ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 25/2010 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 25/2010 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት   (à © Vatican Media)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ፡ “ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጣዖት እየሆነ የሚገኘውን የገንዘብ ፍቅር ማስወገድ ይገባል”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው እለት ማለትም በጥቅምት 30/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ቀሳውስት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙት ስብከት መሰረቱን አድርጎ የነበረው በወቅቱ የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የስረዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት የተከበረውን በሮም ከተማ የሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ላቴራን ባዚሊክ ዓመታዊ ክብረ በዓል በተዘከረበት ወቅት ከዮሐንስ ወንጌል 2፡13-22 ላይ በተጠቀሰው “ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ውስጥ ይነግዱ የነበሩትን ሰዎች እንዳስወጣ” በሚገልጸው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ ስብከት እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በወቅቱ ባሰሙት ስብከት እንደ ግለጹት በዛሬው ዘመን የሚገኙ "አብያተ ክርስቲያኖቻችን" ያላቸውን መንፈሳዊ ቅንዓትና ክብር ጠብቀው ይጓዙ ዘንድ ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይገባናል ብለዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

“አብያተ ክርስቲያናት የእግዚኣብሔር ቤት ወይም ማደርያ ናቸው እንጂ የንግድ ሥፍራ አይደሉም፣ ወይም ደግሞ ዓለማዊ በሆኑ ማኅበራዊ ጉዳዮች የተሞላ አዳራሽ አይደለም” በማለት ስብከታቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው ዛሬ (ጥቅምት 30/2011 ዓ.ም) ከዮሐ. 2፡13-22 ላይ ተወስዶ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ እንደ ተጠቀሰው ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲነግዱ የነበሩ ሰዎችን በገመድ በተሠራ ጅራፍ አባሮ ያስወጣቸው በዚሁ ምክንያት እንደ ሆነ ገለጸው “የእግዚኣብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ በፍቅር አነሳሽነት ለቤትህ ያለኝ ቅንዓት እንደ እሳት ያቃጥለኛል” በማለት ወደ ገበያ መዓከልነት የተቀየረውን የእግዚኣብሔር ቤት ስያነጻ ይታያል” ብለዋል።

ጣዖቶች በባርነት ይገዙናል

ኢየሱስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ በገባበት ወቅት “በቤተ መቅደስ ውስጥ በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው ባገኛቸው ወቅት ይህ ቦታ "ከእግዚአብሔር" ይልቅ "ገንዘብ" ለመለዋወጥ የመጡ ጣዖት አምላኪ ሰዎች እንደ ሚበዙበት ኢየሱስ እንደ ተገነዘበ” የገለጹት ቅዱስነታቸው “በእያንዳንዱ ገንዘብ ውስጥ ጣዖት እንደ ሚገኝ ገልጸው “ጣዖታት ሁልጊዜ ወርቃማ ናቸው፣ ጣዖታት ባሪያዎቻቸው የማደርግ መስባዊ ኃይል አላቸው” ብለዋል። ቅዱስነታቸው ይህንን ሐሳባቸውን በሚገባ ለማስረጽ በማሰብ የሚከተለውን ብለዋል . . .

ይህ የእኛን ትኩረት በመሳብ እኛ ቤተ መቅደሶቻችን እና አብያተ ክርስቲያኖቻችንን እንዴት እንደምናስተናግድ ያሳየናል፣ በእውነት የእግዚአብሔር ቤት ከሆነ፣ የጸሎት ስፍራ ከሆነ፣ ከእግዚኣብሔር ጋር የምንገናኝበት ሥፋር ከሆነ፣ ካህናቱ ይህንን የሚደግፉ እንደ ሆነ እንድናስብ ያደርገናል። ወይም ደግሞ የንግድ መዓከል ይመስላል ወይ? የሚለውንም እንድናስብ ያደርገናል። አዎን! እዚህ በሮም ከተማ ሳይሆን ከሮም ከተማ ውጪ አንዳንድ ቦታዎች የአገልግሎት ክፍያ ዝርዝር የያዘ መግለጫ ተመልክቻለሁ። “ነገር ግን እንዴት ነው ለቤተ ክርስቲያን ምስጢራት ገንዘብ የሚከፈለው?። “ነገር ግን መስጠት የሚፈልግ ሰው ምጽዋት መመጽወት ይችላል። ይህንንም የሚያደርጉት በፈቃደኝነት ነው -ከፈለጉ ብቻ- ይህም ምጽዋት መደረግ የሚገባው በድብቅ፣ ማንም ሳያይ በምጽዋት መስጫ ሳጥን ውስጥ ብቻ ሊሆን ይገባዋል። ዛሬ ምጽዋት የሚሰጥ ብዙ ሰው አይታይም፣ ይህ አደጋ ይታያል፣ ነገር ግን ምጽዋት መስጠት ይኖርብናል፣ አዎን ቤተ ክርስቲያንን መደገፍ ይኖርብናል። ቤተ ክርስቲያንን የሚደግፏት ደግሞ ምዕመናኖቿ ናቸው፣ ነገር ግን ይህንን ማድረግ የሚገባቸው የምጽዋት መስጫ ሳጠን ውስጥ በመጨመር ሊሆን ይገባል እንጂ የዋጋ መክፈያ ዝርዝር በማውጣት ሊሆን ግን አይገባውም።

ቤተ ክርስቲያን የንግድ ማዕከል በፍጹም መሆን የለባትም

ቤተ ክርስቲያን ዓለማዊ የሆነ ፈተና እየገጠማት እንደ ሚገኝ በመጥቀስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህንን በተመለከተ ደግሞ የሚከተለውን ብለዋል. . .

እስቲ ወደ አንድ ምስጢራት ወደ ሚሰጥበት ወይም አንድ የመታሰቢያ በዓል ወደ ሚከበርበት የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ወደ ሚፈጸምበት ቦታ ወደዚያ እንደሄድን እና እንደ ተመለከትን አድርገን እናስብ፣ አንዳንዴ  የእግዚአብሔር ቤት የአምልኮ ቦታ ነው ወይም ደግሞ አንድ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጥበት አዳራሽ ይሁን አይሁን መለየት ያዳግታል። አንዳንድ ክብረ በዓለት በይዘታቸው ወደ ዓለማዊነት ያዘነብላሉ። እውነት ነው ክብረ በዓላት ያማሩ መሆን ይኖርባቸዋል፣ ነገር ግን ዓለማዊ የሆነ ይዘት ግን ሊላበሱ አይገባም፣ ምክንያቱም ዓለማዊነት የሚመነጨው ከገንዘብ አምላክ ነው። ይህም ግልጽ የሆነ የጣዖት አምልኮ ነው። ለቤተ ክርስቲያኖቻችን ያለን ቅንኣት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል፣ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ ለቤተ ክርስቲያን የምንሰጠቅ ክብር ምን ያህል ነው? በማለት እኛም እንድናስብ ያደርገናል።

ልባችን የእግዚኣብሔር ቤተ መቅደስ ነው

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች በጻፈው (1ቆር. 3፡9-11, 16-17) እና በዕለቱ በቀዳሚነት በተነበበው የምጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተመርኩዘው “የእያንዳንዳችን ልብ የእዚኣብሔር ቤተ መቅደስ ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በዚህም ምክንያት ሁላችንም ልባችን የእግዚኣብሔር ቤተ መቅደስ መሆኑን ተገንዝበን “ከዓለማዊነት መንፈስ እና ከጣዖት” ልባችንን ልንታደግ ይገባል ካሉ በኋላ ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
09 November 2018, 15:11
ሁሉንም ያንብቡ >