ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ሆነው፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ሆነው፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሕይወታቸውን በመሰዋት ላይ የሚገኙ የጤና ባለሞያዎችን በጸሎት አስታውሰዋል።

መጋቢት 11/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ የኮሮና ቫይረስ ክፉኛ ባጠቃቸው፥ ቤርጋሞ፣ ትሬቪሊዮ፣ ብሬሻ እና ክሬሞና በተባሉ የሰሜን ጣሊያን ክፍላተ ሀገራት ተሰማርተው የሕክምና አገልግሎትን በመስጠት ላይ የሚገኙ የሕክምና ባለሞያዎችን እና የጤና ረዳቶቻቸውን በጸሎት አስታውሰዋል። በተጨማሪም የሕክምና አግልግሎቶችን እና ሌሎች ዕርዳታዎችን በማስተባበር ላይ የሚገኙ የመንግሥት ባለ ስልጣናትን በጸሎት አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በዛሬው ዕለት ባቀረቡት ስብከተ ወንጌል በወረርሽኙ ላለመጠቃት እቤታቸው እንዲቀመጡ የታዘዙ የጣሊያን ቤተሰቦች፣ ካህናትን በቀላሉ ካለማግኘት የተነሳ የቤተክርስቲያን ምስጢራትን በቀጥታ ማግኘት ባይችሉም ዘወትር በጸሎት እንዲተጉ እና ከይቅር ባይ እግዚአብሔር ምህረትን እንዲለምኑ አደራ ብለዋል።         

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከሰሜን ጣሊያን፣ ቤርጋሞ ክፍለ ሃገር መልዕክት እንደ ደረሳቸው ያስታወቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ ክፍለ ሃገር እና በጎረቤት ክፍላተ ሃገራት የሕክምና አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙ የጤና ባለሞያዎችን እና ረዳቶቻቸውን በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው የሚል መልዕክት ከአንድ ካህን የደረሳቸው መሆኑን ገልጸዋል። ይህን በማስታወስ ባሰሙት ስብከት፣ የሌሎችን ሕይወት ለማዳን ሲሉ የራሳቸውን ሕይወት የሰው እና በመሰዋት ላይ የሚገኙ ሐኪሞች፣ የጤና ረዳቶች፣ በጎ ፈቃደኞች እና የአግልግሎት አስተባባሪዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ የሞት አደጋ ያንዣበበትን ሕዝብ ከስቃይ እና ከጭንቀት ነጻ ለማውጣት ሳይታክቱ ጥረት በማደረግ ላይ የሚገኙትን በጸሎታችን ልናስታውሳቸው ይገባል ብለዋል። ለዕለቱ በተመደበው የመጀመሪያ ንባብ፣ በትንቢተ ሆሴዕ 14:2-10 ላይ በተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በማስተነተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቸሩ እግዚአብሔር ለሚራራለት ሕዝቡ ምሕረትን እንጂ ለፍርድ አሳልፎ የማይሰጥ መሆኑን አስረድተው፣ እግዚአብሔርን ከሁሉ አብልጦ ከማፍቀር በሚመነጭ የልብ መጸጸት ምሕረትን ለሚለምኑት ሁሉ እግዚአብሔር ምሕረቱን የሚልክላቸው መሆኑን አስረድተዋል።  

የዐብይ ጾም ወቅት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይበልጥ የሚነጋገርበት ወቅት መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እኛም ታዲያ በዚህ ወቅት ወደ ግል ሕይወታችን ተመልሰን የእግዚአብሔርን ምሕረት ተገንዝበን ወደ ርህሩህ አባት ዘንድ መመለስ ይገባል ብለዋል። በኃጢአት ብዛት የምናፍር ቢሆንም እንደ እስራኤል ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰን ቁስላችንን መፈወስ ያስፈልጋል ብለዋል። ወደ ፈዋሹ እግዚአብሔር መመለስ ማለት ከእርሱ ዘንድ ርቀን ከሄድንበት ተመልሰን ወደ ቤቱ መግባት ማለት ነው ብለዋል። 

በሉቃ. ምዕ. 15 ላይ ጠፍቶ የተገኘውን ልጅ ታሪክ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ድርሻውን ከአባቱ ተቀብሎ ወደ ሩቅ አገር ሄዶ የቆየው ልጅ ከሄደበት ተመልሶ ወደ አባቱ ቤት ሲመለስ አባቱም ከሩቅ ሆኖ ይጠብቀው እንደነበር እና በተመለሰ ጊዜም በደስታ የተቀበለው መሆኑን አስታውሰዋል።

ወደ ብርሃነ ትንሳኤው መታሰቢያ ክብረ በዓል መቃረባችንን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቅዱሳት ምስጢራትን፣ ከእነዚህም መካከል የምስጢረ ንስሐን ለመፈጸም የሚጠባበቁ በርካታ ምዕመናን መኖራቸውን የተገነዘቡት ቅዱስነታቸው የምሕረት አምላክ በኃጢአታቸው ብዛት ከልብ ተጸጸተው ምሕረትን ለሚለምኑት ሁሉ ምሕረትን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስረድተው “እግዚአብሔር ከእኛ የሚጠብቀው ወደ እርሱ መመለስን ብቻ ነው” ብለዋል።   

20 March 2020, 18:33
ሁሉንም ያንብቡ >