ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “እግዚአብሔር የችግረኞችን ጸሎት ለመስማት ዝግጁ ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጥር 7/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን በተገኙበት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከታቸው ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የምናቀርበው ጸሎት አጭር ቢሆንም እንኳ እግዚአብሔር ከማዳመጥ ወደ ኋላ የማይል መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ከጎናችን መሆኑን ገልጸው፣ ለእኛ ካለን ርህራሄ እና ፍቅር የተነሳ ችግሮቻችንን፣ ኃጢአቶቻችንን እና ውስጣዊ ሕመማችንን ቀድሞ አውቆ ምሕረቱን እና ፈውሱል ይልክልናል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከማርቆስ ወንጌል ምዕ. 1:40-45 ተወስዶ በተነበበው በዛሬው የቅዱስ ወንጌል ንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ የወንጌል ክፍል ለምጻሙ ሰው በኢየሱስ እግር ሥር ተንበርክኮ “ብትፈቅድስ ልታድነኝ ትችላለህ” ማለቱን አስታውሰው፣ የለምጻሙ ሰው ጸሎት ይህን ያህል አጭር ቢሆንም በእምነት ከልብ የመነጨ በመሆኑ የኢየሱስ ክርስቶስ ርህራሄ የተገለጠበት ጸሎት ነበር ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል፣ ከእኛ ጋር ተሰቃይቷል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተሰቃየውም ስቃያችንን እርሱ በመቀበሉ ነው ብለዋል። በአባቱ ፍቅር በመታገዝ ለእኛ ሲል በመሰቃየቱ፣ ለምንሰቃይ በሙሉ ዕረፍትን እና ፈውስን አስገኝቶልናል ብለዋል።

የለምጻሙን ሰው መፈውስ በሚገልጽ የማርቆስ ወንጌል ታሪክ ላይ ያስተነተኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ብትፈቅድስ ልታድነኝ ትችላለህ” የሚለው የለምጻሙ ሰው ጸሎት የእግዚአብሔርን ትኩረት የሳበ፣ ጠንካራ እምነት የሚገኝበት ጸሎት ነበር ብለው “ኢየሱስ ሊያደርገው ይችላል!” በሚል እምነት ራሱን ወደ ኢየሱስ ያቀረበበት ጸሎት ነበር ብለዋል። በለምጽ ሕመም የሚሰቃይ ሰው ጸሎቱን ወደ ኢየሱስ ሊያቀርብ የቻለው የኢየሱስን ርህራሄ ስለተመለከተ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በዚህ የወንጌል ክፍል እንደተገለጠው ለምጻሙ ሰው የተገነዘበው የኢየሱስ ክርስቶስን አዛኝነት ሳይሆን ርህራሄውን እንደሆነ ገልጸው፣ በሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፥ በመበለቷ ታሪክ፣ በደጉ ሳምራዊ ታሪክ እና በአባካኙ ልጅ ታሪክም ርህራሄ መታየቱን አስታውሰዋል።

“ርህራሄ ከልብ የሚመነጭ፣ መልካም ነገርን እንድናደርግ የሚገፋፋን ውስጣዊ ስሜት ነው። ርህራሄ ከሚሰቃዩት ጋር እንድንሰቃይ፣ ስቃያቸውን እኛ ተቀብለን እነርሱ ነጻ እንዲወጡ የምንደርግበት እና የምናድንበት መንገድ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ተልዕኮም ይህ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሕግን በመስበክ፣ የሕዝቡን ችግሮች ከማየት ወደ ኋላ አላለም። ኢየሱስ የመጣው ርህራሄን ይዞ ነው። ይህም ማለት ከምንሰቃይ ጋር ለመሰቃየት፣ ስቃያችንን እርሱ ተቀብሎ እረፍትን እና ሕይወትን ሊሰጠን መጥቷል”።                    

ኢየሱስ ዘወትር ከጎናች ይገኛል፣

ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ከጎናችን መሆኑን መዘንጋት የለብንም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እርሱ በርህራሄው ብዛት፣ በሐዘናችንም ሆነ በማንኛውም ዓይነት ችግራችን መካከል ይገኛል ብለው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን ለብሶ በመካከላችን የተገኘው ዘለዓለማዊ ቃሉን ብቻ ተናግሮ ወደ አባቱ ዘንድ ሊመለስ ወይም እጁን ታጥቦ ሊቀመጥ አይደለም ብለው፣ እርሱ የመጣው ዘወትር ከእኛ ጋር ሊሆን እና ከጎናችንም ሊገኝ ነው ብለዋል። በመሆኑም የኢየሱስ ክርስቶስ ርህራሄው ወደ ጸሎት ሊቀየር የሚችል ተግባር መሆኑን እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል፥

“ጌታ ሆይ ልታድነኝ ትችላለህ! ጌታ ሆይ አንተ ምሕረትህን ልታደርግልኝ ትችላለህ! ልትረዳኝም ትችላለህ። ኃጢአተኛ ነኝና ማረኝ፤ ርህርሄንም ግልጽልኝ በማለት ጸሎታችንን ወደ እርሱ ማቅረብ እንችላለን። እነዚህን አጫጭር ጸሎቶች ዘወትር ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ማቅረብ እንችላለን። ኃጢአተኛ ነኝ እና ማረኝ በማለት ጸሎታችንን ከልብ ማቅረብ እንችላለን”።         

ተዓምር የሚታይበት ጸሎት፣

በማርቆስ ወንጌል ምዕ. 1 ላይ እንደተገለጸው፣ ለምጻሙ ሰው ተዓምርን ያየበት ጸሎት ወደ ኢየሱስ ዘንድ በማቅረብ ከነበረበት ሕመም ተፈወሰ። ኃጢአታችንን ሳይቆጥርብን በርህርሄው ፍቅሩን ለገለጠልን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ማቅረብ አለብን።

“እርሱ አልተጸየፈንም፤ እርሱ ወደ እኛ የመጣው ኃጢአተኞች መሆናችንን በማወቁ ነው። ኃጢአታችን በበዛ ቁጥር ምሕረቱ ከዚያ በላይ ነው። እርሱ ወደ ዓለም የመጣው እኔን ኃጢአተኛውን ይቅር ለማለት፣ ለሰው ልጆች በሙሉ ምሕረቱን ሊሰጥ ነው። በመሆኑም ወደ እርሱ የምናቀርበው ጸሎት አጭር ቢሆንም በእርሱ በመታመን፣ አለኝታነቱን በማመን፣ ርህራሄውን በመመልከት የዘወትር ችግሮቻችንን፣ ኃጢአታችንን፣ ሕመማችንን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በእምነት ማቅረብ ያስፈልጋል” በማለት ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያቀረቡትን የዕለቱን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖአቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
16 January 2020, 17:42
ሁሉንም ያንብቡ >