ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ቤተክርስቲያን ለተራቡት የዕርዳታ እጇን ትዘርጋ”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ መጋቢት 19/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ ተላላፊው የኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት አንዳንድ ቤተሰቦች በረሃብ መሰቃየት መጀመራቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም በዚህ የመከራ ወቅት ቤተክርስቲያን የእርዳታ እጇን መዘርጋት እንዳለባት አሳስበው ካህናት እና ደናግል ከሕዝብ ወገን መሆናቸውን ሳይዘነጉ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለድሆች እና በሕመም ለሚሰቃዩት የሚያቀርቡትን ዕርዳታ ማቋረጥ እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዛሬ መጋቢት 19/2012 ዓ. ም. ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በቪዲዮ ምስል በኩል በቀጥታ የተሰራጨው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት በጣሊያ እና በሌሎች አገሮችም የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት በቁምስናዎች እንዳይፈጸም ከተከለከለ ወዲህ ለሃያኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ባቀረቡት ጸሎታቸው ወረርሽኙ ባስከተለው የኤኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በረሃብ የሚሰቃዩትን ቤተሰቦች በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባሰሙት ንግግር በዓለም ዙሪያ በኮሮና ቫይረስ መዛመት ምክንያት በበርካታ ቤተሰቦች ዘንድ የረሃብ ስቃይ እየገባ መሆኑን አስታውሰው ምዕመናን በሙሉ በያሉበት እነዚህን ቤተሰቦች በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል።

ከዮሐ. 7፡40-53 ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጵሳት ፍራንችስኮስ፣ ካህናት እና ደናግል ለድሆች፣ ለተራቡት እና ለታመሙት በሙሉ ሲያቀርቡ የቆዩትን እርዳታ አሁን በችግር ወቅትም አጠናክረው እንዲቀጥሉበት አደራ ብለዋል። ካህን ከምዕመኑ ራሱን ሳያገል መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ማበርክት አለበት ብለው ከምዕመናን ዘንድ የተመረጠ መሆኑንም መዘንጋት የለበትም ብለዋል።

በዕለቱ በተነበበው የውንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከታቸውም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት የተማረኩት የአካባቢው ሰዎች ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ ለረጅም ጊዜ ኢየሱስን ያደምጡት ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት በልባቸው ውስጥ ዘልቆ ይገባ ስለነበር ነው። የሕግ አዋቂዎች ኢየሱስ ክርስቶስን ይቃወሙት ነበር። ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ የማስተማር ሥራውን ያከናውን የነበረው ሕጋቸውን በመከተል ስላልሆነ ነው። በዚህም የተነሳ በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ። አንዱ ወገን ኢየሱስን የሚከተል፣ ሌላው ወገን ደግሞ የሙሴ መምህራን እና የሕግ አዋቂዎችን፣ ሌላው ደግሞ የእስራኤል ሕዝብ መሪዎችን የሚከተሉ ናቸው። የሙሴ ሕግ መምህራን እና ፈሪሳዊያን ኢየሱስን ይከተሉ በነበሩ ሰዎች ላይ ያፌዙባቸዋል። ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ የተገኘው ቅዱስ ሕዝብ በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን የተቀሩት የሕግ መምህራን እና አዋቂ ነን ባዮች ግን ከኢየሱስ ክርስቶስ ተለይተዋል። አዋቂዎች እና ምሁራን ናቸው፣ ነገር ግን እውነተኛውን እና ትክክለኛው መንገድ ማየት ተሳናቸው። የሙሴ ሕግ መምህራን ትልቁ  ስህተት የአንድ ሕዝብ ወገን መሆናቸውን አለማወቅ ነው።

“የእግዚአብሔር ሕዝብ ትክክለኛ ምክንያቱን ማስረዳት ባይችሉም ኢየሱስን እስከ መጨረሻው መከተልን አያቋርጥም። ኢየሱስ በርካታ ሕዝብን በጥቂት ዳቦ የመገባቸውን ታሪክ ስናስተውስ፣ በዚያን ዕለት በርካታ ሰዎች ሙሉ ቀን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ዋሉ። ሐዋርያትም እስኪሰለቻቸው ድረስ ሕዝቡን ሲያገለግሉ ዋሉ። በመጨረሻም እንዲሸኛቸው ኢየሱስን ጠየቁት። ሐዋርያትም ቢሆኑ ከሕዝባቸው መራቅ፣ ከሕዝባቸው መለየት ፈለጉ። የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆናቸውን ከልብ አለተገነዘቡም ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ የሰጣቸው መልስም “የሚበላ ነገር ስጧቸው” የሚል ነበር።

አዋቂዎች እና ጠቢባን ከሕዝባቸው የመለየት እና የመራቅ ልማድ በአዲስ ኪዳን ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከብሉይ ኪዳንም ጀምሮ ያለ ነው። በኤሊ ልጆች ዘመን በሕዝቦች መካከል መናናቅ ነበ፤ የእግዚአብሔርን ሕግ ማክበር ሲጀምሩ እነዚህ ጠንቋዮች ናቸው ይላሉ። ይህ ደግሞ የእግዚአብሔርን ሕዝብ መናቅ ነው። እኛም እንደምናውቀው አዋቂ ነን ከሚሉ ሰዎች ሕዝብን መናቅ ከቶ አይጠበቅባቸውም። ነገር ግን የእግዚአብሔር ህዝብ ታላቅ ጸጋን አግኝቷል።

የዕውቀት ጸጋን አግኝቷል። መንፈስ ቅዱስ የሚገኝበትን ቦታ የማወቅ ጥበብ አግኝቷል። እንደ እኛ ኃጢአተኛው ወገን ግን ሁሌ ኃጢአተኛ ነው። ቢሆንም ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚወስድ መንገድ የቱ እንደሆነ በሚገባ ያውቀዋል።

አወቅን ባይ ሰዎች ትልቁ ችግር የገዛ ራሳቸውን ወገን፣ የተወለዱበትን ማሕበረሰብ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወገን መሆናቸውን አለማወቅ ነው። ፊታቸውን ወደ ሌላ ወገን መለሱ። በእነዚህ ቀናት እንደምሰማው ከሆነ ካህናት እና ደናግል ወደ ድሆች፣ ወደ ሕሙማን፣ ወደ አረጋዊያን ዘንድ ለመሄድ እና አገልግሎት ለመስጠት ያመነታሉ። በኮሮና ቫይረስ እንዳይያዙ በማለት ከቤት እንዳይወጡ ይደረጋል። ለታመሙት ሕክምናን ማድረግ፣ ለተራቡት ምግብ የማደል አገልግሎት የመንግሥት ነው ይላሉ።  

ካህናት እና ደናግል ሕዝባቸውን ያማያገልግሉ ከሆነ፣ ከሕዝባቸው ጋር ለመዋል ፍላጎት የሚያንሳቸው ከሆነ አንድ ነገር ይጎድላቸዋል ማለት ነው። ለሕግ አዋቂዎች፣ ለሙሴ መምህራን እና ለፈሪሳዊያን የሚጎላቸው ነገር ለእነርሱም ይጎላል። ከሕዝባቸው ወገን ያለመሆን ነው። እግዚአብሔር ዳዊትን ‘ከመንጋው ውስጥ አግኝቼሃለሁ’ ያለውን ማስታወስ ያስፈልጋል። ስለዚህ እግዚአሔር ከራሳቸው ሕዝብ መካከል እንደመረጣቸው ማወቅ ያስፈልጋል።

ሕዝቡ ቀኑን በሙሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከዋሉ በኋላ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ነገር ግን ኒቆዲሞስ አንድ ነገር ታየው። ልቡ በፍርሃት የተዋጠ ቢሆንም ደፋር ነበር። ታማኝም ስለነበር ሕጎችን በማገላበጥ አንዳንድ ሃስቦችን ያፈልቅ ነበር። ወደ ኢየሱስ ቀርቦ መምህር ሆይ! ሕጋችን ለአንድ ሰው ፍርድ የሚሰጠው ሰውየውን ከማዳመጥ አስቀድሞ ነው፣ ምን እንደሚያደርግ ከመሰማት በፊት ነው አለው። ኢየሱስም ሕጋችሁ የሚለውን በመከተል መልስ አልሰጥም። አንተም ምናልባት የገሊላ ክፍለ ሀገር ሰው ነህ፣ አዋቂ አይደለህም፣ ከገሊላ ነብይ አይገኝም አለው።

ዛሬ በርካታ ሰዎች እግዚአብሔርን ለማገልገል ብቃት ያላቸው ሰዎች ከሕዝባቸው ጎን ቆመው አገልግሎታቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። በርካታ ካህናት ሕዝባቸውን ማገልገል አይደክማቸውም። ብርድ የማይበግራቸው፣ ረጅም መንገድ ተጉዘው ቅዱስት ምስጢራትን ለምዕመናን በማደል ላይ የሚገኙ በርካታ ካህናት መኖራቸውን ተገንዝቤአለሁ። የእነዚህ ካህናት ቀዳሚ ተልዕኮ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ሕዝብ ዘንድ ማድረስ ነው። ታዲያ እኛስ ከየትኛው ወገን እንመደባለን። በሙሉ ልብ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ወገን መሆችንን ተገንዝበናል? የእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ያለው አንድነት አይፈርስም፣ አንድነቱ ዘላቂ ነው። ከሕዝባቸው ራሳቸውን የሚያርቁ የሙሴ ሕግ መምህራንን እናስታውስ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለተከታዩ ጢሞቴዎስ ‘እናትህን እና አያትህን አስታውስ’ በማለት መክሮት ነበር” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያቀረቡትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚከተለውን የቅዱስ ቁርባን ቡራኬን ሰሎት በማቅረብ አጠናቅቀዋል፥

ኢየሱስ ሆይ! ራሴን ዞር ብዬ በመመልከት የተሰበረውን ልቤን ይዤ ለንስሐ ወደ እግሮችህ አጠገብ ቀርቤአለሁ። በፍቅር በገለጥካቸው ቅዱሳት ምስጢራት በኩል አክብርሃለሁ፤ በደሳሳ ቤቴ፣ አንተን በልቤ ውስጥ ልቀበልህ እመኛለሁ፤ ከቅዱሳት ምስጢራት ኅብረት የሚገኘውን ደስታ በመጠባበቅ ፣ መንፈስ ቅዱስን መቀበል እፈልጋለሁ፤ ኢየሱስ ሆይ ፣ ወደ እኔ ና! በሕይወቴ ዘመን እንዲሁም በሞቴ ሁሉ ፍቅርህ ይብዛልኝ፤ እምነቴ እና ተስፋዬ አንተው ነህና እወድሃለሁ፤ አሁንም፣ ዘወትርም ይሁን”።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
28 March 2020, 17:11
ሁሉንም ያንብቡ >