ፈልግ

2018.11.12 Messa Santa Marta 2018.11.12 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ጳጳስ አገልጋይ እንጂ ተገልጋይ አይደለም”።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ዛሬ ጠዋት ሰኞ ህዳር 3 ቀን 2011 ዓ. ም. ባሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ፣ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት ደናግልና ምዕመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል ጳጳስ አገልጋይ እንጂ ተገልጋይ አለመሆኑ አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው፣ በላቲን የአምልኮ ስርዓት መሠረት ዛሬ ታስቦ የዋለውን፣ ጳጳስና ሰማዕት የሆኑትን ቅዱስ ጆስፋትን አስታውሰው፣ ለአስተንትኗቸውም ይሆናቸው ዘንድ ዛሬ የተነበበውን የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ወደ ቲቶ በምዕ. 1 ከቁጥር 1-9 የተጻፈውን ጠቅሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቤተክርስቲያን አሁን ወደ ምትገኝበት ደረጃ እንዴት ልትደርስ እንደቻለች ያስርዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቤተክርስቲያን በምድራዊ ጉዞዋ ብዙ ያልተስተካከሉ ነገሮች እንዳሏት፣ ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ እነዚህን ያስተካከሉና ትክክለኛ መንገድን ያልተከተሉ አካሄዶቿንን በሚያስገርም ድንቅ ሃይሉ ስለሚያስተካክለው መደናገጥ የለብንም ብለው ይህም ለክርስቲያናዊ ሕይወታችን መልካም ተስፋን የሚሰጥ ጥሩ ምልክት ነው ብለዋል።

“ቤተክርስቲያን ያለ ችግር፣ ያለ እንቅፋት፣ ያለ ስደት፣ ያለ መከራ ሁሉ ነገር በተመቻቸበት ሁኔታ አልተመሠረተችም፣ አልተጓዘችምም ብለው ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ በችግሮችና በፈተናዎች መካከል ትገኛለች ብለዋል። ነገ ግን ፈተናዎችም ያልፋሉ፣ ችግሮችም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ይወገዳሉ ። የመጀመሪያውን የኢየሩሳሌም ጉባኤ ያየን እንደሆነ ፍትሃዊነትን በሚከተሉትና ፍትሃዊነትን መከተል በማይፈልጉ መካከል ትልቅ ቅራኔ ነበር። በዚህ ቅራኔ መካከልም ቢሆን ባልተሰማሙበት ጉዳይ ላይ በመወያየት ወደ ስምምነት መድረስ ችለዋል።     

ለአንድ ጳጳስ የሚሰጠውም ትርጉም እግዚአብሔር የመሠረታት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሚል ነው ማለት ነው። የሚያስተዳድረውም የቤተክርስቲያንን ቁሳዊ ንብረቶችን ወይም ስልጣንን አይደለም። ጳጳስ ራሱን መመልከት ያለበት እንደ እግዚአብሔር አገልጋይ እንጂ ከዚህ ባሻገር እርሱን በማይመለከቱ በሌሎች የሥራ ዘርፍ ውስጥ መግባት የለበትም። እግዚአብሔር ለአብርሃምም እንደተናገረው አንድ ጳጳስ በራሱ ጉልበት ወይም ስልጣን የሚመራ፣ ራሱ በሚፈልገው መንገድ የሚጓዝ ሳይሆን በእግዚአብሔር የሚመካና በሌሎች ዘንድ ነቀፋ የሌለበት የእግዚአብሔር አገልጋይ መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል።          

የጳጳስ መገለጫ መሆን ያለበትም ይህ ነው። እግዚአብሔር የመሠረታትን ቤተክርስቲያን የሚያስተዳድር ጳጳስ ወደ አገልግሎቱ ከመሰማራቱ አስቀድሞ በርካታ መስፈርቶችንና የብቃት መመዘኛዎችን የሚያሟላ መሆን ይኖርበታል። ከእነዚህም መካከል ትሑት፣ የዋህ፣ አገልጋይ እንጂ ራሱን ተገልጋይ አድርጎ የሚቆጥር መሆን የለበትም። ይህ የአንድ ጳጳስ ትክክለኛ ማንነት በተግባር መታየት ያለበት፣ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ወዲህ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በፊት በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመንም የነበረ በመሆኑ እንግዳ ነገር ሆኖ መታየት የለበትም። ቤተክርስቲያን ጳጳሳትን ስትሾም የጳጳሳት ማንነት፣ አገልግሎታቸውም ምን መምሰል እንዳለበት ቤተክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ማወቅ ይኖርባታል።”    

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በመጨረሻም አንድ ጳጳስ የእግዚአብሔር ትክክለኛ አገልጋይ የሚያሰኙትን እነዚህን መስፈርቶች የማያሟላ ካልሆነ ቤተክርስቲያንን ሊያስተዳድር ወይም ወደ መልካም አቅጣጫ ሊመራ አይችልም ብለው፣ አንድን ጳጳስ በእግዚአብሔርም ዘንድ በአገልግሎቱ የተመሰገን የሚያሰኘው ከሌሎች ጋር ተግባቢ ወይም ማራኪ የሆነ የስብከተ ወንጌል ቃል ስለሚያሰማ ሳይሆን ከሁሉ አስቀድሞ ራሱን ዝቅ በማድረግ በየዋህነትና በትህትና ሌሎችን ለማገልገል የተዘጋጀ ብቻ ሳይሆን አገልግሎቱን በተግባር ያስመሰከረ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት በላቲን የአምልኮ ስርዓት መሠረት ታስቦ የዋለውን ጳጳስና ሰማዕት የሆነውን ቅዱስ ጆስፋትን በማስታወስ፣ ቤተክርስቲያንን የሚያገለግሉ ጳጳሳት፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ባስተላለፈው አደራ መሠረት፣ በታማኝነት፣ በትህትናና በየዋህነት፣ ለእግዚአብሔርም በመታዘዝ ማከናወን የሚያስችላቸውን ሃይል እንዲያገኙ በማለት በጸሎታችን እንድናግዛቸው አደራ ብለዋል።

12 November 2018, 15:05
ሁሉንም ያንብቡ >