ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የክርስቲያን ተስፋ ዘላቂ መሆን ያስፈልጋል” አሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ከካህናት ደናግል እና ምእመናን ጋር በመሆን የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በወቅት ባሰሙት ስብከተ ወንጌል “በተስፋ የምንኖር ከሆነ በሌላ በምንም መመካት የለብንም፤ ኢየሱስን አጥብቀን መያዝ ይኖርብናል፤ አለበለዚያ ሕይወት ውጣ ውረድ የበዛበት፣ ለውጥም የማይታይበት ይሆናል” ማለታቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ዴቦራ ዶኒኒ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለዕለቱ በተመደበው የመጀመሪያ ንባብ፣ ወደ ሮሜ ምዕ. 8: 18-25 ላይ በማስተንተን ሰብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ያላቸው ምኞት ጽኑ እንዲሆን ያስፈልጋል ብለው ይህ ካልሆነ ሕይወት በብዙ ክፋት ውስጥ እንደሚወድቅ፣ የክርስትና ሕይወትም በርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ የሚበከል መሆኑን አስረድተዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ተስፋን ስለ ማድረግ አስመልክቶ ለሮማዊያን የጻፈውን መልዕክት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ሐዋርያው በመልዕክቱ በምዕ. 8፡18 ላይ “ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ” ማለቱን ገልጸው ክርስቲያን እግዚአብሔር እስከሚገለጥለት ድረስ በተስፋን መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ችግር እና ስቃይ ሊኖር ይችላል፤ ያም ቢሆን ነገ ነውና፣ ዛሬ ጊዜ እያለ ቃል የተገባልን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እስኪሰጠን ድረስ በተስፋ መጠባበቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም “ተስፋ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት የምናደርገው ቆይታ ነው፤ መርከብ እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ የያዝነው ገመድ ይመስላል” ካሉ በኋላ በተሰጠን ተስፋ ነጻ የምንወጣው እኛ ብቻ ሳንሆን መላው ፍጥረት ነው ብለው ይህን በማድረጋችን ወደ እግዚአብሔር ልጆች ክብር ውስጥ እንገባለን ብለዋል።

ይህን ዓለም የዘለዓለም መኖሪያችን አድርገን እስካልወሰድን ድረስ ተስፋ ዘወትር ዝግጁዎች ሆነን እንድንኖር ያደርገናል፤ የክርስቲያን ሕይወትም ቀጣይነት ያለው ነው። ታዲያ ክርስቲያን በተስፋ የማይኖር ከሆነ፣ መሠረቱን በተስፋ ላይ ያልገነባ ከሆነ፣ በሕይወቱ ለውጥን ሊያሳይ አይችልም ብለዋል። የማይፈስ ወይም በአንድ ሥፍራ የረጋ ውሃን እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው ውሃ እንኳን የማይንቀሳቀስ ከሆነ ሽታን ይፈጥራል ብለዋል። ክርስቲያንም ቢሆን በክርስትና ሕይወቱ ለውጥን የማያሳይ ከሆነ፣ ወደ ሌሎች ዘንድ የማይሄድ እና ብቻውን የሚቀመጥ ከሆን ችግር እንዳለበት ያመለክታል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ለዚህ ክርስቲያን የክርስትና ሕይወቱ እምነት ብቻ እንጂ ተስፋ የሌለበት ይሆናል ብለዋል።

ተስፋን መገንዘብ አስቸጋሪ እንደሆነ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ስለ እምነት የምንናገር ከሆነ ስለ ፈጠረን እግዚአብሔር፣ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድነትን ስላስገኘልን እግዚአብሔር እንደምንናገር እናውቃለን። ይህንንም በሐዋርያት ጸሎተ ሐይማኖት እንገልጻለን ወይም እናረጋግጣለን። ስለ ቸርነት የምንናገር ከሆነ ለጎረቤቶቻችን እና ለተቸገሩት ሰዎች በምናደርግላቸው በጎ ሥራዎቻችን በተግባር መመልከት እንችላለን። ተስፋን ማወቅ ግን አስቸጋሪ፣ እጅግ በጣም ትሑት እና ድሃ የሆነ ሰው ብቻ ሊያውቀው የሚችለው ነው ያሉት ቅዱስነታቸው የተስፋ ሰዎች ለመሆን ወይም ስለተስፋ ማወቅ ከፈልግን እጅግ ደሃ እና በምንም የማንመካ እና ግልጾች መሆን ይኖርብናል። ተስፋ ትሁት ነው፤ በምንም አይመካም፤ በመሆኑ በየዕለቱ የምንመካበት፣ የየዕለቱ መተማመኛችን ሊሆን ይገባል፤ እርሱም በውስጣችን ሆኖ መልካምን እንድናደርግ የሚገፋፋን መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አስረድተዋል።

በተስፋ እንዴት መኖር እንደምንችል የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዛሬ ከተነበበው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ቅዱስ ሉቃ. የጻፈን መሠረት በማድረግ ስብከታቸውን አቅርበዋል፤ እርሱም። የእግዚአብሔር መንግሥት ምን ትመስላለች፥ በምንስ አስመስላታለሁ? ሰው ወስዶ በአትክልቱ የጣላትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ አደገችም ታላቅ ዛፍም ሆነች፥ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ሰፈሩ አለ። ደግሞም፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን አስመስላታለሁ? ሴት ወስዳ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች አለ (ሉቃ.13: 18-21)። በዚህ የወንጌል ክፍል ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ከሰናፍጭ ቅንጣት ጋር በማመዛዘን ለምሳሌነት መጠቀሙን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የሰናፍጭ ቅንጣት እጅግ በጣም ትንሽ ብትሆንም መብቀል እና ማደግ እንደምትችል ይህ እንዲሆን ጊዜን ሰጥቶ በትዕግስት መጠበቅ የሚያስፈልግ መሆኑን ተናግረው፣ ሐዋርያው ጳውሎስም እንደሚለው፣ የተስፋን ውጤት ወይም ተስፋን ለማየት በትዕግስት መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ተስፋ በዓይናችን የማናየው ነገር ግን ለክርስትና ሕይወታችን ዋስትና የሚሆነን፣ ምንም ቢሆን የማያስቀይመን የዕለተ ዕለት መተማመኛችን ነው ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
29 October 2019, 16:32
ሁሉንም ያንብቡ >