ፈልግ

ር.ዕ.ሊ ጳጳስት ፍራንቸስኮስ  በቅ. ማርታ የጸሎት ቤት ር.ዕ.ሊ ጳጳስት ፍራንቸስኮስ በቅ. ማርታ የጸሎት ቤት   (Vatican Media)

ር.ዕ.ሊ ጳጳስት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በ2018 ዓ.ም በቅ. ማርታ የጸሎት ቤት ያደረጉዋቸው ስብከቶች

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዘንድ በቅርቡ በተጠናቀቀው የ2018 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉዋቸው መስዋዕተ ቅዳሴዎች ላይ ያሰሙዋቸውን ስብከቶች ዋና ዋናዎቹን እንደ ሚከተለው አጠር አጠር አድርገን እናቀርብላችኋለን ተከታተሉን።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ሁለት ዓይነት ሕይወት መኖር ተገቢ አይደለም
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 1/2010 ዓ.ም. ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት ሁለት ዓይነት ሕይወት እየኖሩ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን እረኞች ቤተ ክርስቲያንን እያቆሰሉዋት እንደ ሚገኙ ገልጸው የእዚህን ዓይነት ተግባር በመፈጸም ላይ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን እረኞች ከእዚህ ድርጊታቸው ተቆጥበው በጸሎት እና በርኅራኄ መንፈስ ሰዎች ከእግዚኣብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ አጠናክረው እንዲሄዱ ማበረታታት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በወቅቱ ሕብረት፣ ቅርበት እና ተመጣጣኝ የሆነ ሕይወት መኖር በሚሉ ሦስት ጭብጦች ዙርያ ላይ ባተኮረው ስብከታቸው ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሦስት መገለጫዎች የቤተ ክርስቲያን እረኞ ለሆኑ ሰዎች የተሰጡ ሦስት ባህሪያት፣ የቤተ ክርስቲያን እረኛ የሆነ ሰው እነዚህን ባህሪያት በመላበስ እና መንፈሳዊ ስልጣኑን በመጠቀም ሕዝቡን ወደ እግዚኣብሔር መመለስ ይኖርበታል ማለታቸው ይታወሳል።
ስለሞታችን እለት ማሰብ ተገቢ ነው
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 24/20101 ዓ.ም. ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “ስለ ሞት ማሰብ እኛ የጊዜያት ጌታ እንዳልሆንን ጠንቅቀን እንድንረዳ በማድረግ ግራ ከመጋባት መንፈስ ነጻ ያወጣናል” ማለታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን “ሞት የማይቀር እዳ ነው፣ ሞት ውርሳችን ነው፣ ሞት መታሰቢያችን ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
"እኛ ዘለዓለማዊ ወይም ዘላቂ የሆንን ፍጡራን አይደለንም፣ እኛ በጊዜ ውስጥ እየተጓዝን የምንገኝ ሰዎች ነን፣ በጊዜ ውስጥ የምንጀምር እና በጊዜ ውስጥ የምንጠናቀቅ ሰዎች መሆናችንን በፍጹም መዘንጋት የለብንም” ያሉት ቅዱስነታቸው በእለቱ በላቲን ስረዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት 1 መጽሐፈ ነግሥት 2 ተወስዶ በተነበበው እና የንጉሥ ዳዊትን ሞት በሚያመለክተው ታሪክ ላይ ተመርኩዘው ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “የጊዜን ጥቅም መረዳት የሚያስችለንን ጸጋ እግዚኣብሔር እንዲሰጠን መጸለይ እንደ ሚገብን ገልጸው ይህም ጸጋ ራሳችንን በራሳችን በመቆለፍ የራሳችን እስረኞች እንዳንሆን ይረዳናል” ማለታቸው ይታወሳል።
“ሞት ሁላችንንም የሚነካ ሐቅ ነው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ማት ሊዘገይ ይችል ይሆናል፣ ነገር ግን ዛሬ ይሁን ነገ ለሁላችን የማይቀር ሐቅ መሆኑን ማስታወስ ግን ያስፈልጋል” ያሉት ቅዱስነታቸው ይህንን በተመለከተ የሚከተለውን ብለው ነበር. . .

የሕይወታችን ጌቶች ሆነን እንዲሰማን የሚያደርግ ፈተና ብዙን ጊዜ ያጋጥመናል፣ በእዚህም ምክንያት መጭው ጊዜ በደንብ ስለማይታያቸው ዝም ብለው በራስ ወዳደነት መንፈስ ውስጥ ሲመላለሱ ይኖራሉ። የእዚህ ዓይነቱ ኑሮ ደግሞ ሁላችንም እንደ ምናውቀው በሞት ይጠናቀቃል። ለእዚህም ነው ብዙን ጊዜ ቤተክርስትያን በሞት ዙሪያ የተለያዩ ዓይነት አስተምህሮችን የምትሰጠው፣ እኛ የሞት ጊዜያችንን በሚገባ በማሰብ በጥንቃቄ መኖር እንዳለብን ቤተክርስትያን የምታስተምረን በእዚሁ ምክንያት ነው።

ትዕግስት ሽነፈት አይደለም
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በየካቲት 5/2010 ዓ.ም. በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “ታጋሽ መሆን የምያስችለንን ጸጋ ጌታ ይሰጠን ዘንድ ልንጠይቀው ይገባል” ካሉ በኃላ በተለይም ደግሞ በመካከለኛው ምስርቅ የሚገኙ ክርስቲያኖች በእየለቱ የሚገጥማቸውን ችግር፣ መከራ እና ስደት በትዕግስ ይሸከሙ ዘንድ ልንጸልይላቸው ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።
“ወንድሞቼ ሆይ፤ ልዩ ልዩ መከራ ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት፤ ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ” በሚለው በወቅቱ ከቅዱስ ሐዋሪያው ያዕቆብ መልዕክት 1: 2,3 ላይ ተወስዶ በተነበበው መልእክት ላይ ተመርኩዘው የተናገሩት ቅዱስነታቸው ትዕግስት ሽነፈት አይደለም ማለታቸው ይታወሳል።
“ነገር ግን በሕይወታችን እና በፈተናዎች ውስጥ በትዕግስት መጠበቅ ማለት ምን ማለት ነው? በማለት ጥያቄን በማንሳት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህንን በሚገባ መረዳት ቀላል የሆነ ነገር አይደለም ካሉ በኋላ “በክርስትያናዊ አስተሳሰብ መታገስ ማለት መሸነፍ ማለት ሳይሆን ባለንበት ከመቆም ይልቅ ወደ ፊት እንድንጓዝ የሚረዳን ሰነ-ምግባር ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
“መንገድ በምንጓዝበት ወቅት ሁል ጊዜ መልካም የሆኑ ነገሮች ብቻ ይገጥመናል ብለን ማሰብ ያስቸግራል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “የሕይወት ጉዞዋችን ምን ይሁን ምን ቀጣይነት ባለው መልኩ ወደፊት እንድንጓዝ የሚረዳን በትዕግስት መጓዝ ነው፣ በእዚህ ረገድ ወላጆቻችንን ማስታወስ ተገቢ እንደ ሆነ ጠቅሰው ልጆች በነበርንበት ወቅት ስንታመም፣ ስንወድቅ፣ ስንነሳ በትዕግስት ከእኛ ጋር በመሆን፣ በፍቅር አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ እንድንደርስ ያበቁን በትዕግስ አማካይነት እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ጨምረው መግለጻቸው ይታወሳል።
ክርስቲያናዊ ትዕግስት ሽንፈት አይደለም
“ክርስቲያናዊ ትዕግስት ሽንፈት አለመሆኑን” በድጋሚ በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ታጋሽ ያልሆነ ሰው ግን የሰው ልጅ ወሰን እንዳለው የማይገነዘብ ሰው እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው መግለጻቸው ይታወሳል። “ትዕግስት” የሚለውን ቃል ስር መሰረቱን ለመረዳት መዝገበ ቃላትን ብናገላብጥ ኃላፊነት መውሰድ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ያሰማል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ከመከራ መሸሽ ማለት ሳይሆን መከራን ተሸክሞ መጓዝ ማለት እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
“ትዕግስት ማለት የራሳችንን ችግሮች ተሸክሞ መጓዝ ማለት ነው እንጂ ችግሮቻችንን ሌላ ሰው እንዲሸከም ማድረግ ማለት አይደለም” ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ የእኔ ችግር ነው፣ የራሴን ችግር መሸከም ያልብኝ እኔው ራሴ ነኝ ማለት እንደ ሚኖርብን ቅዱስነታቸው መግለጻቸው ያትወሳል።
“ትዕግሥት ማለት እኛ ሁሉንም ነገሮች የመፈጸም ብቃት እንደ ሌለን መገንዘብ ማለት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው ሰዎች በመሆናችን የተነሳ በሕይወት ውስጥ የሚከሰቱትን ነገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ የመጋፈጥ አቅም እንደ ሌለን፣ ውስን ሰዎች መሆናችንን መገንዘብ ያስፈልጋል፣ ያሉት ቅዱስነታቸው ውስን መሆናችንን ተገንዝበን ከሚገጥሙን ችግራች ጋር በትዕግስ መደራደር ያስፈልጋል ማለታቸውም ይታወሳል።
ምስጢረ ንስሐ ይቅርታን ያስገኛል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 21/2010 ዓ.ም ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት ገለጹት “ምስጢረ ንስሐ በምንገባበት ወቅት የሚጠብቀን ማስፈራሪያ ሳይሆን ይቅርታ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
ሁላችንም መጥፎ የሆነ የሕይወት መስመራችንን እንድንቀይር ጌታ እኛን ከመጥራት መቼም ቢሆን ታክቶ አያውቅም ያሉት ቅዱስነታቸው በተቃራኒው ቀስ በቀስ ወደ እርሱ እንድንመለስ በሚጣፍጥ መልኩ ወደ እርሱ እንድንምለስ ያደርገናል ማለታቸው ይታወሳል።
በእለቱ በቀዳሚነት ከትንቢተ ኢሳያስ ተወስዶ በተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ በተገለጸው፣ ነብዩ ኢሳያስ የሰው ልጆች ሁሉ የሕይወት መስመራቸውን እንዲቀይሩ፣ ወደ እግዚኣብሔር እንዲመለሱ እግዚኣብሔር ያቀረበላቸውን ጥሪ የሰው ልጆች ሁሉ እንዲቀበሉ በሚያሳስበው የትንቢት ቃል ላይ ተመስርተው ስብከተቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በአጥአታችን የተነሳ ኢየሱስ እኛን ከመንቀፍ ይልቅ ለየት ባለ ሁኔታ ጣፋጭ በሆነ መልኩ ወደ እርሱ እንመለስ ዘንድ ይጠራናል፣ መንገዱንም ያሳየናል ካሉ በኃላ እግዚኣብሔር በነቢዩ ኢሳያስ አማካይነት “ኑ እና እንወያይ” በማለት ለሰዶም እና ለጎሞራ ሕዝቦች ተናግሮ እንደ ነበረ መግለጻቸው ይታወሳል። ክፉ የሆነውን የሕይወት አካሄድ በመተው፣ መልካሙን የሕይወት አቅጣጫ ይከተሉ ዘንድ በትህትና ለሕዝቡ ጥያቄ ማቅረቡን ቅዱስነታቸው በዋቢነት ገለጸዋል። ይህንንም በተመለከተ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለው ነበር. . .

ኑና እንዋቀስ”ይላል እግዚአብሔር” አንድ አባት ወጣት ልጁ ጥፋት በሚያጠፋበት ወቅት ይገስጸዋል እንጂ ዱላ አንስቶ ሊመታው አይፈልግም። ምክንያቱም ዱላ ልጁን ይበልጥ እንዲሸሽ ያደርገዋል እንጂ በአባቱ ላይ ያለውን መተማመን አይጨምርለትም። በተመሳሳይ መልኩ እግዚኣብሔር እኛን ልጆቹን “ኑና እነወቃቀስ፣ ኑና እንወያይ፣ አትፍሩ ኑ ወደ እኔ እኔ በዱላ አላስፈራራችሁም” ይለናል እንጂ እንድንፈራ አያደርገንም። “ኃጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል” ይለናል እንጂ እግዚኣብሔር በፍጹም እኛን አያስፈራራንም።

አንድ አበት ወጣት የሆነውን ልጁን ወደ መልካም ጎዳና እንዲመለስ እንደ ሚገስጸው ሁሉ፣ ኢየሱስም በተመሳሳይ መልኩ በእርሱ ተማምነን በምሕረቱ ታግዘን ልባችንን እንድንቀይር በትዕግስት ይጠባበቀናል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው፣ የዜኪዮስን እና ሌዊ በመባል ይታወቅ የነበረው ቀራጭ የነበረው ማቴዎስ ታሪክን በዋቢነት መመልከት እንደ ሚችላ ገልጸው ኢየሱስ በተመሳሳይ መልኩ እኛ ሕይወታችንን እንድንቀይር፣ ቀስ በቀስ ወደ እርሱ እንድንመለስ ይረዳናል ማለታቸው ይታወሳል።
በዐብይ ጾም ወቅት መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በየካቲት 27/2010 ዓ.ም ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን አስተምህሮ በመከተል በዐብይ ጾም ወቅት መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ ትጠይቀናለች ማለታቸው ይታወሳል።
“ቤተ ክርስቲያን በዐብይ ጾም ወቅት መልካም ተግባራትን እንድናከናውን ያግዘን ዘንድ ጾም መጾም፣ መጽዋዕት መመጽወት እና ንስሐ መግባት አስፈላጊ እንደ ሆነ ትመክረናለች፣ እነዚህም ሦስቱ ተግባራት ደግሞ በጎ የሆኑ ተግባራትን እንድናከናውን ያነሳሱናል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በጎ የሚባሉ ተግባራትን በተመለከተ በማቴዎስ ወንጌል 25 የተጠቀሱትን የአንድ ክርስቲያን መገለጫ ባህሪይ የሆኑትን በጎ ተግባራት ማከናወን ይኖርብናል ማለታቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን በዐብይ ጾም ወቅት የስሜት ለውጥ እንድናደርግ ጥሪ እንደ ምታቀርብልን በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በዐብይ ጾም ወቅት ስሜቶቻችንን ወደ መልካም ስሜት ልንቀይር ይገባል፣ የደጉ ሳምራዊ አብነት በመከተል በርኅራኄ የተሞላ ስሜት ሊኖረን ይገባል፣ ስሜቶቻችን በሙሉ የክርስቲያን ስሜት መገለጫ ሊሆኑም ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።
በዐብይ ጾም ወቅት የአስተሰሰብ ዘይቤያችንን በመቀየር፣ የእኔ አስተሳሰብ ምንጩ ምንድነው? በማለት ራሳችንን በመጠየቅ የአስተሳሰባችን ምንጭ ምን እንደ ሆነ ለይተን በማወቅ በእግዚኣብሔር መንፈስ እና በክርስቲያናዊ እሴቶች ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ይኑረን ወይም አይኑረን መርምረን በማወቅ መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ ይረዳን ዘንድ የእግዚኣብሔርን ጸጋ በመማጸን የአስተሰብ ለውጥ ለማምጣት ጸጋውን እንዲሰጠን የምንማጸንበት ወቅት ሊሆን ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።
ጸሎት በትዕግስት እና በብርታት ሊደረግ ይገባል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በመጋቢት 05/2010 ዓ.ም. ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “ማንኛው ጸሎት በትዕግስት እና በብርታት ሊደረግ ይገባል” ያሉት ቅዱስነታቸው በወቅቱ በቀዳሚነት ከኦ.ዘ. 32:7-14 ተወስዶ በተነበበው እና በእግዚኣብሔር እና በሙሴ መካከል ተደርጎ በነበረው ውይይት ውስጥ ጸሎት ያለውን ኃይል በሚያሳየው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ አስተንትኖ እንደ ነበረ መዘገባችን ይታወሳል።
“ብርታት እና ትዕግስት” በነጻነት እና በልጅነት መንፈስ ወደ እግዚኣብሔር የሚደረግ ጸሎት ልዩ የመገለጫ ባህሪያት ሊሆኑ እንደ ሚገባ በመገልጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህንንም ባህሪ በእለቱ በቀዳሚነት በተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ በተጠቀሰው በእግዚኣብሔር እና በሙሴ መካከል ተደርጎ በነበረው ውይይት ውስጥ፣ በወቅቱ የነበረው የእስራሄል ሕዝብ በእግዚኣብሔር ላይ የፈጸሙትን የክህደት አመክንዮአዊ ዝንባሌን ውጤቱ ቀና እንደ ማይሆኑ ሙሴ በሚገባ ተረድቶት እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው ተጋረው እንደ ነበረ ይታወሳል።
"የሕያው አምላክ ምስልን ትተው የወርቅ ጥጃ ሰርተው እንዲሰግዱ" ሕዝቡን የሚያስገድዱ ሰዎችን የጌታን ምስል ለማጥፋት የፈለጉ ሰዎች በመሆናቸው የተነሳ ሙሴ አውግዙዋቸው እንደ ነበረ የገለጹት ቅዱስነታቸው ሙሴ የመከራከሪያ ሐሳቦችን ይዞ በመቅረብ “እግዚኣብሔር አምላክ ከግብጽ ባርነት እንዴት እንዳወጣቸው፣ ለአብራሃም እና ለያዕቆብ ለገባው ቃል ታማኝ መሆኑን ግልጾላቸው እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
ሙሴ ከእግዚኣብሔር ጋር ፊት ለፊት በተገናኘበት ወቅት ምንም እንኳን በወቅቱ የነበረው የእስራኤል ሕዝብ እግዚኣብሔር ያደርገላቸውን መልካም ነገር ዘንግተው፣ እግዚኣብሔርን በመካድ የጣዖት ምስል ማምለክ የጀመሩ ቢሆንም ቅሉ ሙሴ ግን እግዚኣብሔር በቁጣ በሕዝቡ ላይ እንዳይነሳ በመማጸኑ የተነሳ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር በመግለጹ የተነሳ የነብይነት ተሳትፎው ግልጽ በሆኖ መልኩ ይታይ እንደ ነበረ የገለጹት ቅዱስነታቸው በወቅቱ ሙሴ አልዋሸም ነበር፣ እውነቱን ለመናገር አልፈራም ነበር፣ ሕሊናውን ለመሸጥ አልፈለገም ነበር ማለታቸው ይታወሳል። “ይህ የሙሴ ተግባር እግዚኣብሔርን እጅግ በጣም አስደስቶት እንደ ነበረ የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህንንም አጠር ባለ መልኩ “እግዚኣብሔር አንድ ነፍስ ወይም አንድ ሰው አንድ ነገር ከእግዚኣብሔር ፈልጎ በተደጋጋሚ ወደ እግዚኣብሔር ጸሎቱን ቢያቀርብ እግዚኣብሔር እንደ ሚራራለት ያሳያል” ማለታቸው ይታወሳል። ይህንን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለው ነበር. .
“አንድ የምልጃ ጸሎት ለማድረግ ሁለት ነገሮች ያስፈልጉናል፣ አንደኛው እና በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ጽናት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ትዕግስት ነው። እኔ የምለምነውን አንድ ነገር ጌታ እንዲፈጽምልኝ የምፈልግ ከሆንኩኝ ወደ ፊት በጽናት በመጓዝ በተደጋጋሚ በሩን ማንኳኳት ይኖርብኛል፣ የእግዛኢብሔርን ልብ ማንኳኳት ይኖርብኛል፣ ምክንያቱም የምለምነውን ነገር በጽናት መጠየቅ ይገባኛል፣ ነገር ግን ልቤ ከሚፈልገው ነገር ጋር የማይዋዕድ ከሆነ፣ ልቤ ይህንን ጸሎት ወደ እግዚኣብሔር እንዳቀርብ ከጠየቀኝ ሰው ፍላጎት ጋር የተሳሰረ ካልሆነ ጽናት እና ትዕግስት በፍጹም ሊኖረኝ አይችልም።
ስለእዚህ አሉ ቅዱስነታቸው ስለእዚህ አንድ የምልጃ ጸሎት ወደ እግዚኣብሔር በምናቀርበት ወቅት ወጤታማ ለመሆን ከፈለግን ይህንን ጸሎት እንድናደርግ ከጠየቀን ሰው ፍላጎት ጋር ልባችንን ማስተሳሰር፣ ጸሎታንን በጽናት ማድረግ፣ በጾም እና በጸሎት መትጋት ያስፈልጋል ማለታቸው ይታወሳል።
ምስጢረ ንስሐ በእግ/ር የፍቅር እቅፍ ውስጥ እንድንገባ ያደርጋል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በመጋቢት 13/2010 ዓ.ም ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት ምጢረ ንስሐ ማድረግ ማለት የቆሸሸውን ልብሳችንን ለማሳጠብ ወደ አንድ የልብስ ንጽህና መስጫ ቤት እንደ ምንሄድ ዓይነት ከቆሸሸው ሕይወታችን ለመንጻት ሳይሆን በእግዚኣብሔር በሞገስ የተሞላ የፍቅር እቅፍ ውስጥ ለመግባት ነው ማለታቸው ይታወሳል።
“እግዚኣብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ልክ አንድ እናት ለልጇ እንዳላት ዓይነት ፍቅር ነው። እግዚኣብሔር እኛን በፍጹም አይረሳንም። በፍጹም! ሊረሳንም በፍጹም አይችልም፣ ለገባልን ቃል ኪዳን ታማኝ ነው። እኛ ስለራሳችን ‘የእኔ ሕይወት በጣም መጥፎ የሆነ ሕይወት ነው . . .እኔ በእዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ እገኛለሁ፣ እኔ ኃጢኣተኛ የሆንኩ ሰው ነኝ’ . . .ወዘተ ልንል እንችል ይሆናል። እርሱ ግን አንተን ወይም አንቺን በፍጹም አይረሳም፣ ምክንያቱም እርሱ ለአንተ ወይም ለአንቺ ያለው ፍቅር ልክ አንድ አባት እና እናት ለልጃቸው እንዳላቸው ዓይነት ውስጣዊ ፍቅር ለእኛ ስላለው ነው”።
ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት የሚከተለውን ብለዋል. . .

“እግዚኣብሔር በመሆኑ የተነሳ ራሱን ሊክድ፣ እኛንም ሊክደን አይችልም፣ እግዚኣብሔር ፍቅሩን መካድ በፍጹም አይችልም፣ እግዚኣብሔር ሕዝቡን መካድ በፍጹም አይችልም፣ በአጠቃላይ ሊከደን አይችልም ምክንያቱም ለእኛ ከፍተኛ የሆነ ፍቅር ስላለው ነው። ይህም የእግዚኣብሔርን ታማኝነት ያሳያል። እኛ ወደ ምስጢረ ንስሐ በምንቀርብበት ወቅት ሁሉ እባካችሁን ልክ ወደ አንድ የልብስ ንጽሕና መስጫ ጣቢያ በመሄድ የቆሸሸውን ልብሳችንን እንደ ማሳጠብ አድርጋችሁ እንዳትመለከቱ። በፍጹም! ወደ ምስጥረ ንስሐ የምንሄድበት ዋነኛው ምክንያት የእዚህን ለቃሉ ታማኝ የሆነውን እና ሁል ጊዜ ቆሞ የሚጠብቀንን የእግዚኣብሔር ፍቅር ለመቀበል ነው።


 

05 January 2019, 08:59
ሁሉንም ያንብቡ >