ፈልግ

2019.03.18 Messa Santa Marta 2019.03.18 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የደነደነ ልብ ታማኝነትን ከማጣት የተነሳ የአምላክን ስም ወደ ማጥፋት ይደርሳል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐሙስ መጋቢት 19 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት ደናግልና ምዕመናን በዕለቱ የተነበበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሠረት በማድረግ ስብከታቸውን አቅርበዋል። በስብከታቸው እንደገለጹት “የደነደነ ልብ ታማኝነትን ከማጣት የተነሳ የአምላክን ስም ለማጥፋት እና ለማጉደፍ ይደርሳል ብለው እግዚአብሔር የምሕረት አምላክ በመሆኑ ይቅርታን በማድረግ ሰዎችን ወደ እርሱ እንዲመለሱ ይጠራል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በዛሬው ዕለት ባሰሙት የወንጌል ስብከታቸው ልብን በመለወጥ መሐሪ ወደ ሆነው ጌታ ዘንድ መመለስ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል። በዕለቱ በተነበቡት የቅዱሳት መጽሐፍት ንባብ ላይ አስተንትኖን ያደረጉት ቅዱስነታቸው የእግዚአብሔርን ድምጽ ሳይሰማ ለቀናት ለወራት እና ለዓመታት የዘለቀ ልብ ውሃን ሳያገኝ ለረጅም ጊዜ እንደቆየ መሬት ደርቆ ይቀራል ብለዋል። ይህ የደነደነ ልብ የማያስደስተው ነገር ካጋጠመው ደግሞ የእግዚአብሔርን ስም ሊያጠፋ ይነሳል ብለው ከሉቃ. 11, 14 - 23 ተውስዶ በተነበበው የወንጌል ክፍል “ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ እኔን ይቃወማል፣ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ይበትናል” (ሉቃ. 11፤23) ማለቱን አስታውሰዋል።  

ታማኝነትን የማጣት አደጋ እንዳያጋጥም፣

ዜናን በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ በየቀኑ እንሰማለን። የመንደራችንን ወሬ እንከታተላለን። እግዚአብሔርም ጆሮአችንን ወደ እርሱ በማድረግ ቃሉን እንድናዳምጥ እና ልባችንን ሳናደነድን በፍቅር ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይጠይቀናል። በትንቢተ ኤርሚያስ ምዕ. 7፤23-28 ተወስዶ የተነበበው የመጀመሪያው ንባብ፣ እግዚአብሔር የሕዝቡን ቸልተኝነት የገለጸበት፣ የእርሱን ቃል ከማዳመጥ ወደ ኋላ ያለበትን ሁኔት የሚናገር እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸው በትንቢተ ኤርሚያስ ላይ የተገለጸው ታሪክ እግዚአብሔር ቅሬታውን የገለጠበት እንደነበር አስረድተው ሕዝቡ ድምጹን እንዲሰማ እግዚአብሔር ሲያሳስብ ቃል የተገባላቸውን የሚያገኙት ድምጹን የሰሙ እንደሆነ፣ እርሱ ብቻ አምላካቸው እንደሆነ፣ እነርሱብ የእርሱ ሕዝብ እንደሆኑ ነግሮአቸው ነበር። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ሕዝቡ እግዚአብሔርን ሊያደምጡት አለመፈለጋቸውን፣ ጆሮአቸውን እንደደፈኑ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እግዚአብሔር ምን እንደሚናገረን ማድመጥ እና ለማድመጥም ዝግጁዎች መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። ከግብጽ አገር ባርነት ከወጣበት ጊዜ አንስቶ ሕዝቡ ድምጹን እንዲሰማ እግዚአብሔር ነቢያትን እንደተጠቀመ የገለጹት ቅዱስነታቸው ያም ሆኖ ሕዝቡ ከበፊቱ የባሰ ልቡን እንዳደነደነ፣ ጆሮውንም እንደደፈነ ገልጸዋል።

ታምኝነትን ያጎደለ ሕዝብ የታማኝነትን ትርጉም እንዳጣ ይቆጠራል ያሉት ቅዱስነታቸው ዛሬ ቤተክርስቲያን እያንዳንዳችንን “ለእግዚአብሔር ያለኝን ታማኝነት አጥቼአለሁ ወይ”? ብለን እንድንጠይቅ ታሳስበናለች ብለዋል። በየእሑዱ የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት አልካፈልም፣ ማሳየት ያለብኝን ታማኝነት በመነፈግ፣ ልቤን በማደንደን፣ ጆሮዬን በመድፈን ለእግዚአብሔር እድልን እና ቦታን ሳልሰጥ ቀርቼ፣ አንድ ወይም ሁለት ነገር ብቻ እንደ እርሱ ፈቃድ በማድረግ የተቀሩትን እንዳሻኝ አድርጌ ከሆነ በማለት ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል። የአብይ ጾም ጊዜ እነዚህን እና ሌሎችንም ጥያቄዎች አንስተን ራሳችንን እንድንጠይቅ፣ ልባችንንም ለመለወጥ የሚያግዝ ወቅት እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስገንዝበዋል። እግዚአብሔርን ማድመጥ እንደሚያስፈልግ ቤተክርስቲያን ምእመናኖቿን በሙሉ ዘወትር ታሳስባለች ብለዋል። በተጨማሪም ልብን ማደንደን እንደሌለብን፣ በልበ ደንዳናነት የሚኖር ሰው፣ እግዚአብሔርን የማያደምጥ ሰው፣  ለእግዚአብሔር ያለውን ታማኝነት ከማጉደሉ በላይ ስሙን ወደ ማጥፋት ይሄዳል ብለዋል።

ኢየሱስ “ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ እኔን ይቃወማል፣ ከእኔም ጋር የምይሰበስብ ይበትናል”

ኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝቡን ለማግባባት ይፈልጋል። ነገር ግን ሕዝቡ የማይሰማው ከሆነ፣ ነቢዩ ኤርሚያስ በትንቢቱ እንደተናገረው ሁሉ ኢየሱስም ለተከታዮቹ “ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ እኔን ይቃወማል፣ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ይበትናል” ማለቱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት መጠን ለመለካት እንደሚሞክሩ ገልጸው ይህን ከማድረግ ይልቅ ከእርሱ ጋር ከሆኑ ሙሉ በሙሉ ከእርሱ ጋር መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የእለቱን ስብከተ ወንጌልን ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት ሁላችንም ወደ እግዚአብሔር እንድንመለስ ተጠርተናል ብለው ልብችንን የምናደነድን፣ ጆሮአችንን የምንደፍን ቢሆንም እግዚአብሔር የምሕረት አምላክ በመሆኑ ወደ እርሱ እንድንመለስ ያጋብዘናል ብለዋል።

28 March 2019, 17:00
ሁሉንም ያንብቡ >