ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት፣  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “መንፈስ ቅዱስን የሕይወታችን መሪ ልናደርገው ይገባል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት፣ ደናግልና ምዕመናን ለዕለቱ የተቀመጠውን  የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ መሠረት በማድረግ ስብከታቸውን አቅርበዋል። ከዮሐ. በ3፤ ከ7-15 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ምንባብ በማስተንተን ባሰሙት ስብከት መንፈስ ቅዱስ ከአቅማችን ውስንነት እና ከሞታችንም እንድንነሳ ስለሚያደርገን ለእርሱ ዕድል ልንሰጥ ያስፈልጋል ብለው ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ ክርስቲያናዊ ሕይወት መኖር አንችልም ብለውል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አሁን ከምንገኝበት ሕይወት የበለጠ አድገን፣ ከወደቅንበት ተነስተን መቆም የምንችለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት ባስነሳው በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ነው ብለዋል። እግዚአብሔር አምላካችንም መንፈስ ቅዱስን የላከልን ለዚህ ተግባር ነው ብለዋል። ምክንያቱም ብቻችን ምንም ማድረግ እንደማንችል ያውቃልና ብለዋል። ዛሬ በቫቲካን በሚገኝ በቅድስት ማርታ ጸሎት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያቀረቡት ስብከተ ወንጌል፣ በዮሐ. 3፤7-15 ላይ እንደተገለጸው፣ ኒቆዲሞስ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበውን ጥያቄ መሠረት ያደረገ እንደነበር ታውቋል።

እኛም በበኩላችን ተመሳሳይ ጥያቄን ማቅረብ እንችላለን ያሉት ቅዱስነታቸው ሃኡልን ለማግኘት ከፈልግን ከላይ ከሰማይ እንደገና መወልድ እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አስረድተው ይህንን ምስጢር ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ ጋር አንድ አድርገዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንደሆነ አስታውሰው፣ ብርሃነ ትንሳኤው በተከናወነበት ተመስሳይ ዕለት ለሐዋርያቱ ተገልጦ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ” ማለቱንም አስታውሰዋል። የክርስትና ሕይወታችን በበጎ ባሕርያችን እና ጸባያችን ብቻ የሚገለጥ፣ ይህን በማድረግ፣ ያንን ካለማድረግ የሚገለጥ ሳይሆን፣ በርካታ ነገሮችን በእጆቻችን፣ በችሎታችን በመታገዝ ማከናወን ብንችልም ነገር ግን በክርስትና ሕይወትን እንደገና ተወልደን አዲስ ሃይል የምናገኘው ከመንፈስ ቅዱስ በመሆኑ መንፈስ ቅዱስን የሕይወታችን መሪ ልናደርገው ይገባል ብለዋል።

ሕይወታችን፣ ነፍሳችን በርካታ እጅግ በርካታ ቁስሎች አሉበት። ከውስንነታች ተላቅቀን፣ በሃጢአት ከወደቅንበት ተነስተን መቆም የምንችለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት ባስነሳው በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ነው። የብርሃነ ትንሳኤው ትርጉም እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ የሰጠው መልስም እንደገና መወለድ ያስፈልጋል የሚል ነው። ሕይወታችንን ለመንፈስ ቅዱስ አስልፎ የምንሰጠው ለምንድር ነው? ክርስቲያን የሚል መጠሪያ ተሰጥቶን የምንኖረው የክርስትና ሕይወት መንፈስ ቅዱስ ከሌለበት ወይም በሕይወታችን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ቦታ ካልተሰጠው የክርስትና ሕይወታችን ትርጉም የሌለው የስም ክርስትና ብቻ ነው። መንፈስ ቅዱስን የክርስትና ሕይወታችን መሪ ልናደርግ ይገባል። እርሱ ከእኛ ጋር በመሆን ዘወትር እንዲመራን መፍቀድ ያስፈልጋል። ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ምንም የለም፣ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በብርሃነ ትንሳኤው ዕለት ለሐዋርያቱ በመገለጥ እንደተናገረ ሁሉ ለእኛም በመገለጥ መንፈስ ቅዱስ ዘወትር አብሮአችሁ በመሆን፣ ለክርስትና ሕይወታችሁም መሪ ስለሚሆን “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ” ይለናል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስብከታቸውን በመቀጠል፣ የእግዚአብሔር አብ፣ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታ በሆነው በመንፈስ ቅዱስ ዘውትር ያልተመራ እና ያልታገዘ ሕይወት የክርስትና ሕይወት ሊሆን አይችልም።“ይህን ከልብ መማወቅ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ወይም በረከት መጠየቅ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ያለ መንፈስ ቅዱስ ድጋፍ እና መሪነት የምንጓዝ ከሆነ፣ በልባችን ውስጥ፣ በሕይወታችን ውስጥ ለመንፈስ ቅዱስ ቦታን የማንሰጥ ከሆነ ክርስቲያን መሆን አንችልም ” ብለዋል። ታዲያ የክርስትና ሕይወቴን ብቻዬ ሆኜ መጓዝ ካልቻልኩ ለመንፈስ ቅዱስ የምሰጠው ቦታ የቱ ነው በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ብለው የክርስትና ሕይወታችን መሪ በእርግጥም መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ለማወቅ የሚያስችለንን ጥበብ እግዚአብሔር እንዲሰጠን እርሱን መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል።          

 

30 April 2019, 16:18
ሁሉንም ያንብቡ >