ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “በምንሰፍረው መስፈሪያ ለእኛም ይሰፈርልናል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጥር 21/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን በተገኙበት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ የሕይወታችን አካሄድ እና ለሰው ልጆች በሙሉ ያለን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ክርስቲያናዊነትን የተላበሰ፣ ቸርነት እና እውነተኛ ፍቅር የሚታይበት ሊሆን ይገባል ብለዋል። ምክንያቱም በሌላው ላይ በምንፈርደው ፍርድ መጠን በዚያው ልክ በሕይወት ዘመናችን ማብቂያ ላይ ይፈረድብናል በማለት ለዕለቱ በተመደበው፣ በማር. 4: 21-25 በተጻፈው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ለተካፈሉት በሙሉ ስብከታቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከማር. 4: 21-25 ተወስዶ በተነበበው በዛሬው የቅዱስ ወንጌል ንባብ ውስጥ፣ በቁ. 24 ላይ “በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ለእናንተም ይሰፈርላችኋል” በሚለው ጥቅስ ላይ ያስተነተኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሁላችንም በሕይወት ዘመናችን ውስጥ የምናደርጋቸውን ነገሮች ግንዛቤ ውስጥ እናስገባለን። በተለይም ወደ ሕይወት ፍጻሜ ስንደርስ አንድ በአንድ እናያቸዋለን። በመጨረሻው ዘመን የሚሰጠን ፍርድ እንዴት እንደሚሆን ወይም ምን እንደሚመስል የተናገረው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በማቴዎስ ወንጌል በምዕ. 25 ላይ የተገለጸው የብጽዕና መንገድ በሕይወት ዘመናችን ምን ማድረግ እንዳለብን፣ እንዴትስ ማድረግ እንዳለብን፣ በምን ዓይነት መንገድ መኖር እንዳለብን ሁሉ፣ በመጨረሻው ዘመን የሚሰጠን ፍርድ በዚያው መጠን እንደሚሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መናገሩን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

“በየትኛው መለኪያ ነው ሰዎችን የምለካው? በየትኛው መለኪያ ነው ራሴን የምለካው? ቸርነት እና እውነተኛ የእግዚአብሔር ፍቅር በሚታይበት መለኪያ ነው ወይስ ከዚህ ባነሰ መለኪያ? የሚፈረድብኝም በዚያው መጠን ነው እንጂ በሌላ አይደለም። ምርኩዜን የሰቀልኩበት ከፍታ ከፍ ብሎ ነው ወይስ ዝቅ ብሎ ነው? በዚህ መልክ ማየት ይኖርብናል። ይህን በምናደርግበት ጊዜ በሕይወት ዘመናችን ያደረግናቸውን መልካም ነገሮችን ብቻ መመልከት ወይም መቁጠር የለብንም፤ ወይም መልካም ያልሆኑ ሥራዎቻችንን ብቻ ማሰብ የለብንም። ነገር ግን ጠቅላላ የሕይወት አካሄዳችን ምን እንደሚመስል ዞር ብለን ማሰብ ያስፈልጋል”።          

የሕይወት ሞዴላችን እግዚአብሔር ነው፣

እያንዳንዳችን የራሳችን የሕይወት አካሄድ የምንለካበት ሚዛን አለን ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እግዚአብሔርም የሚጠቀመው ሚዛን እኛ ከምንጠቀመው ሚዛን ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ሚዛኑን ለራስ በሚያዳላ መንገድ የምንጠቀም ከሆነ ይህ ከእግዚአብሔር የተሰወረ እንደማይሆን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ራስን ከሌሎች ከፍ በማድረግ፣ ምሕረት የለሽ በሆነ መንገድ ሌሎችን የሚረግጥ እና የሚጨቁን ካለ፣ እርሱም ያለ ምሕረት በዚያው መጠን የሥራውን ዋጋ ያገኛል ብለው፣ በመሆኑም ክርስቲያን ሊከተለው የሚገባ የሕይወት ምሳሌ የቱ መሆን እንዳለበት እንዲህ በማለት አስረድተዋል፥

“ክርስቲያን እንደመሆኔ፣ ክርስትናዬን የምመዝንበት ሚዛን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚፈልገው የክርስትና ሕይወት የቱ ነው ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል። ከክርስትናችን መለኪያ መንገዶች መካከል አንዱ ራስን ማዋረድ ነው ፣ ውርደትን የመቋቋም ችሎታ ነው። ራስን ማዋረድ የማይችል ክርስቲያን፣ ውርደትን ተሸክሞ መጓዝ የማይችል ክርስቲያን አንድ የሚጎድል ነገር አለው። ይህ ክርስቲያን አስመሳይ እና የራሱን ፍላጎት ለማሟላት የተነሳ ክርስቲያን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚለው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እስከሚሞት ድረስ ራሱን አዋረደ። እርሱ አምላክ ቢሆንም ራሱን ዝቅ ማድረግን መረጠ። ይህን በማድረጉ የክርስትና ሕይወት ሞዴላችን ኢየሱስ ክርቶስ ነው”።

ትክክለኛ ማንነታችን የቱ ነው?

በማንነታችን ዓለማዊ ከሆንን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወታችን ምሳሌ ማድረግ አንችልም። ነገር ግን ይህ ሰው ዓለማዊ ነው፣ ይህ ሰው ኃጢአተኛ ነው፣ ይህ ሰው ይህን መንገድ ይከተላል በማለት የሰዎችን ውጫዊ ገጽታ ብቻ በመመልከት አንድ ሰው ዓለማዊ ወይም ክርስቲያን ነው ብለን የምንፈርጅበት ስልጣን የለንም በማለት ዛሬ ጠዋት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ስብከታቸውን ያሰሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚከተለውን በማለት ስብከታቸውን ደምድመዋል፥

“በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ለእናንተም ይሰፈርላችኋል”። መስፈሪያችን ክርስቲያናዊ ከሆነ፣ ኢየሱስን የተከተለ ከሆነ፣ የእርሱን መንገድ የሚጓዝ ከሆነ፣ የሚሰፈርልን መስፈሪያም ብዙ ርህራሄ እና ብዙ ምሕረት ያለበት መስፈሪያ ይሆናል። ነገር ግን መስፈሪያችን ዓለማዊ መንገድን የተከተለ፣ ክርስትናዊ እምነትን ለስም ብቻ የምንጠቀመው ከሆነ በዚያው መጠን ይሰፈርልናል። ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሲል የተጓዘበትን የውርደት መንገድ በማስታወስ፣ በዕለታዊ ሕይወታችን የሚያጋጥመንን መስቀል እና ውርደት መሸከም የምንችልበትን ጸጋ እንዲሰጠን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቅ” ብለዋል

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
30 January 2020, 16:33
ሁሉንም ያንብቡ >