ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የማኅበራዊ መገናኛ ባለ ሞያዎች ከሕዝቡ የብቸኝነት ስሜት እንዲያስወግዱ ጠየቁ።

ቅዱስነታቸው ዛሬ መጋቢት 23/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የማኅበራዊ መገናኛ ባለሞያዎች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በለይቶ ማቆያ እና በቤታቸው ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ብቸኝነት እንዳይሰማቸው በማጽናናት፣ በመምከር እና በማስተማር የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያበረክቱ አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነጻ፣ ባሕሉን የሚያውቅ፣ ለዓለማዊ አስተሳሰብ የማይገዛ፣ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ አዳዲስ ክስተቶችን የሚገነዘብ ነው ብለዋል።     

“ከሚያስጨንቁኝ ከክፉዎች፣ ከሚከብቡኝ አደገኛ ባላንጣዎቼ ጋርደኝ” (መዝ. 17:9)

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዛሬውን መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመጀመራቸው በፊት ለብዙሃን መገናኛዎች እና ማኅበራዊ ሚዲያ ባለሞያዎች ባቀረቡት መልዕክት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በለይቶ ማቆያዎች እና በቤታቸው እንዲቆዩ የተደረጉ ሰዎች ብቸኝነት እንዳይሰማቸው በማድረግ የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍ ተሰማርተው ለሚገኙ የማኅበራዊ መገናኛ ባለሞያዎች እንጸልይ ያሉት ቅዱስነታቸው ባሁኑ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በሚል ዓላማ በቤታቸው ተዘግተው እንዲቀመጡ የታዘዙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰው፣ በብቸኝነት ስሜት እንዳይጎዱ ብዙሃን መገናኛዎች በማዝናናት፣ በመምከር እና በማስተማር የበኩላቸውን እገዛ እንዲያበረክቱ አደራ ብለዋል።

ከዮሐ. 8፡31-42 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ጥቅስ ላይ በማተነተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ያመኑ አይሁዳዊያንን “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል።” (ዮሐ. 8፡31-32) ያለውን በመጥቀስ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ነጻ፣ ባሕሉን ጠንቅቆ በማወቅ ፣ በርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ አዳዲስ ክስተቶችን የሚገነዘብ ነው ብለዋል።     

በእነዚህ ቀናት ውስጥ በዮሐ. ወንጌል በምዕ. 8 ላይ የተጠቀሰውን እንድናነብ ቤተክርስቲያን አዛናለች ያሉት ቅዱስነታቸው በዚህ የወንጌል ክፍል በኢየሱስ እና በሙሴ ሕግ መምህራን መካከል ጠንከር ያለ ውይይት መደረጉን አስታውሰዋል። በዚህ የወንጌል ክፍል ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ የሕግ መምህራን የግል ማንነታቸውን ለይተው እንዳወቁ እኛም የኢየሱስ ክርስቶስ መሆናችንን የሚገልጽ ክርስቲያናዊ ማንነትን ለይተን ለማወቅ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያሳስበናል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የሕግ መምህራንን ለይቶ በማስቀመጥ የነበረባቸውን ቅራኔ እንዲገነዘቡ አድርጎአቸዋል ያሉት ቅዱስነታቸው የሕግ መምህራኑም ምንም አማራጭ ባለማግኘታቸው በቁጣ ተነሳስተው ቅድስት ድንግል ማርያምን እስከ መንቀፍ መድረሳቸውን አስረድተዋል።  

ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ይከተሉ ለነበሩ አይሁዳዊያን “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ” በማለት ደጋግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ እራት ሊበሉ በቀረቡ ጊዜም “በእኔ ኑሩ፣ በአባቴም ኑሩ” ብሎ መናገሩን አስታውሰዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ፣ በእርሱ መኖር፣ ለቃሉ ታማኝ ሆኖ መገኘት ከጥበብ ሁሉ በላይ እንደሆነ መናገሩን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ጸንተው የቆሙት ክርስቲያናዊ ማንነት አላቸው ብለዋል። ክርስቲያናዊ ማንነት ሌላ ሳይሆን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ነው ያሉት ቅዱስነታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ መኖር፣ በቃሉ እና ሕይወቱ መኖር ማለት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ማለት ነው ብለው ይህ ካልሆነ ግን የቤተክርስቲያን አስተምህሮን ማወቅ፣ ለጋስ መሆን እና ባሕልን ማወቅ ደቀ መዝሙር የሚያሰኝ ክርስቲያናዊ ማንነትን ሊያሰጥ አይችልም ብለዋል።             

የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ነጻነትን ያስገኛል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምክንያቱም ደቀ መዝሙር በኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚኖር እና በእርሱ ስለሚታመን ነው ብለዋል። በኢየሱስ መኖር ማለት ምን ማለት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ መኖር ማለት በመንፈስ ቅዱስ መመራት ማለት ነው ብለው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር በዓለማዊ አስተሳስብ አይገዛም ካሉ በኋላ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ በነጻነት የሚጓዝ፣ ባሕሉን የሚያውቅ እና አዳዲስ ክስተቶችን የሚገነዘብ ነው ብለዋል። መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ይኖራል ብለን መዘመር የምንችለው በኢየሱስ ክርስቶስ የምንኖር ከሆነ ብቻ ነው ብለዋል።    

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያሳረጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመፈጸማቸው በፊት የሚከተለውን የቅዱስ ቁርባ ቡራኬ ጸሎትን አሳርገዋል፥

“ኢየሱስ ሆይ! ራሴን ዞር ብዬ በመመልከት የተሰበረውን ልቤን ይዤ ለንስሐ ወደ እግሮችህ አጠገብ ቀርቤአለሁ። በፍቅር በገለጥካቸው ቅዱሳት ምስጢራት በኩል አክብርሃለሁ፤ በደሳሳ ቤቴ፣ አንተን በልቤ ውስጥ ልቀበልህ እመኛለሁ፤ ከቅዱሳት ምስጢራት ኅብረት የሚገኘውን ደስታ በመጠባበቅ ፣ መንፈስ ቅዱስን መቀበል እፈልጋለሁ፤ ኢየሱስ ሆይ ፣ ወደ እኔ ና! በሕይወቴ ዘመን እንዲሁም በሞቴ ሁሉ ፍቅርህ ይብዛልኝ፤ እምነቴ እና ተስፋዬ አንተው ነህና እወድሃለሁ፤ አሁንም፣ ዘወትርም ይሁን”።

ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ባቀረቡት ጸሎት ‘የሰማያት እና የመላዕክት ንግሥት፣ የምሕረት ምንጭ የሆንሽ እናታችን ሆይ ለዓለም በሙሉ ብርሃንሽ ይብራ፤ ከሴቶች ሁሉ በላይ የምትወደጂ ቅድስት ድንግል ማርያም ለምኚልን’ በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

01 April 2020, 17:14
ሁሉንም ያንብቡ >