ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ፣                ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ፣   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የምንገኝበት የጸጥታ ጊዜ ማድመጥን ያስተምረናል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማክሰኞ ሚያዝያ 13/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያመጣውን የጸጥታ ጊዜ በመጠቀብ እርስ በእርስ የመደማመጥ አቅማችንን ልናሳድግ ይገባል ብለው፣ በቀድሞ ክርስቲያኖች መካከል የነገሠውን የጸጥታ ጊዜን በማስታውስ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ዕድል ከሰጠነው ድንቅ ነገሮችን ማድረግ ይችላል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም መንፈስ ቅዱስ ለክርስቲያኖች አንድት እንቅፋት የሆኑ ሦስት ነገሮችን፣ እነርሱም የገንዘብ ፈተናን፣ ኩራትን እና አሉባልታ ወሬን ማሸነፍ ይቻላል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በቪዲዮ በተሰራቸው የቅዳሴ ጸሎት ሥነ ስርዓት መጀመሪያ ላይ እንደገለጹት ባሁኑ ወቅት በዓለማችን ጸጥታ መንገሡ ይስተዋላል ብለው፣ ይህ ጸጥታ የእርስ በእርስ የመደማመጥ ችሎታችንን ለማዳበር ጥሩ ዕድል ፈጥሮልናል ብለው ለዚህም በርትተን መጸለይ ይገባል ብለዋል። 

ከሐዋ. ሥራ 4:32-37 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ሁለተኛ ንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ የመጀመሪዎቹ ክርስቲያን ማኅበረሰብ በመካከላቸው ልዩነት ሳይኖርባቸው በአንድ ልብ እና በአንድ መንፈስ ተባበረው የኖሩ፣ የእኔ ነው የሚሉት ነገር እንዳልነበራቸው፣ ሁሉንም በጋራ ይጠቀሙ እንደነበር በዚህም የሚጎድላቸው ነገር ምንም እንዳልነበራቸው ቅዱስነታቸው አስረድተው መንፈስ ቅዱስ ይህን የመሰለ ድንቅ ነገር ለማድረግ ችሎታ ያለው መሆኑን ተነግረዋል። የመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ማኅበረሰብ መንፈስ ቅዱስ ሥራውን እንዲያከናውን ዕድል የሰጡ እና የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ጎልቶ እንዲታይ በማድረግ መልካም ምሳሌ የሆኑ ናቸው ብለው እኛም በመካከላችን ሰላምን እና መግባባትን ለሚያመጣ መንፈስ ቅዱስ ዕድል ልንሰጥ ያስፈልጋል ብለዋል። በክርስቲያኖች ውስጥ የተለያዩ ችግሮች መፈጠራቸው አልቀረም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመጀመሪያው ችግር ገንዘብ ነው ብለው ድሆችን መናቅ እና ከማኅበረሰቡ ማግለል ገንዘብ ከሚያስከትላችው ስችግሮች መካከል አንዱ እንደሆነ አስረድተው ገንዘብ በማኅበረሰብ እና በቤተክርስቲያን ውስጥ እንቅፋቶችን ሊያስከትል ይችላል ብለዋል። ከቤተክርስቲያን ሕጎችን እና አስተምህሮች በስተጀርባም ቢሆን ገንዘብ አለ ያሉት ቅዱስነታቸው ድህነት በሰዎች መካከል መከፋፈልን አይፈጥርም ብለዋል። በሃብት ውርስ ምክንያት በርካታ ቤተሰቦች ሊለያዩ መብቃታቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ሁለተኛው የክርስቲያኖች አንድነት እንቅፋት ኩራት ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ራስን ከሌላው የተሻለ አድርጎ መቁጠር በሰዎች መካከል መከፋፈልን ሊፈጥር እንደሚችል ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የክርስቲያን ማኅበረሰብን ሊለያይ ይሚችል ሦስተኛው እንቅፋት አሉባልታ ወሬ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ይህም አንዱ ሌላውን እንዲገድል ሰይጣን የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው ብለው መንፈስ ቅዱስ ከዚህ ሁሉ ፈተና ጠብቆን ክርስቲያናው ማኅበራችንን ወደ አንድነት፣ ወደ ሰላም እና ወደ ጋራ ፍቅር ይመልሰን በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት ስብከታቸው በመንፈስ ቅዱስ መወለድ እንደሚያስፈልግ አስረድተው፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚላክልንን መንፈስ ቅዱስ ተቀብለን፣ ሁሉን ነገር እርሱ እንዲያከናውን ዕድል መስጠት ይኖርብናል ብለዋል። መንፈስ ቅዱስን ለመላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል የገባልን መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። የመንፈስ ቅዱስን ድንቅ ሥራን በተግባር መመስከር የቻለው የመጀመሪያው የክርስቲያን ማኅበረሰብ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ለመልካም ምሳሌነት የበቁት ለመንፈስ ቅዱስ ዕድል ስለሰጡ ነው ብለዋል። እኛም እንደ እነርሱ ለመንፈስ ቅዱስ ዕድል የምንሰጥ ከሆነ ብዙ ድንቅ ነገሮችን መመልከት እንችላለን ብለዋል። ያም ሆኖ የተለያዩ ችግሮች መከሰታቸው አይቀርም አይቀርም ያሉት ቅዱስነታቸው ቢሆንም እግዚአብሔር እነዚህ ችግሮች ተመልክተን በመንፈስ ቅዱስ በመታገዝ መፍትሄን ለማግኘት ያግዘናል ብለዋል። በመንፈስ ቅዱስ በሚተማመን የክርስቲያን ማሕበረሰብ መካከል ሁል ጊዜ ሕብረት እና ፍቅር አለ ያሉት ቅዱስነታቸው መንፈስ ቅዱስ ብዙ ነገሮችን መለወጥ እንደሚችል፣ እርሱ ራሱ ፍቅር መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

መንፈስ ቅዱስ ከመከፋፈል፣ ከልዩነት እና ከማንኛውም ዓለማዊ እንቅፋቶች፣ ከገንዘብ ፍቅር፣ ከኩራት እና ከአሉባልታ ወሬ ወይም የሰው ስምን ከማጥፋት ኃጢአት በኃይል ሊያወጣን ይመጣል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መንፈስ ቅዱስ የዓለምን ክፋት በሙሉ የሚቃወም፣ ተዓምራትን ለማከናወን የሚችል የእግዚአብሔር ኃይል ነው ብለዋል። ክርስቲያናዊ ማኅበራችን፣ የቁምስና ምዕመናን፣ ሀገረ ስብከታችን እና ቤተክህነት በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ ለውጥን እበማምጣት በሕብረት እና በፍቅር ወደ ፊት መጓዝ እንዲቻል የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ በጸሎት ጠይቀው ኢየሱስ ክርስቶስም በክርስቲያን መኅበረሰብ መካከል እንዲታይ የሚፈልገው ይህ ነው በማለት ለዕለቱ ያቀረቡትን ስብከት አጠቃልለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያሳረጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመፈጸማቸው በፊት ባቀረቡት የቅዱስ ቁርባ ቡራኬ ጸሎትን፥ ኢየሱስ ሆይ! በቅዱስ ቁርባን ውስጥ በእውነት እንደምትገኝ አምናለሁ። ከሁሉም በላይ አብልጬ እወድሃለሁ፣ በነፍሴ ውስጥ እንድትገኝ እመኛለሁ። አሁን በምገኝበት ሁኔታ ቅዱስ ስጋህን እና ቅዱስ ደምህን መቀበል ባልችልም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በልቤ ውስጥ ግባ። ካንተ ጋር መሆንን እፈልጋለሁና ዘወትር ካንተ እንዳልለይ አድርገኝ፤ አሜን።   

ከፋሲካ በዓል አንስቶ እስከ ጴራቅሊጦስ በዓል ድረስ የሚደገመውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ" የተሰኘ ጸሎት እንደሚከተለው ቀርቧል፥

የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ – ሃሌ ሉያ

እሱን ለመሸከም በቅተሻልና – ሃሌ ሉያ –

እንደተናገረው ከሙታን ተለይቶ ተነሣ – ሃሌ ሉያ

እግዚአብሔርን ለምኝልን – ሃሌ ሉያ

ድንግል ማርያም ሆይ በጣም ደስ ይበልሽ – ሃሌ ሉያ –

ጌታ በእውነት ስለተነሣ – ሃሌ ሉያ፡፡

21 April 2020, 18:09
ሁሉንም ያንብቡ >