ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ጳጳሳት እና ካህናት በመተባበር ወደ ምእመናን እንዲቀርቡ አሳሰቡ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዛሬ ዓርብ መስከረም 9 ቀን 2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ለተካፈሉት ካህናት፣ ደናግል እና ምዕመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል፣ ካህናት እና ጳጳሳት ከምዕመናኖቻቸው ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲኖራቸው በጸሎት እናግዝ ብለዋል። ቅዱስነታቸው ቀጥለውም በመካከላቸው ያለው መንፈሳዊ ግንኙነት በሚያድጉባቸው አራት መንገዶች ላይ ማስተንተናቸውን የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ ዴቦራ ዶኒኒ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።     

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዓን ጳጳሳት በጸሎታቸው አማካይነት ከእግዚአብሔር፣ ከካህናት እና ከሕዝበ እግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ያቀረቡት አስተንትኖ መነሻን ያደረገው ትናንት እና ዛሬ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት ወቅት በተነበቡት የቅዱሳት መጽሐፍት ንባባት ላይ መሆኑ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ትናንት ባቀረቡት ስብከተ ወንጌል፣ የክህነት አገልግሎት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ መሆኑን መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን በዛሬ አስተንትኖአቸው የወንጌል አገልግሎትን ሊያዳክሙ የሚችሉ ሁለት እንቅፋቶች እነዚህም የሃብት ምኞት እና ዋጋ ቢስ የሆኑ ጭቅጭቆች እና ክርክሮች መሆናቸውን አስረድተዋል። አንድ የወንጌል አገልጋይ፣ ጳጳስ፣ ካህን ወይም ዲያቆን በገንዘብ ፍቅር መጠመድ ሲጀምር በበርካታ እንቅፋቶች የሚደናቀፍ መሆኑን አስረድተው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈውን የመጀመሪያ መልዕክት ምዕ. 6፤2-12 የተጠቀሰውን በማስታወስ “ሰይጣን የሚገባው በኪስ በኩል ነው” የሚለውን የአባቶች ንግግር አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅት ያቀረቡት አስተንትኖ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላካቸው ሁለት መልዕክቶች አማካይነት ምክሩን ለቤተክርስቲያን አገልጋዮች በሙሉ ማቅረቡን አስታውሰዋል። ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቅርብ እንዲሆኑ የተጠሩት ጳጳሳት ብቻ ሳይሆኑ ካህናት እና ዲያቆናትም ጭምር መሆናቸውን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ይህን ከተናገሩ በኋላ በመካከላቸው ያለው መንፈሳዊ ግንኙነት በሚያድጉባቸው አራት መንገዶች ጠቅሰዋል። በጳጳስ እና በእግዚአብሔር መካከል ላለው ግንኙነት ቅድሚያን በመስጠት ባቀረቡት ስብከታቸው ሐዋርያት መበለቶችን እና ወላጅ አልባ ልጆችን ለማገልገል ዲያቆናትን እንደመረጡ፣ ለራሳቸው ግን ጸሎትን ለማዘወተር እና ቅዱስ ወንጌልን ለመመስከር በቂ ጊዜን መመደባቸውን አስታውሰዋል። በመሆኑም የአንድ ጳጳስ ቀዳሚ ተግባር ጸሎትን ማቅረብ እንደሆነ ገልጸው፣ ጸሎት ሃይላቸው እንደሚሆን እና የተሰጣቸውን ክህነታዊ የአገልግሎት ስጦታን እንዲያውቁ ያግዛል ብለዋል። ጳጳስን ወደ ምእመናን እንዲቀርብ የሚያግዝ ሁለተኛው መንገድ ከካህናት፣ ከዲያቆናት እና ከቅርብ ረዳቶቹ ጋር ያለው የጠበቀ ግንኙነት እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

አንድ ጳጳስ በስሩ የሚገኙትን ካህናት መዘንጋት ያሳዝናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተለያዩ ምሳሌዎችን ጠቅሰው እንደተናገሩት፣ አንድ ካህን ከጳጳሱ ጋር መገናኘት ፈልጎ ዕድል ሳይሰጠው ሲቀር በእርግጥ ያሳዝናል ብለው ጳጳስ ለካህናት ያለው የአባትነት ስሜት ማነስ የለበትም ብለው ካህናትም እንዲሁ የወንጌል አገልግሎታቸውን በፍሪያማነት ማበርከት የሚችሉት በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት አጠናክረው ሲገኙ ነው ብለው ይህ ካልሆነ ግን ለክፍፍል እና ለልዩነት መንገዶች ይከፈታሉ ብለዋል። ሦስተኛው ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ መቅረቢያ መንገድ በካህናት መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ሲሆን አራተኛው ከምዕመናን ጋር ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ነው ብለዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ መልዕክቱ እግዚአብሔር ከወዴት እንደጠራው መዘንጋት እንደሌለበት የተናገረውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ መልዕክቱ ጢሞቴዎስ የራሱን ሕዝብ ፈጽሞ መርሳት እንደሌለበት ማሳሰቡን ገልጸዋል።              

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም የጳጳሳት ጉባኤ እና የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ከእግዚአብሔር፣ ከካህናት እና ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበው፣ ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን የክህነት አገልግሎት ስጦታ በሚገባ እንዲያውቁ ለጳጳሳት እና ለካህናት መጸለይ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

20 September 2019, 16:58
ሁሉንም ያንብቡ >