ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት  (@Vatican Media)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ወደ ዓለማዊ መንፈስ እንዳንገባ እንዲረዳን የእግዚአብሔርን ጸጋ እንጠይቅ” አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 05/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ቄሳውስት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙት ስብከት በእለቱ በተነበቡት ምንባባት ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደረጉት ስብከት እንደ ገለጹት መንፈሳችን እንዲያንቀላፋ ከሚያደርገው ዓለማዊ ማደንዘዣ መጠበቅ ይኖርብናል ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን ቀስ በቀስ ጌታን እየረሳን በምንመጣበት ወቅት “ከሌሎች አማልክት” ጋር ማለትም “ከገንዘብ፣ ከትዕቢት እና ከከንቱነት ጋር ያለንን ወዳጅነት” ወደ ማጠናከር እንሻገራለን ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት ቀስ በቀስ ከእግዚኣብሔር በመራቅ ሳናስበው እየተንሸራተትን ዓለማዊ ወደ ሆኑ ነገሮች ውስጥ እንገባለን በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እነዚህም የኃጢአት ሁሉ ምንጭ የሆኑት ገንዘብን፣ ከንቱነት እና ትዕቢት እንደ ሆኑ የገለጹ ሲሆን እነዚህም ነገሮች ልባችን ከእግዚኣብሔር እንዲርቅ ያደርጉታል ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት “ሰመመን ውስጥ እንድንገባ የሚያደርገን ማደንዘዣ” የሚለውን ጭብጥ ባብራሩበት ወቅት እንደ ገለጹት በእለቱ በቀዳሚነት 1ኛው መጽሐፈ ነገስት 11፡4-13 ላይ ተወስዶ በተነበበውና ንጉስ “ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ እንደ ተገዛ ሁሉ፣ በፍጹም ልቡ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር አልተገዛም። ሰሎሞንም የሲዶናውያንን ሴት አምላክ አስታሮትን፣ አስጸያፊውን የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን ተከተለ” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተንተርሰው እንደ ገለጹት ንጉስ ሰለሞን ባረጀ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡ ከእግዚኣብሔር እንዲርቅ ማድረጋቸውን ገልጸው ሰለሞን ለእግዚአብሔር የገባውን ቃል እስከ መጨረሻው ሕይወቱ ድረስ በታማኝነት አልጠበቀውም ብለዋል።  

በእርግጥ እርሱ በሸመገለ ጊዜ ሴቶቹ ሌሎች አማልክትን እንዲከተል “ልቡ እንዲቀየር” አድርገው ነበር፣  እርሱ ከመጀመሪያ “ከወጣትነት እድሜው” አንስቶ መልካም የሆነ ወጣት ልጅ” ነበር፤ ጌታን ጥበብን ብቻ የጠየቀ እና እግዚአብሔር ጥበበኛ አድርጎት ፈጥሮት ነበር፣ የሕግ አዋቂዎች እና አፍሪካዊ የሆነቺው ንግስተ ሳባ ሳትቀር የእርሱን ጥበብ ለማየት ስጦታ ይዘው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር በማለት ስለሰለሞን ታላቅነት ያብራሩት ቅዱስነታቸው ይህቺ ሴት ግን ለሰለሞን ያቀረበችለት ጥያቄ የፍልስፍና ይዘት የነበረው ጥያቄ በመሆኑ የተነሳ ምላሹ እጅግ ከብዶት ነበር” ብለዋል።

ዘገምተኛ ክህደት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት በእዚያን ሰለሞን በነበረበት ወቅት ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት ይቻል እንደ ነበረ ያስታወሱ ሲሆን የሰለሞን ድከመት ከአንድ በላይ ሚስት ማግባቱ ብቻ ሳይሆን የሌላ አማልክት አማኝ የሆኑ ሴቶችን ማግባቱ ጭምር ነበር ብለዋል። ሰለሞንም በዚያ “ወጥመድ” ውስጥ በመውደቁ የተነሳ የሌላ አማልክት አማኝ የሆነቺው ሴት የአስታሮትን እና የአሞናውያንን አምላክ እንዲያመልክ እንዳሳመነችው ገልጸዋል። ለአማልክቶቻቸውም መሥዋዕት ለሚያቀርቡ የባዕድ አገር ሴቶች ሁሉ እንዲሁ አደረገ፣ ታዛዢም ሆነ፣ በአንድ ቃል “ሁሉንም ነገር ፈቀደ፣ ብቸኛውን አምላክ ማምለኩን አቆመ” ለሴቶቹ ከነበረው ከፍተኛ ፍቅር የተነሳ ልቡ ስለተዳከመ “አረማዊነት ወደ ህይወቱ ገባ” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ከእዚያም በኋላ ጥበብን እንዲሰጠው እግዚኣብሔርን አጥብቆ የለመነው እና የጠየቀው ያ ብልህ የነበረው ወጣት ልጅ በመጨረሻም በሴት ልጅ ፍቅር በመያዙ የተነሳ ከጌታ ተለየ ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት ሰለሞን የፈጸመው ክህደት እንዲያው  “በአንድ ሌሊት የተፈጸመ ክህደት አልነበረም፣ ዘገምተኛ የሆነ ሂደት የተከተለ ክህደት ነበር” በማለት አብራርተዋል። የንጉስ ሰለሞን አባት የነበረው ንጉስ ዳዊት እንኳን ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ታላላቅ የሚባሉ ኋጢአቶችን ሰርቶ ነበር፣ ነገር ግን ወዲያው ተጸጽቶ ይቅርታን ጠየቀ እስከ መጨረሻው ለሚጠብቀው ጌታ ታማኝ ነበር በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ንጉስ ዳዊት ለሰራው ኃጢአት እና ልጁ አቤሴሎም በመሞቱ የተነሳ አለቀሰ በመጀመሪያ ከእርሱ ሸሸ፣ ሰዎች ይሰድቡት ነበር ኃጢአቱን በማሰብ ራሱን ዝቅ አደረገ፣ እርሱ ቅዱስ ነበር፣ ሰልሞን ግን ቅዱስ አልነበረም ብለዋል። ጌታ ብዙ ስጦታዎችን ሰጠው ነገር ግን እርሱ ልቡ በመድከሙ የተነሳ ሁሉንም ነገር ከንቱ አድረገው፣ አባክነውም ብለዋል።

ከክህደት ሊያስቆመን የሚችለው የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ነው

ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት ቀስ በቀስ ተንሸራተን በኃጢአት ውስጥ ገብተን ከእርሱ እንዳንለይ የሚያደርገን የእግዚኣብሔር ፍቅር ነው ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን በእምነታችን እስከ መጨረሻው ጸንተን እንድንኖር እንዲረዳን የእግዚኣብሔርን እርዳታ መጠየቅ ይኖርብናል ብለዋል። ይህንን ሐሳባቸውን በሚገባ ለማስረዳት በማሰብ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . . .

ይህን የሰለሞን ኃጢአት እናስብ፣ ጥበበኛ የነበረው ሰሎሞን፣ በጌታ የተባረከ እና የአባቱን የዳዊትን ርስት ሁሉ የወረሰው ሰለሞን እንዴት እንደ ወደቀ እንመልከት፣ ዓለማዊ የሆነ መንፈስ እንዲጠናወተው ልቡን በወጋው ማደንዘዣ የተነሳ ቀስ በቀስ ወደ ጣዖት አምላኪነት እንዴት እንደ ገባ፣ ከእግዚኣብሔር መንግሥት ወደ ዓለማዊ መንግስት እንዴት እንደ ተሻገረ እናስብ። ልባችን መዳከም እና መንሸራተት ሲጀምር እኛ ጸንተን መቆም እንችል ዘንድ እንዲረዳን የጌታን ጸጋ እንለምን። ወደ እሱ ከጸለይን የእሱን ሞገስ እና የእርሱ ፍቅር የሰጠናል።

13 February 2020, 15:05
ሁሉንም ያንብቡ >