ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “እግዚአብሔር የሚራራ ልብ እንዲኖረን ይፈልጋል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ የካቲት 10/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ ለልበ ደናዳናነት ፍቱን መድኃኒቱ የእግዚአብሔርን ጸጋ ማስታወስ ነው ብለዋል። በዕለቱ በተመደበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በሆነው፣ በማር. 8: 14-21 ላይ በማስተንተን፣ የመስዋዕተ ቅዳሴውን ጸሎት ለተካፈሉት ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን ባቀረቡት ስብከት፣ ምሕረትን ማድረግ የምንችበትን ንጹሕ እና ታማኝ ልብ የሚሰጠንን የእግዚብሔር የምሕረት ጸጋን መርሳት የለብንም ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ደቀ መዛሙርቱ ለጉዞአቸው የሚሆን በቂ እንጀራን ሳይዙ ከኢየሱስ ጋር በጀልባ መሳፈራቸውን በሚያስታውሰው በማር. 8:14-21 ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከት ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን ጭንቀት በመመልከት “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ”፣ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብስ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኖአል? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” እነርሱም “ዐሥራ ሁለት” ፣ “ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺህ ሰው በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” ባላቸው ጊዜ እነርሱም፣ “ሰባት” ማለታቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። 

ርህራሄ በሌለበት ጣዖት እና ዓለማዊ አስተሳሰብ አለ፣

በዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ያስተነተኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በደነደነው የሰዎች ልብ እና በርህራሄ በተሞላው በኢየሱስ ክርስቶስ ልብ መካከል ያለውን ልዩነት ያስረዱት ቅዱስነታቸው የእግዚአብሔር ፈቃድ ርህራሄውን መግለጽ እንደሆነ ገልጸው፣ እግዚአብሔርም “እኔ የምፈልገው ምህረትን እንጂ መስዋእትን አይደለም” ማለቱንም አስታውሰዋል። በርህራሄ ያልተሞላ ልብ በራስ ወዳድነት እና በዓለማዊ ሃሳቦች የተሞላ ነው ብለዋል። በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን የነበሩ አራት ዓለማዊ አስተሳሰብ ያላቸውን ወገኖችን ያስታወሱ ቅዱስነታቸው፣ እነርሱም ፈሪሳውያን ፣ ሰዱቃውያን ፣ ኤሳውያን እና ቀናተኞች እንደነበሩ ገልጸው እነዚህም ልባቸው የደነደነ፣ የራሳቸውን የግለኝነት አስተሳሰብ እና ዓላማ ከማራመድ በቀር ለእግዚአብሔር የርህራሄ መንገድ ምንም ቦታ ያልነበራቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ለሁሉም የልብ ጥንካሬ ኢየሱስ መድኃኒት ነው

ከልበ ደንዳናነት ለመፈወስ ፍቱን መድኃኒት አለ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም በብዙ ቦታዎች እንደተገለጸው፣ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ የጸጋ ሙላት ልብን ታማኝ እና ለርህራሄ ክፍት አድርጎ በማቆየት ከደንዳናነት ይፈውሳል ብለዋል። ልብ ሲደነድን የእግዚአብሔርን የድነት ጸጋ ማስታወስ ያቅተዋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የደነደነ ልብ በውስጡ ርህራሄ በመጥፋቱ በምትኩ ጠብን፣ ጦርነትን፣ ስግብግብነትን እና በወንድም ላይ መነሳትን ስለሚይዝ ርህራሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቅም ብለዋል። ከመልዕክት ሁሉ ታላቅ፣ እግዚአብሔር ለልጆቹ ያሳየው ርህራሄ መሆኑን ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅዱስ ወንጌልም እንደተገለጸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎችን ስቃይ እና መከራ ሲመለከት የሚያሳየው የመጀመሪያ እርዳታ ርህራሄ መሆኑን ገልጸው፣ ኢየሱስ የአባቱ ርህራሄ መገለጫ እና ለደነደነ ልብም ፍቱን መድኃኒት መሆኑን አስረድተዋል።

በርህራሄ የተሞላ ልብ ይኑረን፣

ለደነደነ ልብ የእግዚአብሔርን የጸጋ ሙላት መጠየቅ ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ዛሬ በምንኖርበት ዓለማችን ልባችን ሲደነድን በእግዚአብሔር ርህራሄ እንዲሚላ ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል ብለው፣ በፍርድ ቀናችንም የሚሰጠን ፍርድ የሚለካው በዓለማዊ አስተሳሰባችን መጠን ሳይሆን በእግዚአብሔር ርህራሄ ተመርተን ባደረግነው መልካም ተግባር መጠን ነው ብለዋል። በራበኝ ጊዜ አብልተኸኛል፣ በታሰርኩ ጊዜ ጎብኝተኸኛል፣ ባዘንኩ ጊዜ አጽናንተኸኛል፤ በርህራሄ የተሞላ ልብ እነዚህን ተግባራት እንድንፈጽም ይገፋፋናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የቀድሞ የእምነት አባቶቻችን የትሕትና መንገድ፣ የድነታችንም መንገድ ሆኖ ይቆያል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ የካቲት 10/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያቀረቡትን ስብከተ ወንጌል ከማጠቃለላቸው አስቀድመው እንደተናገሩት፣ እያንዳንዳችን ልባችን እንዲደነድን የሚያደርግ ነገር አለን ብለው፣ ይህ እንዳይሆን እግዚአብሔር በርህራሄው የደነደነ ልብ ከእኛ አስወግዶ ለእርሱ ታማኝ እና ቅን የሆነ ልብ እንዲሰጠን እንጸልይ በማለት ስብከታቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 February 2020, 16:29
ሁሉንም ያንብቡ >