ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የእግዚአብሔር ቃል የደስታችን ምንጭ ነው”።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሐሙስ መስከረም 22/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከተ ወንጌል ቅዱስ ቃሉ ወደ ልባችን ሲደርስ በደስታ የሚሞላን መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ሰንበትን ያለ እግዚአብሔር ቃል ማክበር አንችልም ብለዋል። በመሆኑም ደስታን የሚሰጠንን የእግዚብሔር ቃል ለመቀበል ልባችንን መክፈት ያስፈልጋል ብለዋል። በዕለቱ ከመጽሐፈ ነህምያ ምዕ. 8 ተወስዶ በተነበበው በመጀመሪያው ንባብ ላይ አስተንትኖን ያደረጉት ቅዱስነታቸው የእግዚአብሔርን ቃል በጽሞና ማዳመጥ እና በልባችን ማኖር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በመጽሐፈ ንህምያ በምዕ. 8 ላይ የተገለጸው ታሪክም ሕዝቡ የእግዚአብሔር ቃል በመቀበል ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገውን ግንኙነት ያመለክታል ብለውል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል የተጠማ ነበር፣

የአገሩ ገዥ የነበረ ነህምያ፣ ካህን እና ጸሐፊ የሆነው ዕዝራ እና ሕዝቡን ያስተዳድሩ የነበሩ ሌዋውያን በሕብረት ሆነው ለሕዝባቸው እንዲህ በማለት ያሳውቃሉ፥ “የዛሬ ቀን ለእግዚአብሔር ክብር የተሰጠ ነው”። ይህ ቀንም እኛ እሑድ የምንለው ነው። እሑድ ቀን ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበት ዕለት ነው። እኔም ወላጆቼም ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት። ለእርሱ የተሰጠ የተቀደሰ ቀን ነው።

ያለ እግዚአብሔር ቃል ሰንበትን ማክበር አንችልም፣

መጀመሪያ በተነበበው በመጽሐፈ ነህምያ ላይ የተገለጸው ታሪክ የእግዚአብሔር ቃል በሚነገርበት ጊዜ ሕዝቡ በደስታ በመሞላት የተነሳ ያልቅስ ነበር ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የእግዚብሔርን ቃል ስንሰማ ምን ይሰማናል? ቃሉን በጽሞና አዳምጣለሁ? ልቤን እንዲነካው ዕድል እሰጣለሁ ወይስ በሌላ ሃሳብ ውስጥ በመግባት ሳልሰማው እቀራለሁ? የእግዚአብሔር ቃል ወደ ልቤ ውስጥ እንዲገባ ምን አደርጋልሁ? የእግዚብሔር ቃል ወደ ልባችን ውስጥ ሲገባ በደስታ በመሞላት እናለቅሳለን፣ በዓልም እናደርጋለን። የእግዚአብሔር ቃል ወደ ልባችን ውስጥ እንዲገባ ካልፈቀድንለት ልንደሰት አንችልም፤ ሰንበትንም በደስታ ማክበር አንችልም። ነህምያም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፥ ሂዱ በዓልን አክብሩ፣ ጮማ ስጋን ብሉ፣ ጣፋጭ የውይን ጠጅንም ጠጡ፣ የቀረውንም ለሌላቸው፣ ለተራቡት እና ለተጠሙት ስጡ” የሚለውን አስታውሰው ሰንበት የእግዚአብሔር ቀን በመሆኑ በዕለቱ የሚነገረውን የእግዚአብሔር ቃል በማዳመጥ ደስታን እና ሃይልን ማግኘት ያስፈልጋል ብለዋል።

ልባችንን ለደስታ አለመክፈት ሐዘንን ያስከትላል፣

በዛሬ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ላይ ያስተነተኑት ቅዱስነታቸው በሐዘን ውስጥ የምንወድቀው ልባችንን ለደስታ ክፍት ስለማናደርግ ነው ብለው ይህም ሃይላችን ሊሆን አይችልም ብለዋል። የእግዚአብሔር ቃል ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል። ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ያለን ግንኙነት በደስታ እንድንሞላ ስለሚያደርግ ሃይላችን ይሆነናል። ክርስቲያኖች ደስተኞች የሚሆኑት የእግዚብሔርን ቃል በልባቸው ስለተቀበሉ ነው። በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር የማያቋርጥ ግንኙነትን ስለሚፈጥሩ እና ቃሉንም ዘወትር ስለሚፈልጉ ነው። የዛሬ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ዋና መልዕክትም ይህ ነው። ስለዚህ ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል፥ የእግዚብሔርን ቃል እንዴት ባለ ሁኔታ አዳምጣለሁ? ወይስ ከነጭራሹ አላዳምጠውም? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት መገናኘት እችላለሁ? ከእግዚአብሔር ስገናኝ የማገኘው ደስታ በእርግጥ የዘወትር ሃይሌ ነው? ሐዘናችን ደስታችን ሊሆን አይችልምና።                       

ልባችን በእግዚአብሔር ደስታ ተሞልቶ በሚያለቅስበት ጊዜ ጠላታችን በሌላ ወገን ደግሞ በሐዘን ሊሞላው ይታገላል። የእስራኤል ሕዝብ ከባቢሎን ግዛት ነጻ በወጣበት ጊዜ ወደር በሌለ ደስታ ውስጥ መግባቱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው እግዚ አብሔርን በቅዱስ ቃሉ በኩል ስናገኘው ደስታችንም ወደር የለውም ብለው አስተንትኖአቸውን ሲያጠቃልሉ እግዚአብሔር ልባችንን የምንከፍትበትን፣ ቃሉንም በውስጣች የምናስገባበትን ድፍረት፣ በደስታ ተሞልተን ሰንበትን የምናከብርበትን ጸጋ ለሁላችን ይስጠን በማለት የዕለቱን ስብከት ደምድመዋል።

03 October 2019, 17:31
ሁሉንም ያንብቡ >