ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የክህነት አገልግሎት ስጦታ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ከካህናት ደናግል እና ምእመናን ጋር በመሆን የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ወቅት ባሰሙት ስብከተ ወንጌል፣ ስለ ቤተክርስቲያን የአገልግሎት ስጦታ ሲነሳ ወደ ግል በማዛወር የስጦታውን ትክክለኛ ትርጉም ወደ መርሳት እንደርሳለን ብለዋል። የተሰጠንን ስጦታ ታላቅነት አናስተውልም ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የክህነት አገልግሎት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እግዚአብሔር መርጦን “ተከተለኝ” ብሎ ለአገልግሎት ሲያሰማራን በክፍያ ወይም የቅጥር ውል አዘጋጅቶ አይደለም ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ካህናት እና ጳጳሳት የተገኙበት ሲሆን በመካከላቸው የክህነታቸውን 25ኛ ዓመት የሚያከብሩ የተገኙ ሲሆን በኢጣልያ የአንኮና ሀገረ ስብከት ጳጳስ የነበሩ ብጹዕ ካርዲናል ኤድዋርዶ ሜኒኬሊ መገኘታቸው ታውቋል። በዕለቱ በቀረበው በመጀመሪያው የቅዱስ መጽሐፍ ንባብ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ጢሞቴዎስ የላከውን መልዕክት መሠረት በማድረግ ስብከታቸውን ያሰሙት ቅዱስነታቸው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ መልዕክቱ ስለ ወንጌል አገልግሎት ስጦታ የተናገረውን አስታውሰው፣ ሐዋርያው ጢሞቴዎስን “በአንተ ውስጥ ያለውን ስጦታ ችላ አትበል” በማለት መምከሩን አስታውሰዋል።                    

“የወንጌል አገልግሎት ስጦታ በአሰሪ እና በሰራተኛ መካከል የሚደረግ የሥራ ውል አይደለም” ያሉት ቅዱስነታቸው “በቅድሚያ የእግዚአብሔርን የአገልግሎት ጥሪ እንደ ስጦታ መቀበል እንደሚያስፈልግ እና ቀጥሎም የዚህን ስጦታ ታላቅነት እና ክብር መረዳት ያስፈልጋል” ብለዋል። “ይህን የምንዘነጋ ከሆነ ለአገልግሎት ጥሪ የሚሰጠውን ትክክለኛ ትርጉም እናጣለን” ብለዋል።

የተሰጠንን የወንጌል አገልግሎት ስጦታን የግል ማድረግ አያስፈልግም፣

“የወንጌል አገልግሎት ስጦታን በትክክል ካለመገንዘብ የተነሳ በበርካታ ችግሮች ውስጥ እንወድቃለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የተሰጠንን የወንጌል አገልግሎት ስጦታን ወደ ግል ጥቅም በማዞር፣ ለኢየሱስ ሊቀርብ የሚገባውን ምስጋና በማጓደል ለእርሱ ያለንን ፍቅር እንቀንሳለን” ብለዋል። የወንጌል አገልግሎትን ማበርከት መልካም ነው፣ ነገር ግን አስቀድሞ የዚህ ስጦታ ምንነት በትክክል መገንዘብ እና በልባችንም መያዝ ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ሐዋርያው ጳውሎስን በመጥቀስ እንደተናገሩት የቤተክርስቲያን አባቶች እጃቸውን ጭነው የሚያወርሱት የቤተክርስቲያን አገልግሎት ለብጹዓን ጳጳሳት እና እንዲሁም ለካህናት ተመሳሳይ ትርጉም አለው ብለው ይህን የወንጌል አገልግሎት ስጦታ ክፍያ እንደሚያስፈልገው ሥራ ዓይነት መመልከት አይገባም ብለዋል።

ለስጦታዎች ምስጋናን ማቅረብ የዘነጋ ፈሪሳዊ፣

የስጦታን ትክክለኛ ትርጉም መርሳት ሰብዓዊ ባሕርይ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሉቃስ ወንጌል ላይ ኢየሱስን ወደ ቤቱ የጋበዘውን ሃብታም ፈሪሳዊ ታሪክ በማስታወስ እንደተናገሩት ይህ ፈሪሳውዊ ሃብታም እና ደግ ቢሆንም በቤቱ ያለውን የሃብት ስጦታ ለእንግዳው በማቅረብ ተገቢ መስተንግዶን ማድረግ መዘንጋቱን አስታውሰው፣ የአገልግሎት ስጦታችንን ወደ ግል ጉዳይ ስንወስደው በጥቅም በመቀየር ትክክለኛ ትርጉሙን እንዘነጋዋለን ብለዋል። እኛ ካህናት የተሰጠንን የወንጌል አገልግሎት ስጦታ በተግባር እናከናውናለን ነገር ግን ማዕከላዊ ትርጉሙን ሳንገነዝብ የምንቀር ከሆነ እና ተልዕኮውም ከወዴት መምጣቱን ካልተረዳን ስጦታችን ትርጉም ያጣል ብለዋል። 

19 September 2019, 17:59
ሁሉንም ያንብቡ >