ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (@VaticanMedia)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ክርስትናችን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ነጻ ስጦታ ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጥር12/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን በተገኙበት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት ክርስትናችን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ነጻ ስጦታ መሆኑን አስረድተው፣ ጥሪውን ተቀብለን ስጦታውንም በታማኝነት መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ክርስትና፣ ክህነት፣ ወይም ጵጵስና የሚሸጥ ወይም የሚገዛ ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሚሰጠን ነጻ ስጦታ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ቅድስናም ቢሆን ከእግዚአብሔር የተቀበልናቸውን ነጻ ስጦታዎች በታማኝነት በመጠበቅ የሚገኝ እንጂ እንዲሁ የሚገኝ አይደለም ብለዋል። ዛሬ በተነበቡት የመጽሕፍ ቅዱስ ንባባት፣ በመዝ. ዳዊት ምዕ. 88, እና በ1ኛ ሳሙ. 16፡1-13 ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በምዕመናን የምስጋና መልስ መዝሙር ላይ እግዚአብሔር ሳኦልን ባለመታዘዙ ምክንያት ማዘኑን፣ ዳዊትን ግን የእስራኤል ንጉሥ አድርጎት መምረጡን አስታውሰዋል። የመጀመሪያ ንባብ በሆነው፣ በ1ኛ ሳሙ. 16፡1-13 ላይ፣

እግዚአብሔር ሳሙኤልን፣ ወደ ቤተ ልሔሙ ሰው ወደ እሴይ ይሄድ ዘንድ፣ ከልጆች መካከል እርሱ እግዚአብሔር የመረጠውን አንዱን እንዲቀባው በማለት ማዘዙን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ እግዚአብሔር በዘመናችንም ከመካከላችን ካህናትን እና ጳጳሳትን መርጦ እንደሚቀባቸው አስታውሰው፣ ክርስቲያኖችም ምስጢረ ጥምቀትን ሲቀበሉ በዘይት የሚቀቡ መሆናቸውን አስታውሰዋል። እግዚአብሔር ሳሙኤልን፣ የሰዎችን ውጫዊ ገጽታ ብቻ በመመልከት ዘይት ከመቀባት እንዲቆጠብ መምከሩን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የሰው ልጅ የሚመለከተው ውጫዊው ገጽታ ዋጋ እንደሌለው፣ እግዚአብሔር ግን ልብን የሚመለከት መሆኑን አስረድተዋል።

የዳዊት ወንድሞች የእስራኤልን መንግሥት ለመጠበቅ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ይዋጉ እንደነበር ያስታወሱት ቅዱስነታቸው እግዚአብሔር ግን ከመካከላቸው የመጨረሻ የሆነው እና ፍልስጥኤማውያንን ለመዋጋት እንኳ ብቁ ያልሆነ፣ ነገር ግን ወደሚዋጉ ወንድሞቹ ዘንድ እየሄደ ይመለከታቸው የነበረ ዳዊትን እንደመረጠ፣ ሳሙኤል ዳዊትን እንዲቀባው በማለት ማዘዙን እና ከዚያን ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ማረፉን አስታውሰዋል።

የእግዚአብሔር ነጻ ምርጫ፣

ከወንድሞቹ መካከል ታናሽ፣ በአቅምም ውስን፣ ምንም ዓይነት ሃላፊነት፣ የውጊያ ልምድም የሌለው፣ የጸሎት ሰው ያልነበረውን ዳዊት በመምረጡ እግዚአብሔር በምርጫው እስከዚህ ድረስ ነጻ መሆኑን ያስገነዝበናል ብለዋል።

“እግዚአብሔር ሲመርጥ ነጻነቱን እንድንመለከት ይፈልጋል፤ ስለራሳችን ብናስብ እንኳ እግዚአብሔር እንዴት ነው የመረጠን? ከክርስቲያን ቤተሰብ ስለሆንን ይመስላችኋል? ወይም በክርስትና ባሕል ውስጥ ስላደግን ይመስላችኋል? አይደለም! በርካታ ክርስቲያን ቤተሰቦች፣ በክርስትና ባሕል ያደጉት እግዚአብሔርን ወደ ጎን ብለውታል፣ ከእግዚአብሔር ርቀዋል። ታዲያ እኛስ እንዴት በእግዚአብሔር ልንመረጥ ቻልን? እግዚአብሔር የመረጠን በነጻ ነው፤ ክርስቲያን የሆንነው ገንዘብ ከፍለን አይደለም፣ ካህናት ወይም ጳጳሳት የአገልግሎት ማዕረግ የተቀበሉት ከፍለው አይደለም። ራሳቸውን በግድ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ካላስገባን ብለው የሚታገሉ አይጠፉም። እነዚህ ታዲያ ክርስቲያኖች አይደሉም። ጥምቀት በንጻ የሚሰጥ ጸጋ ነው፣ ክርስትና በነጻ የሚገኝ እንጂ በገንዘብ የሚገዛ አይደለም። ክህነትም ይሁን የጵጵስና ማዕረግ በነጻ የሚሰጥ ጸጋ ነው። የእግዚአብሔር ስጦታ በነጻ የሚሰጥ እንጂ በገንዘብ የምንገዛው አይደለም”።                               

የእግዚአብሔርን ስጦታ በጥንቃቄ መያዝ ይኖርብናል፣

ታዲያ በነጻ የተቀበልነውን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ምን ማድረግ ይኖርብናል በማለት ጥያቄያቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ክርስቲያናዊ ቅድስና የእግዚአብሔር ስጦታ በመሆኑ በጥንቃቄ ልንይዘው ይገባል፣ በስጦታው አማካይነት እግዚአብሔር በግልጽ እንዲታይ ማድረግ እንጂ በራሳችን ምንም ማድረግ እንደማንችል ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

“በዕለታዊ ሕይወታችን፣ ተቀጥረን በምንሰራበት መሥሪያ ቤት፣ ወደ ከፍተኛ የሕዝብ ወይም የመንግሥት የሃላፊነት ቦታ ለመድረስ ጥያቄን እናቀርባለን እንጂ በስጦታ መልክ እንዲሰጠን በማለት አንጠይቅም። ክርስቲያን መሆን፣ የክህነት ወይም የጵጵስና ማዕረግ መቀበል ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ነጻ ስጦታ ነው። ያለ አድልዎ ለእያንዳንዳችን ሊኖር የሚገባ ትህትናም በዚህ መልክ ሊታይ ይገባል። እኛም ክርስቲያን ያደረገንን ፣ ካህን ያደረገንን ፣ ጳጳስ ያደረገንን የእግዚአብሔር ስጦታ፣ ትህትናን በጥንቃቄ መያዝ ይኖርብናል። ይህም ቅድስናችን ነው፣ ሌላው አይጠቅመንም። ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ታላቅ ስጦታ የቱ ነው? ቢባል እርሱ በመረጠን ጊዜ የሰጠን፣ ንጹህ የጸጋ ስጦታ መንፈስ ቅዱስ ነው”።  

የእግዚአብሔርን ሕዝብ መርሳት ስጦታውን መካድ ማለት ነው፣

እግዚአብሔር ዳዊትን ከተረሳ እና አቅመ ደካማ ከሆነ ሕዝብ መካከል መምረጡን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣

“እኛ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ሕዝብ፣ የማያምኑትንም ቢሆን የምንዘነጋ ከሆነ፣ እኛ ካህናት እና ጳጳሳት ራሳችንን ከፍ በማድረግ መንጋዎቻችንን፣ ሕዝባችንን የምንረሳ ከሆነ የእግዚአብሔርን ስጦታ ክደናል ማለት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ሳይሆን በራሳችን ሃይል ተመክተናል ማለት ነው። ክርስትና ወይም የእግዚአብሔርን ስጦታ በጥንቃቄ መያዝ ማለት ይህ አይደለም”።

ለተሰጠን ታላቅ እና ውብ ስጦታ እግዚአብሔርን እንድናመሰግን፣ ስጦታውንም በጥንቃቄ እና በታማኝነት መያዝ እንድንችል ጸጋውን እንዲሰጠን፣ ዳዊትንም እያሰብን ጸሎታችንን ወደ እግዚአብሔር እናቅርብ በማለት ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያቀረቡትን የቅዱሳት መጽሐፍት አስተንትኖአቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
21 January 2020, 16:37
ሁሉንም ያንብቡ >