ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የእግዚአብሔርን ነጻ ግብዣ መቀበል ያስፈልጋል” አሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን የተገኙበትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ከሉቃ. 14:15-24 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው ብዙን ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ሊቀርቡ የሚችሉ የተለያዩ ምርጫዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ በሕይወቴ ውስጥ ምን ያስፈልገኛ? ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣልኝ ነጻ ግብዣ መቀበል፣ ዘወትር እርሱን መፈለግ እና ወደ እርሱ መቅረብ ወይስ ውስን በሆነ በራስ መንገድ ብቻ በመጓዝ የብቸኝነትን ሕይወት መኖር የሚሉ መገኘታቸውን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሉቃ. 14:15-24 ላይ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘለዓለም የምንኖርበትን የሰማዩን ቤታችን በሚያስታውስ የእራት ግብዣ ምሳሌን በማስታወስ ባቀረቡት ስብከታቸው፣ ተጋብዘን በምንገኝበት በዓል ላይ የምናውቃቸው ሆነ የማናውቃቸው እንዲሁም ልናያቸው የማንፈልጋቸው ሰዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልጸው በነጻ የተጠሩበት ግብዣ በመሆኑ የደስታ ስሜት ይታይበታል ብለዋል። እውነተኛ ግብዣ ነጻ መሆን አለበት ያሉት ቅዱስነታቸው እግዚአብሔር የሚያቀርብልን ግብዣ ገንዘብ የማይከፈልበት ነው ብለው ወደዚህ ግብዣ የምንገባበትን ዋጋ የሚከፍለው ራሱ የግብዣው ባለቤት ነው ብለዋል። ግብዣው ዋጋ የማያስከፍል ነጻ ቢሆንም የራሳቸውን ፍላጎት የሚያስቀድሙ አንዳንድ ሰዎች ይኖራሉ ብለዋል።      

ከሕብረት እና ከአንድነት የሚገኘውን በረከት በጋራ ለመካፈል በሚፈለግበት ወይም በሚታሰብበት ጊዜ ሃሳብን የሚያስቀይር ስሜት ይፈጠራል። ይህ ስሜትም ከሌሎች ጋር ላለመሆን ወይም ላለመዋል የሚያደርግ የብቸኝነት ስሜት ነው። በዚህ የተነሳ ብቻዬን መሆን እፈልጋለሁ፣ ብቻዬን መሆን ያስደስተኛል የሚል ሃሳብ ይመነጫል። የእስራኤል ሕዝብ ኃጢአት የሁላችን ኃጢአት ነው። ከሌሎች ጋር ሕብረትን፣ አንድነትን፣ ወዳጅነትን ከመፍጠር ይልቅ ብቸኝነትን መምረጥ፣ ከሌሎች በመገለል የራስን መንገድ ብቻ መከተል፣ የራስ በሆኑ ነገሮች ብቻ መጨነቅ፣ ከብቸኝነት የሚገኝ ጥቅም የለም።

ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚቀርበውን ነጻ ግብዣ አለመቀበል እና አልፈልግም ማለት ጋባዡን መናቅ እና ማስቀየም እንደሆነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው የእግዚአብሔርን ነጻ ግብዣ አለመቀበል ከእርሱ ጋር በሚገናኙበት ጊዜ የሚያገኙትን ደስታ ማጣት ይሆናል ብለዋል።  

በሕይወት ጉዞ ወቅት ብዙን ጊዜ እነዚህን የመሳሰሉ አማራጮችን እናገኛቸዋለን፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣልንን ነጻ ግብዣ፣ እግዚአብሔርን የመፈለግ፣ እርሱን የማግኘት እና ወደ እርሱ የመቅረብ ጸጋን፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ በራስ መንገድ ብቻ በመጓዝ፣ በራስ ሃሳብ ብቻ በመመራት የራስን ምኞት መፈጸም ነው። በራስ ሃብት፣ እውቀት ወይም ምኞት ብቻ መመካትን በማስመልከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአንድ ባለጸጋ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ ምን ያህል ከባድ ነው በማለት ተናግሯል። ባለጸጋ ወይም ባለሃብት የሆኑ ጎበዞች ሰዎች፣ ቅዱሳኖች፣ የሃብታቸው ተገዥ ያልሆኑ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም። ነገር ግን ለግል ሕይወት ብቻ የሚጨነቁ፣ መመኪያቸውን እና አለኝታቸውን ሃብታቸው እና ገንዘባቸው ያደረጉ ብዙ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ታዲያ ስለ አብሮነት፣ በዓላትን በሕብረት ስለ ማክበር ቢነገራቸው ሊገባቸው አይችልም። ምክንያቱም ለደህንነታቸው ዋትናን የሚሰጥ ከሃብታቸው በቀር ሌላ የላቸውምና።

 

እግዚአብሔር ደጉንም፣ ክፉንም በግብዣው እንዲገኙለት ይፈልጋል፣

እግዚአብሔር በግብዣው ላይ ክፉም ደጉም እንዲገኝለት ይፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰዎች በክፉ ስራቸው ምክንያት በግብዣው ላይ መገኘት እንደማይችሉ ማሰብ እንደሌለባቸው አስረድተው እግዚአብሔር ክፉ ለሰሩትም ሆነ ክፉ ላልሰሩት ልዩ እና ያማረ ግብዣን አዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል ብለዋል። በስብከታቸው የአባካኙን ልጅ ታሪክ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው የዚህ ልጅ አባት ከልጁ አንደበት ምንም የጸጸት ቃል እንዳይወጣ፣ ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ ልጁ በመሆኑ ብቻ የሰራውን ጥፋት ሳይቆጥርበት በርህራሄ ልብ ሊቀበለው መፈለጉን አስታውሰዋል። በመስዋዕት ቅዳሴ ጸሎት ላይ የቀረበውን የመጀመሪያ ንባብ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች የላከውን መልዕክት በማስታወስ ባቀረቡት አስተንትኖ አይሁዳዊያን ራሳቸውን እንደ ጻድቅ ቆጥረው ኢየሱስን ያልተቀበሉ መሆኑን ገልጸው፣ ኢየሱስም በዚህን ጊዜ ዝሙት አዳሪዎች እና ቀራጮች ወደ መንግሥተ ሰማያት በመግባት እንደሚቀድሟቸው መናገሩን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስብከታቸውን በመቀጠል እግዚአብሔር እጅግ የተናቁትን እንደሚወድ ገልጸው በግለኝነት ስሜት ውስጥ በመግባት ከእርሱ ለመራቅ ብንሞክርም የእግዚአብሔር ጥሪ ለሁላችን መሆኑን አስረድተዋል።             

ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረንን ምሳሌ እናስተውል፤ “ሕይወታችን ምን ይመስላል?” ፣ “ምንስ ያምረኛል? ምንስ እመርጣለሁ?”፣ የኢየሱስን ጥሪ መቀበል ወይስ ከሌሎች ራሴን በማግለል በራስ ምርጫ ወይም በራስ መንገድ ብቻ መጓዝን እፈልጋለሁ? እናም ሁል ጊዜ እርሱ ወደሚጠራን ነፃ ግብዣ ለመሄድ የሚያስችለንን ጸጋ እንዲሰጠን እግዚአብሔርን በጸሎታችን እንጠይቅ።  ብለዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅድሴ ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ የክህነታቸውን 70ኛ ዓመት በዓላቸውን ያከበሩ የ96 ዓመት ዕድሜ ካህን መገኘታቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
05 November 2019, 16:30
ሁሉንም ያንብቡ >