ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት   (ANSA)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ዓለማዊ መንፈስ በኃጢአታችን የተነሳ ቀስ በቀስ ተንሸራተን የምንገባበት ጉዳይ ነው!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት በጥር 22/2012 ዓ.ም እርሳቸው የሚያሳርጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ ለመከታተል ለተገኙ ቄሳውስት፣ ደናግላን እና ምዕመናን ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት በዘመናችን እየተፈጸሙ የሚገኙት የክፋት ድርጊቶች እየተፈጸሙ የሚገኙት ኃጢአትን አቅልሎ ከመመልከት እና የኃጢያተኛነት ስሜት እየጠፋ በመሂዱ የተነሳ እንደ ሆነ የገለጹ ሲሆን በወቅቱ ከ2ኛው ሳሙሄል 11፡1-4 ላይ ተወስዶ በተነበበው የመጀመሪያው ምንባብ ላይ ትኩረቱን ባደረገው ስብከታቸው ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት እንደ ዳዊት ያሉ ቅዱሳን እንኳን ሳይቀር በእዚህ ዓለም ፈተና ተወስደው እንደ ነበረ ገልጸዋል። ይህ ሁላችንንም የሚያጋጥመን ፈተና እንደ ሆነ በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ከዓለም መንፈስ መጠበቅ አለብን የምንለው በእዚሁ ምክንያት ነው ብለዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በጣም ከባድ ኃጢአት በምንሰራበት ወቅት እንኳን ሳይቀር ልባችን እንዲያው ሳይሸበር መደበኛ ተግባሩን የሚያከናውን ከሆነ፣ ሰላማዊ ሕይወት እየመራን ከሆነ፣ እየተከናወነ ያለውን ክፋ ነገር የማየት ችሎታ የሌለን ከሆነ ልባችንን የሰለበ ዓለማዊ መንፈስ ውስጥ እንገኛለን ማለት ነው ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያስሙት ስብከት ቀድም ሲል እንደ ጠቀስነው ከሁለተኛው መጽሐፈ ሳሙሄል ላይ ተወስዶ የተነበበ እንደ ሆነ መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን “ቅዱሱ ንጉሥ ዳዊት” ምቹ በሆነው በእዚህ ምድር ሕይወት በመሰድ እግዚኣብሔር ሕዝቡን እንዲያገለግል እንደ መረጠው መዘንጋቱን ቅዱስነታቸው በስብከታቸው አስታውሰዋል። ዳዊት የነበረው ዓይነት ሕይወት የሚኖሩ ሰዎች ዛሬም ቢሆን በእኛ ዘመን እንደ ሚገኙ የገለጹት ቅዱስነታቸው ጥሩ የሚመስሉ  “እሁድ እሁድ ወደ ቤተ-ክርስቲያን በመሄድ መስዋዕተ ቅዳሴ የሚያስቀድሱ፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ፣ ነገር ግን የሚሰሩትን ኃጢያት ልብ የማይሉ ብዙ ክርስቲያኖች እንደ ሚገኙ “ በአጽኖት ገልጸዋል።

የዓለም መንፈስ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ በተነበበው የመጀርያ ምንባብ ላይ ተንተርሰው ዳዊት በሰራው ኃጢአት ዙሪያ ላይ አንዴ ቆም ብለው እንደ ገለጹት የበርሳቢህ ሚስት የነበረችውን ሁሪያን ዳዊት ካስረገዛት በኋላ፣ ይህ ድርጊቱ እንዳይታወቅበት በማሰብ ባሏን በርሳብህን እንዳስገደለው ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ዳዊት የፈጸመው የአመንዝራ ተግባሩ እንዳይታወቅበት ሁኔታዎችን ለማስተካከል በማሰብ ግዲያ መፈጸም እንደ መረጠ ገልጸዋል። ይህንን ተግባር ዳዊት ከፈጸመ በኋላ እንኳን ሳይቀር ዳዊት ምንም እንዳልተፈጠረ በማስመሰል እለታዊ እና መደበኛ የሆነውን የአኗኗር ዘይቤውን መኖር እንደ ቀጠለ የገለጹት ቅዱስነታቸው በጣም ተረጋግቶ ልቡ ምንም ዓይነት ስህተት እንዳልሰራ አምኖ ተቀብሎ የተረጋጋ ሕይወት ይኖር እንደ ነበረ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ይህንን ሐሳባቸውን በሚገባ ለማስረጽ በማሰብ የሚከተለውን ብለዋል . . .

ነገር ግን ቅዱስ የነበረ፣ ብዙ መልካም ነገሮችን ያከናወነ፣ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የነበረ፣ ታላቁ ዳዊት እንዴት እንዲህ ማድረግ ቻለ? ይህ በአንድ ሌሊት የተፈጸመ ጉዳይ አይደለም። ታላቁ ዳዊት በቀስታ እየተንሸራተተ በእዚህ ጉዳይ ውስጥ ገብቱዋል። በጊዜው ኃጢያቶችን እንሰራለን፣ የቁጣ ኃጢአት፣ ልቆጣጠረው የማንችለው ስድብ እነዚህ ነገሮች አንድ ሰው ወደ ዓለማዊ መንፈስ በቀስታ እየተንሸራተተ እንዲገባ የሚያደርጉ ኃጢአቶች ናቸው። እነዚህን ነገሮች ልክ እንደ መደበኛ ነገር አድርግህ እንድትቆጥር የሚያድርግህ ደግሞ የዓለም መንፈስ ነው።

በኃጢአት መንሸራተት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት ኃጢአት ለሰው ልጆች ምቾትን በመፍጠር የሰውን ልጅ ቀስ ብሎ እንዴት እንደሚወስድ የገለጹ ሲሆን በመቀጠል እኛ ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን - ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ የጊዜውን ኃጢአት እንሠራለን፣ እንናደዳለን፣ እንሳደባለን፣ ከእዚያም በፈጸምናቸው ተግባራት እናዝናለን እንጸጸታለን ብለዋል። አንዳንዴ እራሳችንን ወደ ጤናማ ሁኔታ ውስጥ ያሻገርን ስለሚመስለን የተለመደ ኃጢአት እንሰራለን። ለምሳሌ ያህል “ለቤት ሰራተኞቻችን ተገቢውን ክፍያ አንከፍልም፣ ገጠራማ አከባቢ ለሚሰሩ ሰራተኞች የምንክፍለው ክፍያ በጣም አነስተኛ ነው” እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ ተግባራትን ልማዳዊ በሆነ መልኩ እናከናውናለን ብለዋል።

ይህንን ዓይነት ተግባር እያከናወንን የምንሰራቸው ስህተቶችን በቅጡ እንኳን ሳንረዳ ራሳችንን እንደ አንድ መልካም ክርስቲያን አድርገን በመቁጠር በየለተ ሰንበቱ መስዋዕተ ቅዳሴ ለማስቀደስ ወደ ቤተ-ክርስቲያን እንሮጣለን በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህ ደግሞ በጣም አደገኛ የሆነ ባሕሪ ነው፣ ኃጢአት እየሰራን ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ሕሊናችንን አሳምነን መኖር ተገቢ የሆነ ድርጊ ስላልሆነ ራሳችንን መፈተሽ ይኖርብናል ብለዋል።

ከእዚህ ዓይነቱ ስህተቶቻችን ለመላቀቅ እና የተሻለ ክርስቲያኖች ለመሆን ከፈለግን ልክ ንጉሥ ዳዊትን ነቢዩ ናታን እንዳነቃው ሁሉ እኛንም ከተኛንበት በኃጢአት የተሞላ ሕይወት ውስጥ ነቅተን መውጣት እንችል ዘንድ የሚረዱን ሰዎችን መፈለግ እንደ ሚገባን የገለጹት ቅዱስነታቸው ከኃጢአታችን ነጽተን፣ ንጹህ የሆነ ሕሊና ይዘን እግዚኣብሔርን እና ባልንጀሮቻችንን የሚያስደስት ሕይወት እንኖር ዘንድ እንዲረዳን እግዚኣብሔርን ልንማጽን ይገባል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

31 January 2020, 14:51
ሁሉንም ያንብቡ >