ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ለሆኑ ሰዎች በሙሉ ጸሎት ማድረግ ይገባል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት በየካቲት 30/2012 ዓ.ም ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ቅዱስነታቸው ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት በእሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በስፋት እየተስተዋለ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ለሆኑ ሰዎች ጸሎት እንደ ሚያደርጉ ቅዱስነታቸው የገለጹ ሲሆን “በእነዚህ ቀናት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለታመሙ ፣ ለዶክተሮች ፣ ለነርሶች፣ በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ ለተሰማሩ ሰዎች፣ ለሠራተኞች ፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት ውስጥ ላሉ አዛውንቶች ፣ ለእስረኞች ይህንን መስዋዕተ ቅዳሴ አቀርባለሁ” ብለዋል። በእለቱ መስዋዕተ ቅዳሴ የመግቢያ ጸሎት ላይ ያለውን “ጌታ ሆይ አድነኝ፣ ማረኝ። እግሮቼ በተደላደለ መሬት ላይ ይቆሙ ዘንድ፣ በጉባሄው ውስጥ ጌታን እባርከው ዘንድ እርዳኝ” የሚለውን ጸሎት እያንዳንዳችን በእዚህ ወቅት በጋራ ልንደግመው የሚገባን ጸሎት ነው ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን እርሳቸው በበኩላቸው በኮሮና ቫይረስ ተጠቂ የሆኑ ሰዎችን በጸሎታቸው እንደ ሚያስቡዋቸው ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በእለቱ ከትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ (9፡4-10) ላይ ተወስዶ በተነበው የእግዚአብሔር ቃል ላይ መሰረቱን ባደርገው ስብከታቸው ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “ኃጢአትን መናዘዝ” አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስነታቸው መግለጻቸው የተጠቀሰ ሲሆን “ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ጸለያለሁ፤ ተናዘዝሁም፤ ከሚወዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ሁሉ ጋር የፍቅር ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ ታላቅና የተፈራህ አምላክ፤ ጌታ ሆይ፤ እኛ ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናልም፤ ክፋትን አድርገናል፤ ዐምፀናልም፤ ከትእዛዝህና ከሕግህ ዘወር ብለናል” በማለት ሕዝቡ ኃጢያተኛ መሆኑን ተገንዝቦ እንደ ነበረ የገለጹ ሲሆን 'ይህ የኃጢያታችንን መናዘዝ ፣ ኃጢአት እንደሠራን ማወቃችን  በራሱ ከኃጢአት መንገድ ለመመለስ የሚረዳ አንድ እርምጃ ነው ብለዋል።

ለምስጢረ ንስሐ ዝግጅት ማደረግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት ጨምረው እንደ ገለጹት “ምስጢረ ንስሐን ለማድረግ ራሳችንን በምናዘጋጅበት ወቅት ‘የህሊና ምርመራ’ ተብሎ የሚጠራውን ማድረግ ይኖርብናል” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን  ከዛም በአዕምሯዊ ደረጃ በሚከናወኑ ኃጢአቶች ዝርዝር መካከል እና በልባችን ውስጥ የሚገኙ ኃጢያቶች ዝርዝር መካከል ያለውን ልዩነት መፈተሽ እንደ ሚገባ” ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል። ይህንን በተመለከተ ቅዱስነታቸው ሲናገሩ . . .

 በአዕምሮ ውስጥ ያለውን ኃጢያት በመዘርዘር “ኃጢአት ሠርቻለሁ› በማለት ለካህኑ በምንናገርበት ወቅት በካህኑ አማካይነት እግዚአብሔር ይቅር ይለኛል።  በእዚህ መልኩ የምናደርገው ኑዛዜ የበደልኩት ወይም የተሳሳትኩት ነገር እንደ ነበረ በማሰብ የማደርገው ኑዛዜ በአዕምሮ ውስጥ ይቆያል። እውነተኛ ንስሐ ወይም ኑዛዜ ግን በልቡ ውስጥ መቆየት አለበት።

ከአእምሮ ወደ ልብ የሚንቀሳቀስ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት ጨምረው እንደ ገለጹ “ኃጢያታችንን ከልባችን በመነጨ መልኩ መናዘዝ ይኖርብናል፣ ነቢዩ ዳንኤል እንደሚለው የጌታ ፍትህ ከጎንህ ነው” በማለቱ የተነሳ አሳፋሪ ተግባሮቻችንን ሳንደብቅ እና ሳንፈራ መናዘዝ ይኖርባናል” ብለዋል። ይህንን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . . .

ኃጢአት መሥራቴን ስገነዘብ ፣ በደንብ እንዳልጸለይኩ በልቤ ውስጥ ከተሰማኝ የሀፍረት ስሜት ወደ እኔ ይመጣብኛል. . . በኃጢያታችን እያፈርን መጠየቅ የፈለግነው ፀጋ ነው። የእፍረት ስሜቱን ያጣ ሰው፣ ሥነ-ምግባርን የማጣት ስሜትን ያጣ  ሰው ለሌሎች አክብሮት ያጣል። በተመሳሳይ መልኩ እግዚአብሔር ሆይ አቤቱ እኛ እንደ ነገሥታቶቻችን፣ መሳፍንቶቻችን፣ አባቶቻችን እኛ ኃጢአት ስለ ሠራን አቤቱ አምላካችን ሆይ ራራልን በማለት በትህትና ልንጠይቀው ይገባል።

የእግዚአብሔርን ልብ እንነካለን

ኃጢአት መሥራታችንን አስታውሰን በተግባራችን የምናፍር ከሆነ ይህ ስሜት ምስጢረ ንስሐ በምናደርግበት ወቅት በሚታከልበት ጊዜ ​​“ይህ የእግዚአብሔርን ልብ ይነካዋል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው የአፍረት ስሜት የእግዚአብሔርን ምህረት እንድንለማመድ ያደርገናል ብለዋል። ስለሆነም ምስጢረ ንስሐ ማደረግ የኃጢያትን ዝርዝር ማንበብን አያካትትም፣  ነገር ግን “እጅግ በጣም ሩኅሩህ ፣ መልካም እና ጻድቅ ለሆነው አምላክ” የነገርነው ምስጢራችን ነው ብለዋል። ከዚያ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን ሲደመድሙ “ዛሬ በኃጢያታችን ማፈር እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን እንጠይቅ። ጌታ ለሁላችንም ይህንን ጸጋ ይስጠን” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
09 March 2020, 14:11
ሁሉንም ያንብቡ >