ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “መጠለያ የሌላቸውን በጸሎታችን እናስታውስ”!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 22/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሰረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ራስን ለመጠበቅ ሰዎች በቤታቸው በሚገኙበት በዚህ ወቅት በመጠለያ እጦት በየጎዳናው የቀሩትን በጸሎታችን እናስታውስ ብለው። ይህን በመገንዘብ እያንዳንዱ የማኅበረሰብ አባል የቻለውን ዕርዳታ እንዲያደረግ አደራ ብለው ቤተክርስቲያንም በበኩሏ መጠለያ አልባ የሆኑትን ተቀብላ እንድታስተናግድ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዛሬው ዕለት ከኦሪት ዘኁልቍ 21፡4-9 እና ዮሐ. 8፡21-30 ተወስደው በተነበቡት እና የእባብ ምሳሌን በሚናገሩት ቅዱሳት ንባባት ላይ በማስተነትን ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን አቅርበዋል።  

የጥንት እባብ፣

“እባብ ከሌሎች ፍጥረታት ጋር መልካም ዝብድና ያለው እንስሳ አይደለም። በመሆኑም ከሰይጣን ጋር ይመሰላል። በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ሰይጣን እባቦችን ለኃጢአት ምክንያት እንዲሆኑ መጠቀማቸው ተጠቅሷል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ እባብ የሚነድፍ፣ የሚመርዝ፣ የሚጎዳ እና የሚገድል አደገኛ መሆኑ ተጠቅሶ እናገኛለን”።    

እባብ የሰይጣን ምሳሌ ነው፣

ዛሬ በተነበበው የመጀመሪያ ንባብ፣ ከኦሪት ዘኁልቍ 21፡4-9 ላይ እንደተጻፈው ሰዎች እጅግ ስለ ደከማቸው ሩቅ መንገድ ማጓዝ አቃታቸው። የሚበላ እና የሚጠጣ ስላልነበራቸው አማረሩ፤ ከሰማይ የሚወርደውን መና መመገብ ሰለቻቸው።

“በየቀኑ ተመሳሳይ ነገር ሆነ፤ ‘በምድረ በዳ እንድንሞት ከግብፅ ያወጣችሁን ለምንድ ነው? ምግብ የለ! ውሃ የለ! ይህን የማይረባ ምግብ ሰውነታችን ተጸይፎታል’ ሲሉ ተናገሩ። በግብጽ ምድር በቂ የሚበላ እና የሚጠጣ ነገር አግኝተን በመልካም ሁኔታ እንኖር ነበር። እግዚአብሔርም በዚህ ወቅት ህዝቡን መታገሥ የማይችል ይመስላል፤ ተቆጥቷልም፤ ቁጣውም አንዳንድ ጊዜ ይታያል። ‘በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር መርዘኛ እባቦችን ሰደደባቸው፤ ሕዝቡን ነደፉ፤ ብዙ እስራኤላውያንም ሞቱ’ (ዘኁል. 21፡6)። በዚያን ጊዜ እባብ የሰይጣን ምሳሌ ሆኖ ይቀርብ ነበር። እርሱን በሚያዩበት ጊዜ ኃጢአት መሥራታቸውን በመገንዘብ፣ በስሕተታቸውም ይጸጸቱ ነበር”።   

ሙሴ በእንጨት ላይ የሰቀለው እባብ እንደ ጣኦት ሊቆጠር ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ጣኦት ሳይሆን ትንቢት ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሙሴ በእንጨት ላይ የሰቀለው እባብ ወደ ፊት ምን እንደሚሆን የሚናገር ትንቢት ነው ብለዋል። ኢየሱስም እባብ በእንጨት ላይ መሰቀሉ በራሱ የሚደርስ የመስቀል ላይ መከራን የሚናገር የጥንት ትንቢት እንደሆነ ማስታወሱን ተናግረዋል።     

“የትንቢቱ መልዕክት ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ኃጢአት መቀበሉን ያስረዳል። እርሱ ፈጽሞ ኃጢአት አልሠራም። ቅዱስ ጴጥሮስ በመልዕክቱ እንደሚናገረን የእኛን ኃጢአት በሙሉ እርሱ ተቀበለው። ወደ ቅዱስ መስቀል ቀና ብለን ስንመለከት ስለ እኛ የተሰቃየውን ኢየሱስ ክርስቶስን እናስባለን፤ ይህም እውነት ነው። ወደዚህ እውነት ለመድረስ ታዲያ አንድ ጊዜ ቆም ብለን ማሰብ ያስፈልጋል። ‘በዚህ ወቅት እንደ ኃጢአተኛ ተቆጥረሃል፣ ራስህንም ኃጢአተኛ አድርገሃል’። ኃጢአታችንን በሙሉ እርሱ ተሸከመው። የሙሴ ሕግ መምህራን በጠላትነት ተነሳስተው እርሱን አልፈለጉትም። ይህ ሁሉ እዉነት ነው። ከእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘው እውነት ‘ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው ራሱን ኃጢአተኛ በማድረግ የእኛን ኃጢአት ሊሸከም ነው’ የሚል ነው”።

አሰላስሉ ፣ ጸልዩ ፣ ምስጋናን አቅርቡ፣

ይህን እዉነት በመገንዘብ ክርስቲያኖች በቅዱስ መስቀል ላይ ማሰላሰልን የዘወትር ልማድ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ቅዱስ መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ሊበዠን እስከ ሞት ድረስ ራሱን ለስቃይ አሳልፎ የሰጠበት ነው። ይልቁንም እርሱ የስቃይ ሽንፈትን የቀመሰበት ጊዜ ነበር። ብቻውን ሆኖ የእኛን ኃጢአት ለመሸከም የመረጠው እና ራሱን በሞት እንዲቀጣ ሙሉ በሙሉ የአባቱ ፈቃድ መሆኑን የተረዳበት ጊዜ እንደነበር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

‘ይህን ሃቅ በመረዳት ወደ ድምዳሜ ላይ መድረስ ቀላል ባይሆንም ቆም ብለን ማሰላሰል፣ መጸልይ እና ምስጋናን ማቅረብ ያስፈልጋል’።         

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያሳረጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመፈጸማቸው በፊት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ባቀረቡት ጸሎት

‘የሰማያት እና የመላዕክት ንግሥት፣ የምሕረት ምንጭ የሆንሽ እናታችን ሆይ ለዓለም በሙሉ ብርሃንሽ ይብራ፤ ከሴቶች ሁሉ በላይ የምትወደጂ ቅድስት ድንግል ማርያም ለምኚልን’” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ፣
31 March 2020, 16:29
ሁሉንም ያንብቡ >