ፈልግ

2018.10.12 Messa Santa Marta 2018.10.12 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “እኛ ትክክል ነን የሚሉ ክርስቲያኖችን ልብ በሉ”!

ለእለቱ ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖን በመቀጠል ቅዱስነታቸው እንዳስገነዘቡት፣ የሙሴ ሕግ መምሕራንና ፈሪሳዊያን፣ ወግን ከማክበር ወይም ከማጥበቅ ሌላ ራሳቸውን ለመለወጥ፣ ከሌላው ሕዝብም ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማስተካከል የተዘጋጁ አይደሉም ብለው እነዚህን በመሰሉ ሰዎች ዘንድ ምን ጊዜም ቢሆን ስር የሰደደ ችግር እንዳለባቸው ገልጸው መልካም በሚመስል ክርስቲያን ላይም ችግሮች እንዳሉበት ገልጸው በእነዚህ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሌለ፣ ነገር ግን በዓለማዊ መንፈስ እንደታሠሩ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ፣ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት ደናግልና ምዕመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል እንዳስረዱት ትክክል ነን የሚሉ ክርስቲያኖችን ልብ ማለት እንደሚያስፈልግ አሳስብዋል። የነፍሳት ድነት ለሁላችን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስጦታ ነው፣ እርሱ የነጻነትን መንፈስ ይሰጠናል ብለዋል። ይህን ካሉ በኋላም የግብዞች ልብ የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታ ለመቀበል የተዘጋጀ ባለመሆኑ ልንጠነቀቃቸው ይገባል ብለዋል።

ከሉቃ. ወንጌል ከምዕ 11. 37-41 በተነበበው በዛሬው የወንጌል ንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ያገለገላቸውና ያስተማራቸው ሰዎች ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር፣ ለፈሪሳዊያንና ለሙሴ የሕግ መምህራን ከሚሰጡት ፍቅር ጋር በማወዳደር፣ እነዚያ ራሳቸውን ንጹሕ አድርገው የሚቆጥሩ ፈሪሳዊያንና የሙሴ የሕግ መምህራን ኢየሱስ ክርስቶስን ጥፋተኛ አድረገው ሊይዙት ሊቀጡት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ፈሪሳዊያንና የሙሴ ሕግ መምሕራን በሕዝቡ መካከል የተከበሩና ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ቢሆንም ትክክለኛ ሕይወት እንደሌላቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ያውቅ እንደነበር አስረድተዋል። የሰዎችን በደልና ሐጢአት ይቅር የሚል፣ ከበሽታቸው የሚፈውስ፣ ይህስ እግዚአብሔር ሊሆን አይችልም ይሉት እንደነበርና ለሰዎች ስቃይና ችግር ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሙሴ ሕግ ክብርን መስጠት እንደሚመርጡ ገልጸዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ነጻ ስለሆነ ከፈሪሳዊያን ሳይቀር የምሳ ግብዣ ሲርብለት በደስታ ይቀበላል። ኢየሱስ ወደ ፈሪሳዊው ቤት ገብቶ ምሳ ለመብላት በማእድ ተቀመጠ። ምሳ ከመብላቱ በፊት እጁን ስላልታጠበ ፈሪሳዊው ተደነቀ። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ እናንተ ፈሪሳዊያን የብርጭቆውንና የሳህኑን ውጭውን አጥርታችሁ ታጥባላችሁ፣ በውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶባችኋል (በሉቃ. ወንጌል 11 ቁጥር 38)። ይህን ለሚሰማ ሰው፣ ኢየሱስ የተናገራቸው ነገሮች በእርግጥ ጥሩ አልነበሩም፣ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዝም ስላልነበረ እውነቱን ተናግሯል። በማከልም ለመሆኑ እናንተ ለምን ውጭውን ብቻ ትመለከታላችሁ፣ ውስጡንም ተመልከቱት እንጂ ያለውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎችን ውጫዊ ገጽታንና የልባቸውን ውስጥ ለይቶ በመመልከት ክፋታቸውን በሙሉ በግልጽ ነግሮአቸዋል ብለዋል።

በሌሎች የወንጌል ክፍሎች የተገለቱትን የሙሴ ሕግ መምሕራንና የፈሪሳዊያንን ማንነት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ሰዎች በአንድ ቃል ብቻ ግብዞች ብሎ ይጠራቸዋል ብለዋል። እነዚህ ሰዎች፣ ሰዎችን መግደል የሚችሉ፣ የሰዎችን ስም ማጥፋት የሚችሉ እንደሆኑ ገልጸው ዛሬም ቢሆን ይህን የመሰለ ክፋት የሚሰሩ፣ ገንዘብ ከፍለው የሐሰት ወሬን እንዲሰራጭ በማድረግ የሰዎችን ስም የሚያጎድፉ አልታጡም ብለዋል።

ለእለቱ ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖን በመቀጠል ቅዱስነታቸው እንዳስገነዘቡት፣ የሙሴ ሕግ መምሕራንና ፈሪሳዊያን፣ ወግን ከማክበር ወይም ከማጥበቅ ሌላ ራሳቸውን ለመለወጥ፣ ከሌላው ሕዝብም ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማስተካከል የተዘጋጁ አይደሉም ብለው እነዚህን በመሰሉ ሰዎች ዘንድ ምን ጊዜም ቢሆን ስር የሰደደ ችግር እንዳለባቸው ገልጸው መልካም በሚመስል ክርስቲያን ላይም ችግሮች እንዳሉበት ገልጸው በእነዚህ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሌለ፣ ነገር ግን በዓለማዊ መንፈስ እንደታሠሩ አስረድተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህ ሰዎች ነፍሳቸውን በፍቅር ክፍት በማድረግ፣ ነጻ ስጦታ የሆነው የእግዚአብሔር የማዳን ጸጋ እንዲገባ ዘወትር እንደሚመክራቸው ተናግረው፣ ሰውን ማዳን የሚችል ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ማንም እንደሌለ አስረድተዋል።

ከምዕመናን ወይም ከካህናት ወይም ከጳጳሳት መካከል ሕግን እናከብራለን፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ነን በማለት ከሚመጻደቁ ሰዎች ራሳቸውን ጠብቁ። ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣቸው የለምና፣ የነጻነት መንፈስ ይጎላቸዋልና ብለዋል። በመጨረሻም ይህ የራሳችንን ማንነት እንድንመለከት ያደርጋናል ብለው፣ ልባችንን ለጸሎት፣ ለእውነተኛ ነጻነት፣ ምህረትን የሚያስገኙ መልካም ተግባራትን ለመፈጸም የሚያስችለንን ነጻነት መለመን ያስፈልጋል ብለው የዕለቱን ስብከተ ወንጌል አጠቃልለዋል።                                 

16 October 2018, 17:27
ሁሉንም ያንብቡ >