ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የመከራን እና የስቃይ ዋጋ እየከፈሉ ያሉት አቅመ ደካሞች ናቸው”።

በዓለማች ውስጥ በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን መከራ፣ ስቃይ እና ሞት በመመልከት ይህ ስቃይ ለሚደርስባቸው ሰዎች በመራራት የምናለቅስበትን ልብ እንዲሰጠን እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት፣ ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ማሳረጋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው የጸሎት ሥነ ስርዓት ላይ ለተገኙት ካህናት፣ ደናግል እና ምዕመናን ባሰሙት የቅዱሳት መጻሕፍት አስተንትኖ፣ እግዚአብሔር በእውነተኛ ፍቅሩ እንደሚወደን ገልጸው እኛም በዓለማች ውስጥ በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን መከራ፣ ስቃይ እና ሞት በመመልከት፣ ይህ ስቃይ ለሚደርስባቸው ሰዎች ራርተን የምናለቅስበትን ልብ እንዲሰጠን እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል።      

በዕለቱ በተነበበው የመጀመሪያ ንባብ፣ ከኦሪት ዘፍጥረት በምዕ. 6፣ 5-8 እና ምዕ. 7፣ 1-5 እንዲሁም በቁጥ. 10 ላይ የተጻፈውን ታሪክ ዛሬ በዘመናችን ከሚከሰቱ የመከራ ሕይወት ጋር በማመሳሰል ባቀረቡት ስብከታቸው፣ ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ስቃይ በማስታወስ በርካታ የሚራቡ ሕጻናት፣ ያለ ወላጅ ቤተሰብ የቀሩ ሕጻናት፣ አቅመ ደካማ የሆኑ እና ያለ ረዳት የቀሩ፣ በድህነት ሕይወት የሚገኙ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ለሚከሰቱት ጥፋቶች እና ቀውሶች በሙሉ ዋጋ የሚከፍሉ እነዚህ ሰዎች መሆናቸውን አስረድተው፣ የእግዚአብሔርን የሚመስል መለኮታዊ የርህራሄ እና የእውነተኛ ፍቅር ልብ እንድናገኝ መለመን ያስፈልጋል ብለዋል።

እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይራራል፣

በእለቱ ከቀረበው የመጀመሪያ ንባብ ሁለት ሃሳቦችን መንደርደሪያ ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በመጀመሪያው ሃሳብ እግዚአብሔር በሰው ልጆች ክፋት የተነሳ እንደሚሰቃይ፣ ስቃዩንም በሃሳብ ወይም በቃል ሳይሆን ራሱን ለስቃይ አሳልፎ በመስጠት፣ ከሚሰቃዩት ጋር በመሰቃየት በተግባር እንደገልጸ ገልጸው ይህም የእግዚአብሔር አባታዊ ፍቅር የተገለጸበት ምስጢር ነው ብለዋል።

እግዚአብሔር ይራራል፣ እርሱ ይወደናል፣ ፍቅር በሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት የሚገለጥበት መንገድ ነው። ነገር ግን በተግባር፣ በሥራ የሚገለጥ መሆን ይኖርበታል። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው ለድሎት ሳይሆን ስቃይ የበዛበትን፣ መስዋዕትነትም ያለበት የፍቅር መንገድን ሊያሳየን ነው። ስቃይን በመቅመስ በተግባር የገለጠልን የፍቅር መንገድ ለእኛ በመራራት፣ እውነተኛ ፍቅርን ለመመስከር ብሎ ነው። የእኛ አምላክ የፍቅር አምላክ ነው፣ የሚያፈቅረንም ፍቅሩን በተግባር በመግለጽ እንጂ በሃሳብ አይደለም። የሚቀርበንም በፍቅር ነው፣ የሚገስጸን እንደ መልካም አባት በፍቅር ነው፣ ለራሳችን ከእኛ በላይ እርሱ ይጨነቅልናል

የዘመናችን መከራ ካለፉት ከብሉይ ኪዳን ዘመን መከራ የተለየ አይደለም፣

እግዚአብሔር ፍቅሩን በስቃይ ከገለጠልን እኛም በእርሱ ፊት ሆነን ፍቅራችንን በሃሳብ ሳይሆን በተግባር መግለጽ መቻል አለብን ብለዋል። ይህን እውነት መረዳት ይኖርብናል ብለው አሁን የምንኖርበት ዘመን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከብሉይ ኪዳን የስቃይ ዘመን የተለየ አይደለም ብለው በዓለማችን የሕጻናት ስቃይ፣ የድህነት ስቃይ፣ የረሃብ ስቃይ፣ የጦርነት ስቃይ፣ የግርፋት ስቃይ በስፋት መኖሩን አስታውሰዋል። በጦርነት ሕይወታቸውን የሚያጡ በርካታ ሰዎች የጥፋት መሣሪያ ስለሚጣልባቸው ነው ብለዋል።

“ዘመናችን ከብሉይ ኪዳን የጥፋት ዘመን የተሻለ ነው ብዬ አላስብም። በዓለማችን ውስጥ በሰዎች ላይ የሚደርሱ አደጋዎች ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው። የአደጋው ሰለባዎችም እንደዚሁ። ከአደጋው ራሳቸውን ማዳን ወይም መከላከል የማይችሉ ሕጻናትን እና አቅመ ደካማ የሆኑ ድሆችን እናስብ። በረሃብ የሚሰቃዩ ሕጻናት፣ መሠረታዊ ትምህርትን የማያገኙ ሕጻናት፣ በጦርነት ወላጆቻቸውን ያጡ፣ በጦርነት ምክንያት ሰላማዊ ሕይወት የማይኖሩ ሕጻናት ቁጥር እናስብ። በለጋ የሕጻንነት ዕድሜአቸው ለጦርነት የሚመለመሉት ሕጻናትን ቁጥር እናስብ”።

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ማልቀስ፣

በዓለማች ውስጥ በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን መከራ፣ ስቃይ እና ሞት በመመልከት ይህ ስቃይ ለሚደርስባቸው ሰዎች በመራራት  የምናለቅስበትን ልብ እንዲሰጠን እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ልጅ አባቱን እንደሚወድ፣ አባትም ልጁን እንደሚወድ፣ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ፍቅር እንዲኖረን፣ መለኮታዊ ፍቅር እንዲኖረን ያስፈልጋል ብለዋል። 

“ራሳቸውን ከአደጋ እና ከጥፋት መከላከል የማይችሉ ሕጻናት፣ አቅመ ደካሞች፣ በድህነት የሚሰቃዩ ሰዎች በመክፈል ለይ የሚገኙበት ከባድ መከራ በዓለማች ውስጥ ይገኛል። በእነዚህ ሰዎች ስቃይ ምክንያት እግዚአብሔር እጅግ አዝኗል። እኛም ወደ እርሱ ቀርበን በጸሎት እንጠይቀው፣ የሐዘኑም ተካፋዮች እንሁን። የዚህ ሁሉ ስቃይ እና መከራ ምንጭ፣ መልካም የሆነውን የእግዚአብሔር ፍጥረት ሊያጠፋ የተነሳው ክፉ መንፈስ እርሱም ሰይጣን መሆኑን በመገንዘብ በጸሎት ከእግዚአብሔር በምናገኘው ሃይል በመታገዝ ልናሸንፈው ይገባል” ብለዋል።    

19 February 2019, 16:35
ሁሉንም ያንብቡ >