ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የክርስቲያኖች ወደ ውድቀት መጓዝ የባዶነት ምልክት መሆኑን አስታወቁ።

አንዳንድ ክርስቲያኖች ካለማወቅ እና ካለመገንዘብ የተነሳ የሽንፈት ጎዳናን በመምረጥ ሰይጣን ለሚፈጽምባቸው ተንኮል ራሳቸውን ምቹ ስፍራ ያደርጋሉ ብለዋል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መጽናናትን እና ተስፋ ማድረግን ትተው የእግዚአብሔርን ተግሣጽ በመፍራት ከምንም ሳይሆኑ ባዶ ሕይወትን ለመኖር ይበቃሉ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 1 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት ደናግልና ምዕመናን በዕለቱ የተነበበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሠረት በማድረግ ስብከታቸውን አቅርበዋል። ከኦሪት ዘሁልቅ ምዕ. 21.4-9 ተውስዶ በተነበበው የመጀመሪያው ንባብ ላይ አስተንትኖ ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የድካም መንፈስ ተስፋን ሊያሳጣ እንደሚችል አስረድተዋል።

አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች የሽንፈት ጎዳናን በመምረጥ፣ ከዚህም የተነሳ ልባቸው በቅሬታ የተሞላ፣ ሕይወታቸውም እርካታ የሌለበት እንደሚሆን ገልጸው ይህ ደግሞ ለሰይጣን ጥቃት ምቹ አጋጣሚን እንደሚፈጥር አስረድተዋል። በኦሪት ዘሁልቅ፣ በምዕ. 21 ላይ የተጻፈው ታሪክ፣ በግብጽ ምድር በባርነት ይሰቃይ የነበረ ሕዝብ፣ ከዚያ ስቃይ ወጥቶ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀለት የነጻነት ምድር ለመድረስ ባደረገው ጉዞ ወቅት የተሰማውን ድካም የሚገልጽ እና በዚህ ድካም ምክንያት በልቡ የያዘው ተስፋ ቀስ በቀስ እንደተሟጠጠ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአስተንትኖአቸው ወቅት ገልጸው ይህን የመሰለ የድካም መንፈስ ተስፋችንን ከእኛ በማራቅ፣ ያሉንን መልካም በረከቶችን ሳይሆን መጥፎ ገጠመኞቻችንን ብቻ እንድንመለከት ያደርገናል ብለዋል።           

በሕይወታችን ውስጥ ባዶነት ሲሰማን፣ የክርስትና ሕይወታችንን በአግባቡ መጓዝ ያቅተናል። ከዚህ የተነሳ ወደ ጣዖት መሄድ፣ ወደ ማጉረምረም እና ወደ ሌሎች በርካታ ወደማያንጹን ነገሮች መሄድ እንጀምራለን ብለዋል። በውስጣችን የሚፈጠር የድካም መንፈስ ሕይወታችንን ያለ እርካታ እንድንኖር በማድረግ፣ ደስታን እንድናጣ ያደርገናል ብለዋል። 

አንዳንድ ክርስቲያኖች ካለማወቅ እና ካለመገንዘብ የተነሳ የሽንፈት ጎዳናን በመምረጥ ሰይጣን ለሚፈጽምባቸው ተንኮል ራሳቸውን ምቹ ስፍራ ያደርጋሉ ብለዋል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መጽናናትን እና ተስፋ ማድረግን፣ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ በመፍራት ከምንም ሳይሆኑ ባዶ ሕይወትን ለመኖር ይበቃሉ ብለዋል። ይህም የመሰለ ሕይወት የሚኖሩ ክርስቲያኖች ቁጥር በርካታ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው እነዚህ ክርስቲያኖች ታዲያ ዘወትር ቅሬታን በማሰማት፣ ትችቶችን በማብዛት እርካታ የሌለበትን ሕይወት ይኖራሉ ብለዋል። እኛ ክርስቲያኖች አድካሚ የክርስትና ሕይወትን መጓዝ አንመርጥም ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም የውድቀታችን ምልክት ነው ብለው ይህ ውድቀታችንም በምድረ ገነት ውስጥ ከነበረው፣ ከዚያ ፈታኝ ከሆነው ምድራዊ እባብ የሚመጣ ፈተና ነው ብለዋል። ሔዋንን ያታለላት እባብ እግዚአብሔር ካዘጋጀላቸው የተሟላ ህይወት ተነጥለው በብቸኝነት እንዲሞቱ መንገድ አዘጋጅቷል ብለዋል።

ተስፋን የማድረግ ፍርሃት፣

ሕይወታቸውን በሙሉ በማጉረምረም፣ ተስፋን ከማድረግ ይልቅ ተስፋን በመቁረጥ፣ የሞትን ሃይል አሸንፎ ለትንሳኤ በበቃው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ተስፋን ከማድረግ ይልቅ ሽንፈትን የመረጡ በርካታ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ተናግረዋል። የዕለቱን አስተንትኖአቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት በኦሪት ዘሁልቍ ምዕ. 21 ቁ. 4 ላይ ሕዝቡ በመንገድ ሳለ ትዕግስቱ አለቀ ተብሎ የተጻፈውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ክርስቲያኖች ትዕግስታቸው አልቋል፣ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ተግሳጽ ፈርተዋል ብለው እርካታን አጥተናል፣ በድካም ተጠምደናል፣ ሽንፈትን መርጠናልና እግዚአብሔር ከዚህ በሽታ ይፈውሰን በማለት የዕለቱን የወንጌል ስብከታቸውን አጠቃልለዋል።         

09 April 2019, 16:40
ሁሉንም ያንብቡ >