ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “እምነት በርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ መበረዝ የለበትም”።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ማክሰኞ መስከረም 27/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከተ ወንጌል፣ ከልባቸው ማነስ የተነሳ የተለያዩ ፍርዶችን እየሰጡ የሚገኙት በርካታ የክርስቲያን ወገኖች መኖራቸውን አስታውሰው፣ እምነትን በርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ መለወጥ አያስፈልግም ብለዋል። ቅዱስነታቸው ይህን ካሳሰቡ በኋላ ፍርድን ሳይሆን ድነትን ይዞ የመጣው እግዚአብሔር የሰው ልጅ ለሚያደርገው በደል ምሕረት እንዲያበዛ በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዛሬ ከትንቢተ ዮናስ ምዕ. 3፤1-10 ተወስዶ በተነበበው የመጀመሪያው ንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው በእግዚአብሔር እና በነብዩ ዮናስ መካከል ስለተፈጠረው ታሪክ በማንሳት አብራርተዋል። የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፤  “ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ፣ በእርሷ ላይ ስበክ፤ ክፋቷ በእኔ ፊት ወጥቶአልና።” ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ኰበለለ፤ ወደ ተርሴስም ለመሄድ ተነሣ። (ትንቢተ ዮናስ 1፤1-3) በዚህ በመጀመሪያው የትንቢተ ዮናስ መጽሐፍ ላይ ያስተነተኑት ቅዱስነታቸው ነብዩ ዮናስ ከእግዚአብሔር መራቅን የመረጠ ቢሆንም እግዚአብሔር ከዓሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ በሦስተኛው ቀን አውጥቶት እንዳዳነው አስታውሰዋል።

መለውጥን ለሚሹት እግዚአብሔር ይራራል፣

እግዚአብሔር ለሁለተኛ ጊዜ ባቀረበለት ጥሪ ነብዩ ዮናስ መታዘዙን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ነብዩ ዮናስ ልበ ደንዳና እና ከአቋሙ መለየት ያልፈለገ ቢሆንም እግዚአብሔር በምሕረቱ ብዛት ሊያድነው እንደመጣ አስታውሰዋል። በክርስቲያኖች መካከልም የነብዩ ዮናስን መንገድ የሚከተሉ እንዳልጠፉ፣ ክርስትናቸውን ባሻቸው መንገድ በመተርጎም በሚፈልጉት አቅጣጫ የሚጓዙ፣ የእግዚብሔርን እቅድ እና ሃሳብ ሳይቀር በራሳቸው መንገድ እና አስተሳሰብ የሚለውጡ መኖራቸውን አስረድተዋል።

የራሳቸውን መንገድ የሚከተሉ ክርስቲያኖች መለወጥን ይፈራሉ፣

ከእግዚአብሔር ይልቅ በሚመስላቸው መንገድ መጓዝ የሚፈልጉ ክርስቲያኖች ወደ ዓለማዊ ርዕዮተ ዓለም የሚያዘነብሉ መሆናቸውን ተናግረው ከክርስትናው መንገድ ወደ ርዕዮተ ዓለሙ አስተሳሰብ የሚያደርጉት ጉዞ የማይመች እና ስቃይ የበዛበት እንደሚሆንባቸው አስረድተዋል። ይህን መንገድ የሚጓዙ በርካታ ክርስቲያኖች መኖራቸውን አስታውሰው፣ መለወጥን የሚፈሩ፣ የሕይወት ፈተናዎችን መጋፈጥ የማይፈልጉ፣ እግዚአብሔር በሚመርጥላቸው መንገድ መጓዝን የማይፈልጉ መሆናቸውን አስረድተው፣ እነዚህ ሰዎች ከክርስቲያን ማሕበረሰብ ራሳቸውን በማራቅ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብን መከተል የወሰኑ ናቸው ብለዋል። እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ማድረግን የሚፈሩ፣ ከልባቸው ማነስ የተነሳ በሌሎች ላይ የሚፈርዱ ናቸው ብለው    እግዚአብሔር ግን የሰውን ልጅ ውድቀት በመመልከት ዘወትር ለመፈወስ እና ለማዳን እንጂ ለመፍረድ ያልመጣ አለመሆኑን አስረድተዋል።

08 October 2019, 16:59
ሁሉንም ያንብቡ >