ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “በዚህ ከባድ ወቅት በቤተሰብ ውስጥ ሰላም እንዲነግሥ እንጸልይ”!

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዛሬ መጋቢት 5/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ በኮሮና ቫይረስ መዛመት ምክንያት የዓለማችን ሕዝብ በጭንቀት ውስጥ ባለበት ባሁኑ ወቅት በቤተሰብ ዘንድ ሰላም፣ ደስታ እና የመንፈስ ጥንካሬ ይሰፍን ዘንድ እንጸልይ ብለው በተለይም የአካል ጉዳተኞችን በጸሎታችን ማስታወስ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በዘላቂነት በሚተላለፍ የቪዲዮ ምስል ሲሰራጭ መቆየቱ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በተላላፊው የኮሮርና ቫይረስ ተይዘው የሚገኙትን በሙሉ በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑ ታውቋል። ዛሬ መጋቢት 5/2012 ዓ. ም. ባቀረቡት ጸሎታቸውም በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ያሉባቸው ቤተሰቦችን አስታውሰው፣ በእነዚህ ቤተሰቦች መካከል ሰላም፣ መረጋጋት እና የመንፈስ ጥንካሬ እንዲኖር በጸሎታችን እናስታውስ ብለዋል።      

“በተላላፊው የኮሮርና ቫይረስ ለተጠቁት ሰዎች የምናቀርበውን ጸሎት ሳናቋርጥ መቀጠል ይኖርብናል።  ከበሽታው ራስን ለመከላከል እቤት ውስጥ ለሚገኙት ቤተሰቦች እንጸልይ። የቤተሰብ አባላትን በተለይም ልጆችን ሕጻናትን በመንከባከብ ላይ የሚገኙ ቤተሰቦች የዕለት ሥራዎቻቸውን በትዕግስት፣ በሰላም እና በደስታ ማከናወን እንዲችሉ፣ በጸሎታችን አማካይነት ብርታትን እንለምን። የአካል ጉዳተኛ ያለበትን ቤተሰብ በጸሎታችን እናስታውስ። ለአካል ጉዳተኞች እንክብካቤን የሚሰጡ ማዕከላት በሙሉ ተዘግተዋል። በመሆኑም የአካል ጉዳተኞቹ ወደየ ወላጆቻቸው ቤት እንዲመለሱ ተደርገዋል። እነዚህ ወላጆች በትዕግስት እና በሰላም እንዲሞሉ፣ እንክብካቤአቸውንም በልበ ሙሉነት፣ በመንፈስ ጽናት እና በደስታ ማከናወን የሚችሉበትን ጸጋ በጸሎት እንለምን”። 

ከሉቃ. 15: 1-3- እና 11-32 ተወስዶ በተነበበው እና ጠፍቶ የተገኘውን ወይም አባካኙን ልጅ ታሪክ በሚናገረው በዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።

“በሉቃ. ምዕ. 15 ላይ የተገለጸውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል ብዙ ጊዜ ሰምተነዋል። ይህን ታሪክ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ ምሳሌ ያቀርበዋል። ፈሪሳዊያን፣ ጸሐፍት እና ኃጢአተኞች የኢየሱስን ትምህርት ለመስማት ወደ እርሱ መጥተው ነበር። “ይህ ሰው ኃጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር ይበላል” እያሉ በኢየሱስ ላይ ማጉረምረም ጀመሩ። ኢየሱስም በምሳሌ ሊነግራቸው ጀመረ። በሥፍራው የነበሩ ጢአተኞች ኢየሱስን ለማዳመጥ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ቀስ እያሉ ወደ እርሱ መቅረብ ጀመሩ። ቅዱስ ወንጌል እንደሚነገረን ፈሪሳዊያን እና የሕግ መምህራን ግን የኢየሱስን ስልጣን በመቃወም በእርሱ ላይ ማጉረምረም ጀመሩ። “ይህ ሰው ከኃጢአተኞች ጋር ይቀበላል” በማለት ከሰሱት። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ግን መዳንን ይፈልግ እና ይመኝ ነበር። የዕውቀት ማነስ ቢታይበትም አምላክ የሚሆነን ፣ መሪ የሚሆነን እንፈልጋለን ይሉ ነበር። በኢየሱስ ላይ የመሪነት፣ የአባትነት ስልጣን እንዳለ ይመለከቱ ነበር። በሕይወታቸው ውስጥ ድጋፍን እና እርዳታን ይፈልጉ ነበር። ሌሎች ፈሪሳዊያን እና ቀራጮች ግን ራሳቸውን አዋቂ በማድረግ፣ “ሕግ ምን እንደሚል እያንዳንዱን በሚገባ እናውቃለን፣ ከፍተኛ የትምህርት ማስረጃም አለን፣ የዶክተርነት ማዕረግ አለን” በማለት ይመኩ ነበር። ሌሎችን ግን ኃጢአተኞች ናቸው በማለት ይንቋቸው ነበር። ነገር ግን ቅዱስ ወንጌል ጠፍቶ ስለተገኘው ልጅ ታሪክ ሲናገር፥ ይህ ልጅ ወደ አባቱ ቀርቦ “አባባ! ከሃብትህ ከፍለህ ድርሻዬን አሁኑን ስጠኝ” አለው። አባትዬውም ምንም ሳይናገር የተጠየቀውን አደረገለት፤

አንድ አባት ስቃይን በዝምታ ማሳለፍ ምን እንደሆነ ያውቃል፣ ወደ ፊት የሚመጣ ጊዜን ይመለከታል። ክፉ የመከራ ጊዜን በትዕግስት ያሳልፋል። አንዳንድ ጊዜ የአባት ተግባር የሞኝ ተግባር ይመስል ይሆናል። ሁለተኛው ልጅም ወደ አባቱ ቀርቦ መሳሳቱን እና ትክክል አለመሆኑን ይነግረዋል። ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን? የቀደመው ልጁ ዓለምን ሁሉ ለራሱ ሊያደርግ ፈለገ፤ ነጻነትን የተነፈገ መሰለው፤ ስለዚህ ከመኖሪያው ወጥቶ መጥፋት ፈለገ። አባቱንም “ከሃብትህ ከፍለህ ድርሻዬን አሁኑን ስጠኝ” ብሎ ለመጠየቅ ድፍረትን እና ኃይልን አገኘ። አባቱ በልጁ መሄድ ቢያዝንም እጅግ ራራለት፣ ፍቅሩንም ገለጠለት። ከጊዜ በኋላ “ተነስቼ ወደ አባቴ ልሂድ” ባለ ጊዜ፣ አባቱ ከሩቅ ሆኖ ልጁ የሚመጣበት ጊዜ የጠባበቅ ነበር። በመተመለሰ ጊዜም በደስታ ተቀበለው።

ታላቅ ወንድሙ እጅግ መቆጣቱን ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል። ንቀት እንደተሰማው ይገልጻል። ብዙን ጊዜ እንቆጣለን፣ የንቀት መግለጫ ብቸኛ መንገድ ቁጣ ነው። ቅዱስ ወንጌል የሚናገረን እና ከታሪኩም የምንረዳው ይህን ነው። ችግሩ የሚጀምረው የቱጋ ነው ብለን ብንጠይቅ ከታላቅ ልጁ ነው። እርሱ ከአባቱ ጋር የመሆን ትርጉም ወይም ጥቅም አልተገነዘበም። እቤት ውስጥ ማከናወን ያለበትን ሥራ ሲያከናውን፣ ግዴታውንም ሲፈጽም ቆይቷል። ነገር ግን ከአባቱ ጋር የነበረውን ፍቅር አላወቀም። በዚህም የተነሳ ተቆጥቶ ወደ ቤት መግባት አልፈለገም። ፈሪሳዊያን እና የሕግ አዋቂዎችም እንደዚሁ ናቸው። ታላቅ ልጁም እንዲህ አለ፥ ነገር ግን ይህ ልጅህ ንብረትህን ከጋለሞቶች ጋር አውድሞ ሲመጣ፣ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት።’ “አባቱም እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፤ አንተ ሁል ጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” አለው። ታላቅ ልጁ ይህን አላወቀም ነበር። የሚኖርበት ቤት የእንግዳ መረፊያ ይመስለው ነበር። በቁጥር በርካታ ሰዎች ቤተክርስቲያንን እንደ ግል ቤት የሚቆጥሩ አሉ።

አባት አባካኝ እና ኃጢአተኛ ልጁ ወደ ቤቱ ተመልሶ በመጣ ጊዜ በዓል አዘጋጅቶ በደስታ ተቀበለው። የእግዚአብሔርን አባትነት ማወቅ ለተሳናቸው፣ ልባቸው ለደንደነባቸው ለእነዚያ ፈሪሳዊያን እና ቀራጮች ኢየሱስ ያቀረበው ምሳሌ ሊገባቸው ይገባ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበው ምሳሌ፣ እርሱን ለሚቃወሙት የሰጠው መልስ ብዙ ነገር ያስተምረናል። ዛሬም ቢሆን ብዙ ሰዎች የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ይቃወማሉ፣ ድሆችን ለመደገፍ፣ ትሑታንን ለማገልገል፣ በሥራ የሚደክሙትን ለማገዝ፣ እኛንም ጭምር ለማገልገል የሚመጡትን ሰዎች የሚቃወሙ ብዙ ሰዎች አሉ። የችግሩ መነሻ ከወዴት እንደሆነ የምናውቅበትን ጸጋ  እግዚአብሔር ይስጠን። ችግሩ በእርሱ ቤት ውስጥ በሕብረት እየኖርን ነገር ግን በመካከላችን ውስጥ የአባትነት፣ የወንድማማችነት መንፈስ ጠፍቶ የሥራ ቦታ ወይም ሌላ ዓይነት ግንኙነት የሚመስል ግንኙነት መኖሩ ነው”

በማለት ለዕለቱ ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኗቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
14 March 2020, 18:06
ሁሉንም ያንብቡ >