ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “እግዚአብሔር ከኃጢአት መንገድ እንድንመለስ ይፈልጋል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጥር 26/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ከተገኙት ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን ጋር ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት ንጉሥ ዳዊት በልጁ ሞት በማዘን ያሰማው ለቅሶ እግዚአብሔር ለእኛ ያለንን ፍቅር የሚገልጽ ነው ብለው እግዚአብሔር ፍቅሩን ለእኛ የገለጠልን ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እስኪሞት ድረስ ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባሰሙት ስብከታቸው እግዚአብሔር አባታዊ ፍቅሩን ለእኛ ከመግለጽ ምን ጊዜም ወደ ኋላ አይልም ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለዛሬ በተመደበው የመጀመሪያ ንባብ፣ ከ2ኛ ሳሙኤል 18:9-10 ፣ 14:24-25 እና 19:1-4 ተውስዶ በተነበበው ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው ዳዊት የልጁን አቤሴሎም ሞት በተረዳ ጊዜ እጅግ በማዘን ማልቀሱን አስታውሰዋል። በዚህ የመጀመሪያ ንባብ ላይ አቤሴሎም አባቱን ዳዊትን በመቃረን ከእርሱ ጋር ያደረገው ጦርነት ያበቃ መሆኑን በሚገልጽ ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንጉሥ ዳዊት ዙፋኑን ለልጁ ሊያወርሰው ይፈልግ እንደነበር ነገር ግን ልጁ አቤሴሎም ሕዝቡን የሚያስጨንቅ ጦርነት በማወጁ እና በዚህም ከአባቱ መለየቱን እና ዳዊትም ሕይወቱን ከሞት ለማትረፍ  ኢየሩሳሌምን ለቆ ለመሰደድ መገደዱን አስታውሰዋል።

የንጉሥ ዳዊት እንባ የእግዚአብሔርን ልብ ይገልጻል፣

የጦርነቱን ዜና ለመስማት በጉጉት ይጠብቅ የነበረው ንጉሥ ዳዊት የልጁን የአቤሴሎም በጦርነት መካከል መሞቱን በተረዳ ጊዜ እጅግ በማዘን ልጄ አቤሴሎም! ልጄ አቤሴሎም! ባንተ ምትክ እኔ በሞትኩ! በማለት በምሬት ማልቀሱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። በቅርብ ሆነው የንጉሥ ዳዊትን እጅግ ማዘን የተመለከቱ በሙሉ፣

ለምን ታለቅሳለህ? ልጅህ አቤሴሎም ያንተ ጠላት ነበር፤ አባትህነትንም የካደ ነበር፤ በአንተ ላይ የስድብ ቃላትን በማውጣት እጅግ አዋርዶሃል፣ አሰቃይቶሃልም፤ ስለዚህ እርሱ በመሞቱ እና አንተ ድል ስለተቀዳጀህ ልትደሰት ይገባል። ንጉሥ ዳዊት ግን ልጄ አቤሴሎም! ልጄ አቤሴሎም! በማለት አማርሮ አለቀሰ። ይህ የንጉሥ ዳዊት ለቅሶ ያለፈ የጦርነት ታርክን ያስታውሰናል። በሌላ ወገንም ትንቢትን ይነግረናል። እግዚአብሔር ለእኛ ያለንን ፍቅር የሚያሳይ ነው። እኛ ከእርሱ ስንርቅ እግዚአብሔር ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? በኃጢአታችን ምክንያት እኛ ራሳችንን ለጉዳት ስንዳርግ እግዚአብሔር ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? እግዚአብሔር አባታችን በመሆኑ አባታዊ ፍቅሩን ከእኛ አንስቶ አይወስድም። እግዚአብሔር በእኛ ላይ እጅግ እንደሚያዝን የምናውቀው ኃጢአታችንን ለመናዘዝ ስንቀርብ ነው። ምክንያቱም ለኑዛዜ መቅረብ ወይም መሄድ ማለት ወደ የትም ከመሄድ ጋር ሊወዳደር አይችልም። ምክንያቱም በሐዘን ውስጥ ወደሚገኝ አፍቃሪ አባት ዘንድ ነው የምንሄደው”።

እግዚአብሔር አባትነቱን ፈጽሞ አይክድም፣

ንጉሥ ዳዊት በልጁ ሞት ምክንያት እጅግ በማዘኑ፣ “ልጄ አቤሴሎም! ባንተ ምትክ እኔ በሞትኩ”! በማለት ያሰማው ለቅሶ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው አባታዊ ፍቅር በትንቢታዊ መንገድ የተገለጠበት መሆኑን ያስርዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ወሰን የለውም፣ ይህን ፍቅር በተጨባጭ ለመግለጽ እንደ እኛ ሰው በመሆን በመስቀል ላይ ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል። እርሱ የተሰቀለበትን መስቀል ብንመለከት ኣባታዊ ፍቅሩን ማወቅ እንችላለን። እግዚአብሔር አባትነቱን ፈጽሞ አይክድም፣ በአባታዊነቱም ፈጽሞ የሚደራደር አይደለም”።

እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ በኩል ለእኛ ሞተ፣

“እግዚአብሔር ለእኛ ያለንን ፍቅር በመስቀል ላይ በመሞት ገልጾታል” በማለት ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህንንም ያደረገው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት አሳልፎ በመስጠቱ ነው ብለዋል። ከእግዚአብሔር በምንርቅበት ጊዜ፣ በኃጢአት ውስጥ በምንወድቅበት ጊዜ፣ እርሱ ለእኛ በመጨንቅ ልጄ ምን እያደርክ ነው? ልጄ ምን እያደርግሽ ነው? በኃጢአት ምክንያት ራስህን ፣ ራስሽን ለሞት ፈጽሞ አሳልፈህ ፣ አሳልፈሽ መስጠት የለብህም፣ የለብሽም። ምክንያቱም እኔ ለእናንት በደል እና ኃጢአት ስል ሞቼአልሁና።  ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአታችን ምክንያት የሚያለቅሰው ለእርሱ ፍቅር ባለመገዛታችን ምክንያት ነው” በማለት ዛሬ ጠዋት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያቀረቡትን የቅዱሳት መጽሐፍት አስተንትኖአቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት ባቀረቡት አባታዊ አስተምህሮ፥ “በፈተና ጊዜ ፣ በኃጢያት ወቅት ፣ እራሳችንን ከእግዚአብሔር በምናርቅበት ወቅት ፣ ‘ልጄ ሆይ! ይህን ለምን ታደርጋለህ?’ የሚለውን የእግዚአብሔር ድምፅ ለመስማት እንሞክር” በማለት የዕለቱን ስብከታቸውን ደምድመዋል።         

04 February 2020, 16:12
ሁሉንም ያንብቡ >