ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (ANSA)

“መሐሪ፣ አጽናኝ እና ርህሩህ አምላክ ስላለን መጨነቅ የለብንም”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኅዳር 30/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማሳረጋቸው ታውቋል። በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ወቅት በቀረቡት የእለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። የመስዋዕተ ቅዳሴውን ጸሎት ለተካፈሉት ቄሳውስት፣ ደናግል እና ምዕመናን ባሰሙት ስብከታቸው እግዚአብሔር መልካም እረኛ በመሆኑ ምሕረትን ፈልገው ወደ እርሱ የሚቀርቡትን በመቀበል የእርቅ ጸጋ ወደሚገኝበት መንገድ ይመራቸዋል ብለዋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እግዚአብሔር ሕዝቡን ይመራዋል፣ ያጽናናዋል፣ ያጠፋም ቢኖር በርኅራሄ ልብ ይቀጣዋል ብለዋል። በዕለቱ ከትንቢተ ኢሳያይስ 40:1-11 ተውስዶ በተነበበው የመጀመሪያ ንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚቀጣውም በጭካኔ ሳይሆን በአባታዊ ርህራሄ፣ ግልገሎችን በደረቱ ተሸክሞ እንደሚሄድ መልካም የበግ እረኛ ነው ብለዋል። እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዴት ያጽናናል፣ እንዴትስ ያስተካክላል ለሚለው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት እንዳስረዱት፣ በትንቢተ ኢሳ. 40:1 ላይ ተስፋን በሚሰጥ መንገድ ነው ብለው አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፤ ይላል አምላካችሁ የሚለውን ጠቅሰው ቀጥለውም በቁ. 2 ላይ “ለኢየሩሳሌም አለዝባችሁ ንገሯት፤ ዐውጁላትም፤ በባርነት ያገለገለችበት ዘመን አብቅቶአል፤ የኃጢአቷም ዋጋ ተከፍሎአል” እግዚአብሔር ማለቱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

መጽናናት የሚፈልገውን እግዚአብሔር ያጽናናል፣

ከእግዚአብሔር ዘንድ መጽናናትን የምንፈልግ ከሆነ እግዚአብሔር ዘወትር ያጽናናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባጠፋን ጊዜ ሲገስጸን ወይም ሲያስተካከለን ተግሳጹ መልካም እረኛ ለበጎቹ እንደሚጨነቅ ዓይነት በርህራሄ ነው ብለው እግዚአብሔር ሲያጽናናን፣ ሲገስጸን፣ ባጠፋን ጊዜም ቢሆን ሲቀጣን በርህራሄ ልብ እንደሆነ አስረድተዋል። የእግዚአብሔር ርህራሄ ከልብ የሚመነጭ በመሆኑ በሠሩት ኃጢአት ተጸጸተው ምህረትን ለመለመን ወደ እርሱ የሚመጡትን በደስታ ይቀበላል ብለዋል።

እግዚአብሔር በኃጢአተኛ ሰው ሲደሰት ርህራሄውን ይገልጻል፣

በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰውን የአባካኙን ልጅ ታሪክ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ልጁን ከሩቅ የተመለከተው አባት ከረጅም ጊዜ አንስቶ ይጠብቀው ስለነበረ ወደ ቤቱ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ከልብ ምሕረትን በማድረግ በዓል በማዘጋጀት የተቀበለው መሆኑን አስታውሰዋል። አሁንም በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተገለጸውን ታሪክ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መቶ በግ ያለው ሰው ከመካከላቸው አንዱ ቢጠፋ ሊፈልገው መሄዱን አስታውሰው ባገኘው ጊዜ ከእርሱ ጋር ከነበሩት ዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ በተገኘው በግ እጅግ መደሰቱን አስረድተዋል። እግዚአብሔርም ኃጢአተኛን ሰው ሲያገኝ የሚሰማው ደስታ፣ እኛም ወደ እርሱ ስንቀርብ የሚሰማው ደስታም ይህን ይመስላል ብለው እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ስለሆነ ወደ እርሱ መቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

እግዚአብሔር ምሕረቱን ስለሚሰጠን መጨነቅ የለብንም፣

በችግር ስንወድቅ ብዙ እንጨነቃለን ያሉት ቅዱስነታቸው ሰይጣንም በችግር ተደናቅፈን በሃዘን ውስጥ እንድንወድቅ እና እንድናማርር ይፈልጋል ብለው ችግር ሲያጋጥማቸው ብዙ የሚያማርሩ እና የሚጨነቁ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። በኃጢአታችን ይህን ያህል ብንጨነቅ እና ብናዝን ኖሮ ያኔ እግዚአብሔር ወደ እያንዳንዳችን ዘንድ በመምጣት ምህረት ያደርግልናል ብለዋል። ሰማይን እና ምድርን የፈጠረ፣ አንድ ልጁን ለእኛ ኃጢአት እንዲሞት አሳልፍ እስኪሰጥ ድረስ የወደደን እግዚአብሔር የምሕረት እና የመጽናናት አምላክ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

ለመጽናናት አምላክ አደራን እንስጥ፣

ኅዳር 30/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ወቅት ያቀረቡትን ስብከታቸውን ባጠቃለሉበት ወቅት እንደገለጹት ምህረትን ለመጠየቅ በቆራጥነት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ መቅረብ እንደሚያስፈልግ አስረድተው እግዚአብሔር ርህሩህ እና አጽናኝ አምላክ በመሆኑ ወደ እርሱ የሚቀርቡትን በደስታ የሚቀበላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
10 December 2019, 15:24
ሁሉንም ያንብቡ >