ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ዲያብሎስ ሰውን ሊያጠፋ የተነሳው እግዚአብሔር እንደ እኛ ስጋን ለብሶ በመምጣቱ ነው” ብለዋል።

ማክሰኞ ህዳር 2/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከተ ወንጌል “ዲያብሎስ ሰውን ሊያጠፋ የተነሳው እግዚአብሔር እንደ እኛ ሰው ሆኖ በመምጣቱ ነው” ብለዋል። ለዛሬ ከመጽሐፈ ጥበብ ምዕ. 2፡ 23 - ምዕ. 3፡9 ላይ ተወስዶ በተነበበው የመጀመሪያ ንባብ ላይ በማስተነተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን ለብሶ ወደዚህ ዓለም መምጣቱ ያስቀናው ዲያቢሎስ እኛን ሰዎች ሊያጠፋን ዘውትር ይሞክራል ብለዋል። የመስዋዕተ ቅዳሴውን ጸሎት ለተካፈሉት ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን በዕለቱ በተነበቡት የቅዱሳት ንባባት በማስተንተን ባቀረቡት ስብከታቸው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን በመልበስ በመካከላችን መገኘቱ ያላስደሰተው ዲያቢሎስ ሞትን የሚያስከትል ጠላትነትን በዓለማችን ውስጥ በመዝራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊያሰናክለን የሚፈልግ ዲያቢሎስ ዘወትር ከጎናችን አልጠፋም በማለት ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅንዓት ተነሳስቶ የእግዚአብሔር ልጅ ስጋን መልበሱን አልወደደም በዚህም የተነሳ የሰውን ልጅ ማጥፋት ይፈልጋል ብለዋል። ልባችንም እርሱ በዘራው የቅንዓት እና የጥላቻ ስሜት የተዋጠ ቢሆንም በወንድማማችነት ፍቅር በሰላም እንኖራለን ብለው በፍቅር እና በሰላም የምንኖር ከሆነ የዲያቢሎስን ጥቃት መመከት እንችላለን ብለዋል። “እኔ በፍጹም በሰው ላይ ጥቃትን አድርሼ አላውቅም የሚለውን የበካታ ሰዎች አባባል ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ጥቃትን መፈጸም የሚቻለው የጥቃት መሣሪያን በመታጠቅ ብቻ ሳይሆን የሰዎችን ስም በማጥፋትም ጥቃትን መፈጸም የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል። ምላስ አስፈሪ መሣሪያ ነው፣ ሰውን የመግደል ሃይል አለው የሚለውን የሐዋርያው ያዕቆብ መልዕክትን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በአሉ ባልታ ወሬ የሰውን ስም ማጥፋት ሰውን ሊገድል የሚችል መሆኑን አስረድተዋል።

“እኔ ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበልኩ፣ ክርስቲያናዊ ሕይወትን በተግባር የምኖር ሰው ነኝ። ታዲያ እንዴት ሰውን ለመጉዳት ወይም ለመግደል እነሳለሁ”? በማለት የሚከራከሩ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የገለጹት ቅዱስነታቸው ከመጀመሪያው ጀምሮ በውስጣችን ጦርነት አለ ብለው፣ ቃኤል እና አቤል ወንድማማቾች ነበሩ። ነገር ግን ቃኤል በወንድሙ በአቤል ላይ በቅንዓት ተነሳስቶ ሊገድለው የበቃ መሆኑን አስታውሰዋል። ይህንን እውኔታ ለመረዳት የሚከብደን ከሆነ በዓለማችን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርነትን እና የጥፋት ተግባራትን መመልከት ብቂ ነው ብለዋል። በጀርመን የቤርሊን ግድግዳ የፈረሰበትን መታሰቢያ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በዚያች አገር የናዚ ስርዓት አቀንቃኞች የበርካታ ሰዎች ሕይወት በከንቱ እንዲጠፋ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

“ይህ ሁሉ ክፋት በሰዎች ላይ እንዲደርስ የሚያደርግ አንድ ሃይል አለ። ይህን ሃይል ፈተና እንለዋለን። ንስሐ ለመግባት ስንቀርብ ይህን እንዳደርግ፣ ያን እንዳደርግ የሚገፋፋ ፈተና በውስጥ አለ እንላለን። ይህ ማለት ደግሞ በልባችን ውስጥ ገብቶ ማድረግ የሌለብንን ነገር እንድናደርግ የሚያድረግ ሃይል፣ ጥፋትን እንድናስከትል የሚገፋፋን፣ ጥላቻን በልባችን ውስጥ የሚዘራ ሃይል አለ ማለት ነው። በዓለማችን ውስጥ ጠላትነትን በመዝራት ጥፋትን የሚያስከትሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን በድፍረት መናገር መቻል ይኖርብናል”።             

በየዕለቱ የምንሰማቸው ዜናዎች የጥላቻ፣ የአጥፍቶ ጠፊነት እና የጦርነት ናቸው። በአለማችን በርካታ ሕጻናት በረሃብ የሚሞቱ መሆናቸው ግልጽ ነው። በንጹሕ የመጠጥ ውሃ እጥረት በውሃ ጥም የሚሞቱ ሰዎች ብዙ ናቸው። የትምህርት እና የሕክምና አገልግሎት ዕድል የማያገኙ በርካቶች ናቸው። ይህ ለምን ይሆናል ብለን ስንጠይቅ ለልማት መዋል የሚቻለው ገንዘብ ለጦር መሣርያ መግዣ ስለሚውል ነው መልስ እናገኛለን። ይህ የሆነበት ምክንያት የፍቅር ሳይሆን የጥላቻን ዘር ዲያቦሎስ በሰዎች ልብ ውስጥ ዘርቶ ስለሄደ ነው በማለት ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

“ዲያቢሎስ ይህን የሚያደርገው የእግዚአብሒር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን ለብሶ ወደዚህ ዓለም መምጣቱን መቀበል ስላቃተው ነው”።       

የክፉ ተግባር ምንጭ የሆነው ዲያቢሎስ በሰዎች መካከል ሰላም እና ፍቅር እንዲጠፋ ስለሚያደርግ ነው። በዓለማችን ውስጥ ለሚከሰቱት የጦርነቶች እና የረሃብ ጥፋቶች እና አደጋዎች በሙሉ ምንጩ ዲያቢሎስ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

“ይህን የመሰለ ጥፋት በዓለማችን ውስጥ ለምን ይከሰታል፣ በሕዝቦች መካከል የጠላትነት ስሜት እያደገ የመጣበት ምክንያት ለምንድነው ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። በቤተሰብ መካከል፣ በጎረቤት መካከል፣ በሥራ ቦታ፣ በፖለቲካ ዘርፍም ቢሆን ጥላቻ የነገሠበት ዋናው ምክንያት ጠላትነትን የሚዘራ የዲያቢሎስ እጅ ስላለበት ነው”።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ያሰሙትን ስብከተ ወንጌል ባጠቃለሉበት ወቅት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት በልባችን ውስጥ እንዲያድግ፣ ዲያቢሎስ የሚያቀርብልንን ስጋዊ ፈተናዎች ማስሸነፍ እንድንችል፣ በልባችን ውስጥ ጥላቻን እና ምቀኝነትን የሚዘራ ዲያቢሎስን ማሸነፍ የምንችልበትን ሃይል እንዲሰጠን ወደ እግዚአብሔር አባታችን ጸሎታችንን ማቅረብ ያስፈልጋል በማለት የዕለቱን ስብከተ ወንጌል ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

12 November 2019, 16:34
ሁሉንም ያንብቡ >