ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ  በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት   (ANSA)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የታመመው፣ የተራበው እና የታሰረው ወንድማችን የት አለ? ብለን መጠየቅ ይገባል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸሶስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ለሚሰበሰቡ ቀሳውስት፣ ደናግላን እና ምዕመናን መስዋዕተ ቅዳሴ እንደ ሚያሳርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት በዛሬው እለት ማለትም በየካቲት 11/2011 ዓ.ም ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙት ስብከት መሰረቱን በእለቱ ከኦሪት ዘፍጥረት 4፡1-15 ተወስዶ በተነበበው እና አዳም እና ሄዋን ቃየን እና አቤል የሚባሉ ሁለት ልጆች መውለዳቸውን፣ ቃየን ውንድሙን በቅንዐት መንፈስ ተነሳስቶ መግደሉን በሚተርከው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ ስብከት እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “የታመመው፣ የተራበው፣ እና የታሰረው ወንድማችን በየተኛው የልባችን ክፍል ውስጥ እንደ ሚገኝ እግዚኣብሔር ሁላችንንም ይጠይቀናል” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

“የት ነህ ያለኸው? ወንድምህስ የት ነው ያለው? እነዚህን ጥያቄዎች እግዚኣብሔር ለአዳም እና ለቃየን ያቀረባቸው ጥያቄዎች መሆናቸውን” በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች ዛሬም ቢሆን እግዚኣብሔር ለእኛ እንደ ሚያቀርብ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

“እግዚኣብሔር በአንድ ወቅት ለቃየን አቅርቦት የነበረውን ዓይነት ጥያቄ ዛሬም በተመሳሳይ መልክ “ወንድምህ የተ ነው ያለው?” በማለት ለእኛ ጥያቄ እንደ ሚያቀርብ የገለጹት ቅዱስነታቸው ለዚህ ጥያቄ እያንዳንዳችን የግል ምላሽ መስጠት እንደ ሚገባ ጨምረው ገልጸው በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ 25 ላይ እንደ ተጠቀሰው “ወንድሜ የት ነው ያለው፣ ታሙዋል፣ ተርቡዋል፣ ወይስ ታስሩዋል” በማለት እለታዊ በሆነ መልኩ እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳት እንደ ሚገባ ጨምረው ገልጸዋል።

ይህንን የመሳሰሉ ለእኛ በጣም “ምቹ ያልሆኑ እና አፋጣኝ የሆነ ምላሽ የሚጠይቁ” ጥያቄዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ወስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሰው እንደ ሚገኙ በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እግዚኣብሔር ቃየንን “ወንድምህ የት አለ?” በማለት ቃዬንን ጠይቆ እንደ ነበረ ገልጸው ቃየን በበኩሉ በሰጠው ምላሽ ራሱን ለመከላከል በማሰብ ትንሽ ግራ የተጋባ የሚመስል መልስ ስጥቶ እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል። “እኔ በወንድሜ ሕይወት ውስጥ ምን አገባኝ?” እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ ወይ? እኔን ምንም አይመለከተኝም” በማለት ነበር ቃየን እግዚኣብሔር ላቀረበለት ጥያቄ ራሱን ነጻ ለማድረግ የወሰነው በዚሁ መልክ ነበር” ብለዋል።

ምቾት የማይሰጡ ጥያቄዎች

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ውስጥ ምቾት የማይሰጡ ጥያቄዎችን ብዙን ጊዜ ጴጥሮስን ጠይቆት እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ለምሳሌም “ትወደኛለህን?” በማለት ኢየሱስ ለጴጥሮስ 3 ጊዜ ያህል ጥያቄ አቅርቦለት እንደ ነበረ ገልጸው ጴጥሮስም ምን ብሎ መመለስ እንደ ነበረበት ግራ ተጋብቶ እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በተመሳሳይ መልኩም ለደቀ-መዛሙርቱ “ ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል” ብሎ ጥያቄ አቅርቦ እንደ ነበረም ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ጨምረው ገለጸዋል። እነርሱም “ከነቢያት አንዱ፣ መጥምቁ ዮሐንስ . . .” በማለት ግራ ተጋብተው መመለሳቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ነገር ግን “እናንተ እኔን ማን ትሉኛላችሁ? ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ደግሞ ይበልጡኑ ግራ መጋባታቸውን ቅዱሰነታቸው አስታወሰዋል። በተመሳሳይ መልኩም ዛሬ በሰማነው የመጀመሪያ ምንባብ ውስጥ (ኦ.ዘፍጥረት 4፡1-15) እግዚኣብሔር ቃየንን “ወንድምህ የት አለ?” በማለት ብዙ ምቾት የማይሰጥ ጥያቄ ጠይቆት እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ምንም እንኳን ለእነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች መልስ ማቅረብ ብንችልም በድፍረት ግን መናገር በጣም ይከብደናል ብለዋል።

ግራ የተጋባ መልስ

“ወንድምህ የት ነው ያለው?” ተብሎ ለሚቅርብልን ጥያቄ እያንዳንዳችን ግራ የተጋባ መልስ ልንሰጥ እንችል ይሆናል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በኢየሱስ እና በእግዚአብሔር ፊት በጽናት ለመቆም ያስችለን ዘንድ “የታመመው ወንድምህ ይት ነው ያለው፣ የተራበው ወንድምህ የት ነው ያለው? የታሰረው ወንድምህ የት ነው ያለው? በፍትህ እጦት ምክንያት እየተንገላታ የሚገኘው ወንድምህ የት ነው ያለው? ለሚሉት ጥያቄዎች ግራ ሳንጋባ በጽናት መልስ መስጠት ይኖርብናል” ለእነዚህ ጥያቄዎች በአግባቡ መልስ መስጠት እንችል ዘንድ እግዚኣብሔር ሁላችንንም ይርዳን ካሉ በኋላ ስብከታቸውን አጠናቀዋል። 

Photogallery

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት
18 February 2019, 18:47
ሁሉንም ያንብቡ >