ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “በቤተክርስቲያን የታላቅነት መገለጫ አገልግሎት እንጂ ሥልጣን አይደለም”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ የካቲት 17/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ታላቅነት የሚገለጸው በአገልግሎት እንጂ በሥልጣን ደረጃ አለመሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም “የእግዚአብሔር ዋና ጠላት ዓለማዊነት ነው ብለው፣ ከዚህ ተለይቶ ዓለምን መቃወም የሚቻለው ብቸኛው መንገድ ራስን ዝቅ በማድረግ ሌሎችን በትህትና ማገልገል ስንጀምር ነው ” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ዛሬ ጠዋት በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ለተካፈሉት ካህናት ደናግል እና ምዕመናን፣ በዕለቱ በተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ላይ በመመርኮዝ ስብከታቸውን አቅርበዋል። ከማር. 9:30-37 ተወስዶ

በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስተንተን ባሰሙት ስብከት፣ ከመካከላችን ራሱን ከፍ ማድረግ የሚፈልግ ቢኖር ከሁሉ በፊት ራሱን ዝቅ በማድረግ ሌሎችን የሚያገለግል መሆን አለበት ብለው፣ በቅዱስ ወንጌል ቃል እንመራለን እየተባለ በሌላ ወገን በዓለማዊነት እየተመሩ ሌሎችን ማሰቃየት ወይም በሌሎች ላይ ሃያልነትን መቀዳጀት የእግዚአብሔር ጠላት ያደርጋል ብለዋል። በተቃራኒው ኢየሱስ ክርስቶስ ራስን ዝቅ በማድረግ ለሌሎችን ማገልገል እንደሚያስፈልግ ያስተምረናል ብለዋል።      

ኢየሱስ ወደ ቤት ከገባ በኋላም፣ “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለ ምን ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱ ግን በመንገድ ላይ የተከራከሩት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው በሚል ስለ ነበር ዝም አሉ። ከተቀመጠ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን ጠርቶ፣ “መጀመሪያ ለመሆን የሚፈልግ፣ ከሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ ይሁን” አላቸው (ማር. 9፡33-35)።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በዕለቱ ያቀረቡትን የወንጌል አስተንትኖ በመቀጠል እንደተናገሩት ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች እንደሚበልጡ አድርገው በሚቆጥሩበት ጊዜ ፣ በሰዎች መካካል ልዩነትን በሚያደርጉበት ጊዜ ወደ የዓለማዊነትን ባህርይ በመላበስ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጣት የእርሱ ጠላት ይሆንሉ ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በሌላው የወንጌል ክፍል ለደቀ መዛሙርቱ ከእኔ ጋር ከሆናችሁ የእኔ ወገን ናችሁ፣ ነገር ግን ከእኔ ጋር ያልሆናችሁ ከሆነ የሌላ ወገን ናችሁ በማለት የተናገረውን አስታውሰው፣ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰውን የኢየሱስ ክርስቶስ ንግግር በሚገባ ሰምተው በሌላ ወገን ራሳቸውን ከሌሎች ሰዎች በመነጠል ፣ ከፍ ሊያደርጉ የሚፈልጉ ሰዎች ራሳቸውን የእግዚአብሔር ጠላት ያደርጋሉ ብለዋል።         

25 February 2020, 18:11
ሁሉንም ያንብቡ >