ የተሰማሩት በሙሉ ብርሃንን አያቁትም፣ ለይተው ማወቅም አይችሉም ብለዋል።

ከብርሃን ወይስ ከጨለማ ወገን ነን?

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን ስብከት ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት “ከብርሃን ወይስ ከጨለማ ወገን ነን?” ብለን ራሳችንን እንጠይቅ ብለው፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሔር ብርሃን በእኛ ላይ እንዲያርፍ እናድርግ ብለዋል።  

22 April 2020, 19:26
ሁሉንም ያንብቡ >