ፈልግ

2018.11.08 Messa Santa Marta 2018.11.08 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የወንጌል ምስክርነት የእግዚአብሔርን ምሕረት የምናውቅበት መንገድ ነው”።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ጥዋት በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚያሳርጉ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ዛሬ ጠዋት ሐሙስ ጥቅምት 29 ቀን 2011 ዓ. ም. ባሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ፣ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት ደናግልና ምዕመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል፣ የወንጌል ምስክርነት የእግዚአብሔርን ምሕረት የምናውቅበት መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በላቲን የአምልኮ ስርዓት የቀን አቆጣጠር መሠረት ከሉቃስ ወንጌል በምዕ. 15, 1-10 ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው በዚህ የወንጌል ክፍል ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ሊሰሙት በቀረቡት በሙሴ ሕግ መምሕራን፣ በቀራጮችና በሃጢተኞች ፊት የሰጠውን ምስክርነት አስታውሰዋል።

የወንጌል ምስክርነት ለቤተክርስቲያን እድገት ነው፣

በዚያን ጊዜ በሙሴ የሕግ መምሕራንና በፈሪሳዊያን ዘንድ ምስክርነትን መስጠት እንግዳ ነገር እንደሆነ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወደ ሐጢአተኞች ዘንድ መሄድ፣ እንደ ሐጢአተኛ ስለሚያስቆጥር፣ ከዚህም ባለፈ እንደ አንድ የሥጋ ደዌ በሽተኛን እንደመንካት ስለሚቆጠር ፈሪሳዊያንና የሙሴ ሕግ መምሕራን ይህን የመሰለ ተግባር ለመፈጸም ፈጽሞ እንደማይደፍሩ ያስረዱት ቅዱስነታቸው በታሪክ ውስጥ ምስክርነትን መስጠት ለመስካሪዎችም ሆነ ለማንም ቀላልና ምቹ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ነገር ግን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምስክርነትን መስጠት ራስን ወደ መልካም ጎዳና እንደሚመልስ፣ በመሆኑም ቤተክርስቲያን የወንጌል ምስክርነትን ሳታቋርጥ በመስጠት ላይ ትገኛለች ብለዋል። የወንጌል ምስክርነት ትልቁ ምስጢርም ቤተክርስቲያንን እንድታድግ ማድረጉ ነው ብለው ኢየሱስ ክርስቶስም በአገልግሎቱ ወቅት ምስክርነትን መስጠት አላቋረጠም ብለዋል። የሙሴ ሕግ መምሕራን፣ ፈሪሳዊያንና ቀራጮች አልተገነዘቡትም እንጂ ምስክርነትን መስጠት ከብሉይ ኪዳን ዘመን አንስቶ የነበረ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው እነዚያ የሙሴ ሕግ መምሕራን በመጽሐፋቸው ውስጥ “ምህረትን እንጂ መስዋዕትን አልፈልግም” ተብሎ የተጻፈውን ያነቡታልም፣ ነገር ግን የምሕረትን ትርጉም አልተረዱትም ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የእግዚአብሔርን ምሕረት ምስክርነትን በመስጠት ግልጽ አድርጎታል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በስብከታቸው፣ ምስክርነት ወደ መልካም መንገድ እንደሚመራና በሌላ በኩልም ወደ አደጋ ውስጥም ሊከት እንደሚችል አስረድተዋል።

ግጭትን ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ፣ የማይረባ ወሬን ማብዛት፣

የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት፣ ግጭትን ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ፣ ፋይዳ በሌለውና በማይረባ ከንቱ ወሬ ጊዜያቸውን ለሚያባክኑ የሙሴ ሕግ መምሕራን መልካም ትምህርት ሆኗቸዋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የሙሴ ሕግ መምሕራንና ፈሪሳዊያን “ይህስ ሃጢአተኞችን ይቀበላል፣ ከእነርሱም ጋር አብሮ ይበላል” እያሉ በኢየሱስ ላይ ያጉረመርሙ ነበር እንጂ ይህ ሰው መልካም ሰው ሃጢአተኞችን ከክፉ ተግባራቸው ለመመለስ ይጥራል፣ ይመክራቸዋል አላሉም ነበር ብለዋል። ይህ አስተሳሰባቸው የምስክርነትን ትርጉም የሚያሳንስና የሚያንቋሽሽ እንደነበር አስረድተዋል። በዕለታዊ ኑሮአችንም ቢሆን ሰዎች ችግሮችን ለመፍታት እርስበርስ ከመመካከርና ከመወያየት ይልቅ ተደብቀው የሚያደርጉት ማጉረመረም ማሕበርዊ ኑሮን፣ ቁምስናዎችንም ጭምር የሚጎዳ መሆኑን አስታውሰው፣ ሰዎች የሚያጉረመርሙትም በአደባባይ ለይ በግልጽ አውጥተው ለመናገር ድፍረት ስለሚያንሳቸው ነው ብለዋል። በሃገረ ስብከቶች መካከል፣ በፖለቲካ ዘርፍም ያየን እንደሆነ አንድ መንግሥት ለሕዝቡ ታማኝ ያልሆነ እንደሆነ ስም ወደ ማጥፋት ወንጀል ይሄዳል ያሉት ቅዱስነታቸው አምባ ገነን መንግስታትን ለምሳሌነት ወስደው፣ የአምባ ገነን መንግሥታት ቀዳሚ ተግባር የብዙሃን መገናኛዎችን በመቆጣጠር ለአገዛዙ ጠንቅ የሆኑትን ያሸማቅቃል ወይም ስማቸውን ማጥፋት ይጀምራል ብለዋል።

የኢየሱስ ጥያቄ፣

ግብዞች የሚከተሉት መንገድ እውነታውን ላለማየት ወይም ሰዎች እንዲያስቡበት አለመፍቀድ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ግን በእርሱ ላይ በሚያጉረመርሙት ላይ ፍርድን ከመስጠት ይልቅ እነርሱ ራሳቸው የሚጠቀሙበትን ጥያቄዎችን የማቅረብ መንገድ ይከተል እንደነበርና በዚህም ይረታቸው እንደነበር አስታውሰዋል። በዕለቱ ከተነበበው ከሉቃስ ወንጌል በምዕ. 15 ከቁ። 4 የተጻፈውንም እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል። እንደሚከተለው ይነበባል፦ “መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው?  ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ። የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል። እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል”።

የወንጌል አመለካከት ከዓለም አመለካከት ይለያል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻ በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ያደረጉትን አስተንትኖ ሦስት መሠረታዊ ቃላትን በማስታወስ አጠቃልለዋል። እነስርሱም ለቤተክርስቲያን ማደግ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የወንጌል ምስክርነት፣ ምስክርነትን ከመስጠት ይልቅ በራስ ላይ ምንም ጉዳት ሊያስከትል የማይችል ማጉረምረምና በመጨረሻም ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ለመጉዳት የሚፈልጉትን ለመርታት ይከተል የነበረው ጥያቄን የማቅረብ መንገድ መሆናቸውን አስረድተው በማከልም የሙሴ ሕግ መምሕራንና እነርሱን የሚከተሉት በሙሉ  ያልተገነዘቡትን አንድ መንገድ ይህም ከወንጌል የሚገኝ ደስታ እንደሆነ ገልጸው፣ ዓለም ከሚያቀርብልን መንገድ ይልቅ ቅዱስ ወንጌል የሚያሳየንን መንገድ በሚገባ እንድናውቅ እግዚአብሔር አምላክ ይርዳን ብለዋል።        

08 November 2018, 16:23
ሁሉንም ያንብቡ >