ፈልግ

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት  (@Vatican Media)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ራስ ወዳድነት ፉክክር፣ ጭቅጭቅ እና ጦርነት ያስከትላል!”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው እለት ማለትም በጥቅምት 26/2011 ዓ.ም በቫቲካን በምገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ለተገኙ ቀሳውስት፣ ደናግላን እና ምዕመናን ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት በሕይወት ሂደት ውስጥ አንድ ሰው “የራሱን ፍላጎት” ለሟሟላት በማሰብ መኖር እንደ ሌለበት ገልጸው ነገር ግን ሁሉንም በእኩልነት ተጠቃሚ ማድረግ የምያስችል ዓለማቀፋዊ የሆነ አድማስ መዘርጋት ያስፈልጋል ምክንያቱ ራስ ወዳድነት ፉክክር፣ ጭንቀት እና ጦርነትን ያስከትላል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

"ተቀናቃኝ የመሆን ፍላጎት እና ጭቆና"

"ተቀናቃኝ የመሆን ፍላጎት እና ጭቆና" የኅብረተሰቡን ሥር መሠረት አጥፍቷል፣ መከፋፈልንና ግጭቶችን በመዝራት ላይ ይገኛል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በዕለቱ ከሉቃስ ወንጌል (14፡12-14) ላይ ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ተመርኩዘው ባሰሙት ስብከተት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “የእራስ ወዳድነት መንፈስ” ሰላማዊ ያልሆነ እና ከኢየሱስ አስተምህሮዎች ጋር የሚቃረን ሐሳብ ነው ብለዋል።

ነጻነት በተናጥል የሚገኝ ነገር ሳይሆን ሁሉን አቀፍ ነው

“የኢየሱስ አስተምህሮ በጣም ግልጽ የሆነ አስተምህሮ ነው፣ ሁሉንም ነገር የራሳችንን የግል ጥቅም ለሟሟላት ብቻ በማሰብ መከወን እንደ ሌለብን የሚያሳስበን አስተምህሮ ነው” በማለት ስበከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ጓደኝነትን የምንመስርተው የራሳችንን ፍላጎት ብቻ ለሟሟላት በማሰብ ላይ በተመሰረተ መልኩ ሊሆን አይገባም ብለዋል። የራስን ፍላጎት እና ጥቅም ብቻ ለማስከበር መሮጥ በራሱ በእርግጠኛነት “የራስ ወዳድነት መንፈስን” የምያመላክት ነገር ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ነገር ግን የኢየሱስ አስተምህሮ ከዚህ በጣም የተለየ አስተምህሮ መሆኑን ገልጸው ኢየሱስ የራሳችንን ጥቅሞች ከማሳደድ ይልቅ ሁሉንም ሰዎች በእኩልነት ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ዓለማቀፋዊ የሆነ ምዕዳር መፍጠር እንዳለብን ነው ኢየሱስ የሚመክረን ብለዋል። የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ተጠቃሚ ማድረግ በራሱ “ክፍፍል የሚፈጥር ነገር ነው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በዕለቱ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ፊሊጲስዮስ (ፊሊጲ 2፡1-4) በጻፈው መልእክቱ ላይ እንደ ተጠቀሰው "አንድነትን የሚጻረሩ ሁለት ነገሮች እንዳሉ” መጥቀሱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው እነዚህም “ፉክክርና ጭቅጭቅ ናቸው” ብለዋል።

ይህንን በተመለከተ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . . .

ሌላው ቀርቶ ጭቅጭቅ የሚፈጠረው ከፉክክር ነው፣ ምክንያቱም ብዙ ሰዎች እነርሱ በማደግ ላይ መሆናቸው ሰለማይሰማቸው ነው፣ አንደኛው ከአንደኛው በተሻለ ሁኔታ ማደጉን ለማሳየት በምያደርገው ፍክክር ጭቅጭቅ ይፈጠራል፣ ፉክክር ሰዎችን የሚያጠፋ አፍራሽ የሆነ ተግባር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ሚለው “በማነኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የተቀናቃኝነት መንፈስ አይኑር” ይላል። ፉክክር ሌላውን ለመጨቆን የምደረግ ትግል ውጤት ነው። ፉክክር በጣም አስቀያሚ የሆነ ነገር ነው፣ ግጭት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ መፍጠር ይቻላል፣ ነገር ግን ሁልጊዜ ሌላውን ለማጥፋት እና እራስን ከፍ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው። እናም እኔ በሌሎች ፊት ጎበዝና በጣም ጥሩ ሆኜ ለመታየት በመፈለግ ሌሎችን አሳንሼ እመለከታለሁ። የራሴን ከፍታ ብቻ ጠብቄ እጓዛለሁ። ፉክክር የወደፊቱን የራሴን ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል መንገድ ነው።

እብሪት ማኅበረሰብን ያፈርሳል

በተመሳሳይ መልኩም ራሱን ከሌሎች ጋር በማፎካከር እርሱ ራሱን ከሁሉም የተሻለ አድርጎ ራሱን የሚቆጥር እብሪተኛ የሆነ ሰው ለማኅበርሰቡ አደገኛ ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህንን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስነታቸው የምከተለውን ብለዋል . . .

እንዲህ ዓይነት ባህሪይ አንድን ማኅበረሰብ ያፈርሳል፣ እንዲያውም በተጨማሪ አንድን ቤተሰብ ያፈርሳል . . . የአባታቸውን ወይም የቤተሰብ ሐብት ለመውረስ የምፎካከሩ ሁሉት ወንድማማቾችን ሁኔታ በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል፡ ይህም በእየለቱ የምያጋጥም እውነታ ነው። እስቲ ደግሞ ከሁሉም በላይ እንደ ሆኑ አድርገው ራሳቸውን የምቆጥሩትን እብሪተኛ ስለ ሆኑ ሰዎች እናስብ።

የክርስትና ሕይወት የተወለደው ኢየሱስ ከሰጠን ነጻ የሆነ ጸጋ ነው!

“የክርስትና ሕይወት የተወለደው ኢየሱስ ከሰጠን ነጻ የሆነ ጸጋ ነው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ክርስቲያኖች የእግዚኣብሔር ልጅ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳያቸውን አብነት መከተል እንደ ሚገባቸው ገለጸው በተለይም ደግሞ ኢየሱስ በነጻ የሰጠንን ጸጋ በመመልከት እኛም በበኩላችን ከሌሎች ሰዎች በምላሹ ምንም ዓይነት ነገር ሳንጠብቅ የኢየሱስን አብነት በመከተል ነጻ የሆነ አገልግሎት መስጠት እንደ ሚያስፈልግ ገልጸው ማነኛውንም እብርት እና ፉክክር አስወግደን ጥቃቅን በሚባሉ ሰላምን ለመገንባት የምያስችሉንን ተግባራትን በእየቀኑ በመፈጸም ዓለማችን በሰላም መንገድ ላይ እንድትጓዝ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል። ይህንን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስነታቸው የምከተለውን ብለዋል

የጦርነት ዜናዎችን ስናነብ፣ ለምሳሌም በየመን በረሃብ አረንቋ እየተገረፉ የምገኙትን ሕጻናት ጉዳይ ስንመለከት ይህ ጉዳይ የጦርነት ፍሬ እንደ ሆነ እንገነዘባለን፣ እነዚህ ምስኪን ሕጻናት ለመኖር ሲታገሉ እንመለከታለን. . . ለምንድነው እርሱ የሚበላ ነገር የሌላቸው? ነገር ግን በተመሳሳይ መልኩም በየቤታችን በየተቋሞቻችን በፉክክር የተነሳ ተመሳሳይ የሆኑ ጦርነቶች ይካሄዳሉ፣ ጦርነት የሚጀምረው ከዚህ ነው! ሰለዚህ በቅድሚያ ሰላም ማስፈን መጀመር የሚገባን ከዚህ ነው፣ ከቤተሰብ፣ ከቁምስና፣ ከተቋማት፣ ከሥራ ቦታ ሊጀመር ይገባል፣ ይህንንም የምናደርገው ሁል ጊዜ አንድ የሆነ ማኅበረሰብ ለመገንባት እና የራሳችንን ሳይሆን የማኅበረሰቡን ጥቅም በማስጠበቅ ሊሆን ይገባል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
05 November 2018, 08:33
ሁሉንም ያንብቡ >