ፈልግ

 2018.10.19 Messa Santa Marta 2018.10.19 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “መንፈስ ቅዱስ የክርስቲያኖች ቤዛ ነው”።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባወረሰን የመንፈስ ቅዱስ ሃብት በመታገዝ ወደ ፊት በመጓዝ ወደ ዘላለማዊው ቤታችን መድረስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት፣ ዓርብ ጥቅምት 9 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ውስጥ ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ ለተካፈሉት ካህናት ደናግልና ምዕመናን ባሰሙት ስብከታቸው የመንፈስ ቅዱስን የማዳንና የመለወጥ ሃይልን የማይቀበሉ ግብዝ ክርስቲያኖች መኖራቸውን አስታውሰው መንፈስ ቅዱስ የክርስቲያኖች ቤዛ እንደሆነ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው እንደገለጹት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባወረሰን የመንፈስ ቅዱስ ሃብት በመታገዝ ወደ ፊት በመጓዝ ወደ ዘላለማዊው ቤታችን መድረስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከሉቃስ ወንጌል በምዕ. 12 1-7 በተነበበው የዕለቱ ንባብ ላይ ያስተነተኑት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እርሾ የተናገረውን በማስታወስ፣ የሚያሳድግ እርሾ እንዳለ ሁሉ የሚያበላሽና ወደ ውስጥ የሚያሳድግ እርሾ አለ ብለዋል። እንዳናድግ የሚያድረገን፣ የፈሪሳዊያን፣ የሰዱቃዊያንና የሙሴ ህግ መምህራን፣ የግብዞች እርሾ ነው ብለዋል። በጥቂቱም ቢሆን ለሌሎች የሚያድረጉትን መልካም ነገር በሰዎች ዘንድ ለመታየት ብቻ የሚያከናውኑ፣ ውስጣቸውን ዝግ ያደረጉ ስግብግብ ሰዎች መኖራቸውን ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ከፈሪሳዊያን እርሾ ተጠንቀቁ ያለውን በመጥቀስ፣ ይህም የእነዚህ ሰዎች ግብዝነትን እንደሚጠቁም አስረድተው ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዝነትን ፈጽሞ ችላ አይልም ብለዋል። መልካም መስለው የሚታዩ በባሕርያቸውና በዕውቀታቸው የተመሰገኑ ነገር ግን ውስጣቸው ሲታይ በክፋት የተሞሉ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንዳስጠነቀቀው ከውጭ ሲታዩ ያማሩ፣ ነገር ግን ውስጣቸው ሲታይ እጅግ በጥላቻና በጥፋት የተሞሉ እንዳሉ አስረድተው እነዚህ ሰዎች ለራሳቸው ብቻ የሚጨነቁና የወደ ፊት ተስፋቸውም የጨለመባቸው እንደሆነ ገልጸዋል። በተቃራኒው ከራስ ይልቅ ለሌሎች የሚጨነቁ፣ ከወደቁበት ማንኛውም ዓይነት ችግር ለማላቀቅ የተቻላቸውን ለማድረግ ወደ ኋላ የማይሉ እንዳሉ አስረድተዋል።        

የታላቅ ደስታ ቃል ኪዳን፣

ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ “በፍቅሩም፣ እግዚአብሔር በጎ ፈቃዱ ሆኖ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ልጆቹ እንድንሆን አስቀድሞ ወሰነን” ያለውን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ መልዕክቱ፣ ራሳቸውን ለሌሎች ሰዎች አገልግሎት ያቀረቡትን ሰዎች መኖራቸውን ለመናገር ፈልጎ እንደሆነ አስረድተዋል። አንዳንዴ ይሳሳታሉ ነገር ግን ከስህተታቸው ይመለሳሉ፣ አንዳንዴ ይወድቅሉ ነገር ግን ከውድቀታቸው ይነሳሉ፣ አንዳንዴ ሃጢአትን ይሰራሉ ነገር ግን ተጸጽተው ንስሐን ይገባሉ። እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያወርሳቸው ቃል የገባላቸውን ታላቅ ደስታን ለመቀበል የተዘጋጁ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚለው “ኢየሱስ ክርስቶስ ሊሰጣችሁ ተስፋ ባደረገላችሁ በመንፈስ ቅዱስ ትታተማላችሁ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች በምዕ. 1, 13. በመንፈስ ቅዱስ በመታተማችን ደግሞ የእግዚአብሔር ክብር በሚገለጥበት ጊዜ የምስጋናን መስዋዕት ለጌታችን እናቀርባለን። 

ልባችን በደስታ ተሞልቶ፣

በመንፈስ ቅዱስ እንደምንታተም የተገባልንን ቃል ኪዳን ሐዋርያው ጳውሎስ ያስታወሰውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመጓዝ ወደ ውስጥ፣ ወደ ራስ ብቻ በሚለው አስተሳሰብ ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል በሚለው አስተሳሰብ በመነሳሳት፣  ምንም እንኳን በችግሮች፣ በፈተናዎችና በውድቀቶች መካካል ብንገኝም መንፈስ ቅዱስ ደግፎን ወደ ፊት እንድንጓዝ ያደርገናል ብለዋል።

ራስን ብቻ የሚያስብ፣ ለራስ ብቻ የሚጨነቅ፣ እድገቱ ወደ ፊት ሳይሆን ወደ ኋላ ነው። ወደ ኋላ እንዲያድግም የሚያደርግ ደግሞ በውስጥ ያለ መጥፎ እርሾ እንደሆነ ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስጠነቀቀው ሁሉ መጥፎ እርሾ በውስጣቸው ካለባቸው ግብዞች ራስን መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል። የመንፈስ ቅዱስን ሃይል የማይቀበሉ ግብዝ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የክርስቲያኖች እርሾ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ አስረድተው የመንፈስ ቅዱስ ሃይል ከውድቀታችን የምንነሳበትን፣ ከሐጢአታችን የምንፈወስበትን ተስፋ ይሰጠናል ብለዋል። በልባቸው ውስጥ መንፈስ ቅዱስን ያስገቡ ሰዎች በመከራ ውስጥ እንኳ ሆነው ደስታ እንደሚሰማቸው፣ ግብዞች ግን ለዚህ ደስታ አለመታደላቸውንና፣ ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘውን ደስታ ትርጉም የሚያውቁ አይደሉም በማለት የዕለቱን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ አጠቃልለዋል።             

19 October 2018, 17:21
ሁሉንም ያንብቡ >