ፈልግ

2018.10.12 Messa Santa Marta 2018.10.12 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ብልህና ክፉ መንፈስ ወደ ዓለማዊነት ሊመራን ይፈልጋል”።

ሰይጣን ወደ ሰው ልብ ውስጥ የመግባት እድል ካገኘ ለቅቆ መውጣትን አይፈልግም።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት ዓርብ ጥቅምት 2 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ፣ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት ደናግልና ምዕመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል እንዳስረዱት ብልህ አጋንንት ሳይታወቁ ወደ ነፈስ ውስጥ ስለሚገቡ ነቅቶ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አሳስብዋል።  

በላቲን የአምልኮ ስርዓት የቀን አቆጣጠር መሠረት ከሉቃስ ወንጌል በምዕ. 11. 15-26 ተወስዶ በተነበበው በዛሬው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፣ ክፉ መንፈስ ሳይታወቅ ወደ ነፍሳት ውስጥ ዘልቀው በመግባት ወደ አመጽ፣ ጥላቻና ጦርነት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል ብለዋል።

በውስጣችን ኢየሱስ ከአጋንንት ጋር እየተዋጋ ይገኛል፣

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከተ ወንጌል እንዳስረዱት ሰይጣን ወደ አንድ ሰው ልብ ውስጥ ለመግባት እድል ካገኘ ለቆ መውጣትን አይፈልግም። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣንን ከሰው ውስጥ ሲያባርረው የሰውን አካል ጭምር ይጎዳል ብለዋል። በሰው ውስጥ የተቀመጠ ሰይጣን የሰው ልጅ ክፋትን እንዲሠራ በማደፋፈር እዚያው መኖርን ይፈልጋል ብለው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱም የእኛም ጠላት የሆኑትን ክፉ መናፍስት ብዙ ጊዜ አባርሮአቸዋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በስብከታቸው በብሉይ ኪዳን የተገልጸው፣ በእግዚአብሔርና በእባቡ መካከል የተደረገው እውነተኛ ውጊያ፣ በኢየሱስ ክርስቶስና በሰይጣን መካከል የተደረገው ውጊያ ነው ብለዋል። ሳንገነዘበው ቀርተን ካልሆነ በስተቀር ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ውስጥ ሆኖ ከርኩስ መንፈስ ጋር እንደሚዋጋ አስረድተዋል።

ሰይጣን የተጠራው የእግዚአብሔርን ሥራ ለማፍረስ ነው፣

የሰይጣን ተልዕኮ ማውደም ነው ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሰይጣን የተጠራው የእግዚአብሔርን ሥራ ለማውደም እንደሆነ በመገንዘብ፣ በምንም ሳንታለል ሃይልን በሚሰጠን በኢየሱስ ክርስቶስ በመታጋዝ በርትተን መዋጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ለእኛ የሚዋጋልንና መከታችን የሚሆን የእግዚአብሔር ሃይል ስላለን፣ ይህን መገንዘብ የሚችል ብልህ ሰይጣን ጥቃት ሲከፍት ፊት ለፊት እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ሰይጣን የሚያጠቃው በክፉ ሰዎችና በጦርነቶች አማካይነት ነው።

በሉቃስ ወንጌል ምዕ. 11 ከቁ. 24-26 ኢየሱስ ክርስቶስ “ርኩስ መንፈስ ከሰው ውስጥ በወጣ ጊዜ የሚያርፍበት በመፈለግ ውሃ በሌለበት በደረቅ ምድር ሁሉ ይዞራል። የሚያርፍበት ቦታ ካገኘ ግን ወደ ወጣሁበት ቤቴ ተመልሼ ልሂድ ይላል። ስለዚህ ተመልሶ ሲመጣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚህ በኋላ ሄዶ ከእርሱ ይብስ የከፉ ሌሎች ሰባት አጋንንት ይዞ ይመጣል። ቀድሞ እርሱ በነበረበት ቤትም ገብቶ በዚያ ይኖራሉ። የዚያም ሰው የመጨረሻ ሁኔታ ከመጀመሪያው ይልቅ የባሰ ይሆናል” ያለውን በመጥቀስ እንዳስገነዘቡት ሰይጣን በክፉ ሰው በኩል ወይም በሰዎች መካከል ጦርነቶችን በመክፈት ሊያጠቃን ሳይችል ሲቀር ሌላ ማጥቂያ መንገድን ይፈልጋል እንጂ ተኝቶ አያድርም ብለው ይህን የማጥቂያ መንገድ በሁላችን ላይ ይፈጽማል ብለዋል።

እኛ ክርስቲያኖች ነን፣ ካቶሊኮች ነን፣ መስዋዕተ ቅዳሴን እናስቀድሳለን፣ ዘወትር እንጸልያለን፣ በእኛ በኩል ሁሉም መልካም ነው ብለን እናስብ ይሆናል። ነገር ግን ድክመታችንን መገንዘብ፣ ሐጢአታችንን ማወቅ ያስፈልጋል። ሰይጣን ብልጥ በመሆኑ ዘወትር ሊያጠቃን ይፈልጋል። በሮቻችንን በየጊዜው ያንኳኳል። እውስጣችን የመግባት ዕድል ካገኘ ክፉኛ ሊያጠቃን ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ አደጋ እንዳይደርስብን ሃይላችንም መከታችንም በመሆን ያስጠነቅቀናል ብለዋል።

ሰይጣን ወዳጅነትን ለመፍጠር ይፈልጋል፣

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዕለቱ በተነበበው የወንጌል ክፍል ያደረጉትን አስተንትኖ በመቀጠል፣ በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ ስንገኝ፣ ከውድቀት ለመዳን ተጠንቅቀን መቆም ያስፈልጋል ብለዋል። ቀጥለውም ከእነዚህ ከሁለቱ የሚብሰው የቱ ነው? በሐጢአት ውስጥ ወድቀህ ዘወትር እንድታፍር የሚያደርግ ክፉ መንፈስ ወይስ ወዳጅህ መስሎ በውስጥህ እየኖረ ሐጢአትን እየፈጸምክ እንድትኖር የሚያድረግ ክፉ መንፈስ” በማለት ጠይቀዋል።

ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል፣

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለዕለቱ ያቀረቡትን የወንጌል አስተንትኖ ከማጠቃለላቸው በፊት በተለያዩ መንገዶች ሊያጠቁን ከሚፈልጉ ክፉ መናፍስት ራሳችንን ለመከላከል ተረጋግተንና ነቅተን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንደሚመክረን አስረድተው የዕለቱን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኗቸውን አጠቃልለዋል።      

12 October 2018, 17:19
ሁሉንም ያንብቡ >