ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በወረርሽኙ ምክንያት ፍርሃት ውስጥ ለገቡ ሰዎች እንጸልይ አሉ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 21/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው ዛሬ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎታቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በፍርሃት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በሙሉ አስታውሰዋል። እግዚአብሔርን ማመስገን ይኖርብናል ያሉት ቅዱስነታቸው በማከልም ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን ማግኘት እንችል ዘንድ ኃጢአቶቻችንን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዛሬም እንደ ባለፉት ቀናት ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በቪዲዮ ምስል በቀጥታ በተሰራጨው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ የተጀመረውን የዓብይ ጾም አምስተኛ ሳምንት ምክንያት በማድረግ ከመዝ. 55:2 ላይ “ወደ እኔ ተመልከት፤ መልስልኝም። በውስጤ ታውኬአለሁ፤ ተናውጬአለሁም” በማለት ወደ እግዚአብሔር የቀረበውን ጸሎት በማስቀደም በጀመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ያጋጠማቸውን ፍርሃት መቋቋም ያልቻሉ ሰዎች ብርታትን እንዲያገኙ በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል።

ከዳን. ምዕ. 13:1-9 ፣ 15-17, 19-30 ፣ 33-62 እና ከዮሐ. 8:1-11 ተወስዶ በተነበበው በዕለቱ የቅዱሳት መጽሐፍት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የሞት ቅጣት ፍርድ የተፈረደባቸው ሁለት ሴቶች፣ የንፁህ ሱዛን እና የሌላኛዋ አመንዝራ ሴት ታሪክ አስታውሰው፣ በእነዚህ ሁለት ሴቶች ላይ ክሳቸውን ያቀረቡትም የሞት ቅጣት ፍርድ የጣሉትም በሙስና የወደቁ ብልሹ ዳኞች እና ግብዝ ቀራጮችና ፈሪሳዊያን መሆናቸውን አስታውሰው እግዚአብሔር እነዚህ ሁለት ሴቶች ከተመሠረተባቸው ክስ ነጻ በማውጣት፣ ፍትህን በማውረድ ከተበየነባቸው የሞት ቅጣት ፍርድ ነጻ ያወጣቸው መሆኑን አስረድተዋል። በዛሬው ዕለት በተነበቡት ቅዱስት መጽሐፍ ውስጥ የእግዚአብሔር ምሕረት እና ፍትህ በሚገባ መጠቀሱን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጽሐፈ መዝ. 23፡1-4 ላይ “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል። በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ ብሄድ እንኳ፣ አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ፣ እነርሱ ያጽናኑኛል” የሚለውን ጥቅስ አስታውሰው እግዚአብሔርን ማመስገን ዘወትር ማመስገን እንደሚገባ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን ማግኘት እንችል ዘንድ ኃጢአቶቻችንን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።   

“በመጽሐፈ መዝ. 23 ላይ “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል። በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ ብሄድ እንኳ፣ አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ፣ እነርሱ ያጽናኑኛል” የሚለውን ጸሎት በሕብረት ጸልየናል።

ዛሬ በተነበቡት ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት የተገለጹት ሴቶች ልምድ ይህ ነው። አንደኛዋ ሴት ምንም በደል ሳትፈጽም የሐሰት ክስ ተመስርቶባታል፣ ስም የማጥፋት ወንጀልም ተፈጽሞባታል። ሌላኛዋ ሴት በማመንዘሯ ምክንያት ኃጢአት ሰርታለች። ሁለቱም የሞት ቅጣት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል። አንድ የቤተክርስቲያን አባት የእነዚህን ሁለት ሴቶች ታሪክ ከቤተክርስቲያን ሕይወት ጋር አመሳስለዋል። ቤተክርስቲያን ቅዱስ ብትሆንም በውስጧ ኃጢአተኞችን ይዛ ትገኛለች። በላቲን አሜሪካ ውስጥ፥ “ከኃጢአተኛ ልጆቿ ጋር የምትኖር ቅድስት” የሚል አባባል አለ።

ሞት የተፈረደባቸው ሁለቱ ሴቶች በተበየነባቸው ቅጣት በጣም ተጨንቀው እና ደንግጠው ነበር። ሱዛን ግን እምነቷን በእግዚአብሔር ላይ አድርጋለች። በሌላ ወገን ሁለት ዓይነት ሰዎች መኖራቸውን እንረዳለን። ሁለቱም ወገኖች ቤተክርስቲያንን ለማገልገል የቆሙ ዳኞች እና የሕግ አዋቂዎች ናቸው። የቤተክህነት ወገን ሳይሆኑ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ በፍርድ አሰጣጥ እና በሕግ መምህርነት ሥራ ላይ የተሰማሩ የተለያዩ ሰዎች ናቸው። የመጀመሪያዎቹ በሱዛን ላይ የሐሰት ክስ የመሠረቱ ሙሰኛ ዳኞች ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ምሳሌዎች እነዚህ ሰዎች በሙስና የወደቁ፣  በእግዚአብሔር የማያምኑ እና ለሌሎች ሰዎች ምንም ግድ የማይላቸው መሆኑን ይናገራል። ሁለተኛው ወገን ምንም እንኳን በሙስና የወደቁ ሳይሆኑ ነገር ግብዞች መሆናቸውን ይናገራል።

ከእነዚህ ሁለት ሴቶች መካከል አንደኛዋ በግብዞች እጅ ወድቃለች። ሌላኛዋ በሙሰኞች እጅ ወድቃለች። ምንም ማምለጥ አልቻሉም። “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ ብሄድ እንኳ፣ አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ፣ እነርሱ ያጽናኑኛል” ሁለቱም ሴቶች በጨለማ ውስጥ ሆነው ወደ ሞት ይጓዙ ነበር። የመጀመሪዋ በእግዚአብሔር የታመነች እና የእርሱን እገዛ ያገኘች ናት። ሁለተኛዋ ሴት በማመንዘሯ ምክንያት በሰዎች መካከል ከፍተኛ ውርደት እና ሃፍረት የተሰማት ናት። በወንጌል ውስጥ ባይጠቀስም በልቧ ውስጥ እርዳታን ትፈልግ ነበር።

በዚህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ለሚገኛ ሕዝብ የእግዚአብሔር እቅድ ምን ነበር? የሐሰት ክስ ለተመሠረተባት ሴት ፍትህን በማምጣት ከሞት ቅጣት ፍርድ አዳናት። በማመንዘር ለተከሰሰችው ሴትም ምሕረት አደረገላት። በሙስና ለወደቁት ዳኞች ፍርድን፣ ግብዞች ልባቸውን እንዲለውጡ በሕዝቡ መካከል ቆሞ “ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት እርሱ አስቀድሞ ድንጋይ ይወርውርባት” በማለት ያግዛቸው ነበር። ይህን እንደ ሰሙ፣ ከሽማግሌዎች ጀምሮ አንድ በአንድ ወጡ በማለት  ሐዋርያው ዮሐንስ ይናገራል። ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህ ሁለቱ ወገኖች በጥፋታቸው ተጸጽተው ወደ ምሕረት ይሚመለሱ ከሆነ ዕድል ሰጣቸው። በሙስና የታወቀው እና ለሌሎች ሰዎች ምንም ደንታ ለሌለው ዳኛ ምሕረትን አላደረገለትም። ምክንያቱም በሠራው ኃጢአት አልተጸጸተም፣ ልቡን በማደንደን ኃጢአቱን መመልከት አልቻለም፤ ምህረትንም አልጠየቀም። ይባስ ብሎ ሰዎችን መጉዳት ቀጠለ፤ ራሱንም በእግዚአብሔር ቦታ አስቀመጠ።

ለሁለቱ ሴቶች እንዲህ መለሰላቸው፥ ሱዛንን ከሙሰኞች እጅ ነጻ አወጣት፣ በሰላምም አሰናበታት። አምንዝራይቱንም  “እኔም አልፈርድብሽም፤ በይ ሂጂ፤ ከእንግዲህ ግን ኃጢአት አትሥሪ” አላት። በሕዝቡ ፊት ነጻ አሰናበታት። ኢየሱስ ክርስቶስ በወሰደው የመጀመሪያ ዕርምጃ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመሰገነ። በሁለተኛ ዕርምጃው ሕዝቡ ስለ እግዚአብሔር ምሕረት ምንነት ትምህርትን አገኘ።

እያንዳንዳችን የግል ታሪክ አለን። እያንዳንዳችን ኃጢአትን ሰርተናል። የማናስታውስ ከሆነ ቆም ብለን ማሰብ ያስፈልጋል። ወደ ልባችን ተመልሰን ካሰብን ኃጢአቶቻችንን ማግኘት እንችላለን። ያገኘን እንደሆነ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባል። የማንገኝ ከሆነ ራስን በማታለል እንደ ሙሰኛው ሰው እንሆናለን። ምሕረትን ወደሚሰጥ እግዚአብሔር እንመልከት። ማፈር ያለብን የቤተክርስቲያን አባል በመሆናችን ሳይሆን ኃጢአተኞች በመሆናችን ሊሆን ይገባል። ዛሬ በተነበበው ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ክርድቶስ የወሰዳቸውን እርምጃዎች በማስታወስ በእግዚአብሔር ምህረት ሙሉ እምነት ሊኖረን ይገባል። “ጌታ ሆይ! ለስምህ ክብር ስትል ወደ ትክክለኛ መንገድ ምራኝ” በማለት የእግዚአብሔርን ምሕረት በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል። በጨለማ ብጓዝም፣ በኃጢአት ውስጥ ብገኝም፣ አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ፣ እነርሱ ያጽናኑኛል” በማለት የምስጋን ጸሎትን ማቅረብ ያስፈልጋል“።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዛሬ መጋቢት 21/2012 ዓ. ም. ያቀረቡትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በፊት የሚከተለውን የቅዱስ ቁርባ ቡራኬ ጸሎትን አሳርገዋል፥

“ኢየሱስ ሆይ! ራሴን ዞር ብዬ በመመልከት የተሰበረውን ልቤን ይዤ ለንስሐ ወደ እግሮችህ አጠገብ ቀርቤአለሁ። በፍቅር በገለጥካቸው ቅዱሳት ምስጢራት በኩል አክብርሃለሁ፤ በደሳሳ ቤቴ፣ አንተን በልቤ ውስጥ ልቀበልህ እመኛለሁ፤ ከቅዱሳት ምስጢራት ኅብረት የሚገኘውን ደስታ በመጠባበቅ ፣ መንፈስ ቅዱስን መቀበል እፈልጋለሁ፤ ኢየሱስ ሆይ ፣ ወደ እኔ ና! በሕይወቴ ዘመን እንዲሁም በሞቴ ሁሉ ፍቅርህ ይብዛልኝ፤ እምነቴ እና ተስፋዬ አንተው ነህና እወድሃለሁ፤ አሁንም፣ ዘወትርም ይሁን”። 

ለመንፈስ ቅዱስ አደራ ከተሰጠው የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ከመውጣታቸው አስቀድመው “ሰላም ላንቺ” የሚለውን ጸሎት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ አቅርበዋል።

30 March 2020, 15:58
ሁሉንም ያንብቡ >