ፈልግ

2018.10.11 Messa Santa Marta 2018.10.11 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ኢየሱስ ክርስቶስ በርትተን መጸለይ እዳለብን ያስተምረናል”።

ከእግዚአብሔር ዘንድ የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት እንጸልያለን። የምንጸልየውም በድፍረት መሆን አለበት። ምክንያቱም ጸሎታችንን የምናቀርበው ወዳጃችን ወደ ሆነው፣ ምንም ወደ ማይጎድልበት፣ የምንፈልገውን ሊሰጠን ወይም ሊሰማን ወደ ተዘጋጀው ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ነውና።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት ሐሙስ ጥቅምት 1 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ፣ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት ደናግልና ምዕመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል እንዳስረዱት ኢየሱስ ክርስቶስ በርትተን መጸለይ እዳለብን ያስተምረናል ብለው እግዚአብሔርን አንድ ነገር ስንጠይቅ ደፋሮች መሆን ይኖርብናል ብለዋል።

በላቲን የአምልኮ ስርዓት መሠረት ከሉቃስ ወንጌል በምዕ. 11. 5-13  ተወስዶ በተነበበው በዛሬው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፣ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን በሚያሳስበው ክፍል ላይ ትኩርት በማድረግ ባሰሙት ስብከታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ፣ ሌሊት ተነስቶ የሚበላ ነገር ካለ ለመለመን ወደ ጓደኛው ቤት ስለ መጣ ሰው ታሪክ የተናገራቸውን አስታውሰዋል።

በድፍረት ያለመታከት መጸለይ ያስፈልጋል፣

በዚህ የወንጌል ታሪክ ውስጥ የተገለጹትን ሦስት ነገሮች እንዳሉ፣ እነርሱም እርዳታን ፈላጊ ሰው፣ ጓደኛውና ዳቦ ናቸው ብለዋል። ርቦት የሚበላ ካለ ሊለምነው ወደ ጓደኛው ዘንድ የመጣው ሰው፣ በጓደኛው እምነት ስለጣለበት፣ የሚያስፈልገውን ነገር ሊሰጠው እንደሚችን በመተማመኑ እንደሆነ አስረድተው፣ እግዚአብሔርም በዚህ ምሳሌ በኩል እንዴት መጸለይ እንደሚገባ ሊያስተምረን ፈልጓል ብለዋል። ከእግዚአብሔር ዘንድ የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት እንጸልያለን። የምንጸልየውም በድፍረት መሆን አለበት። ምክንያቱም ጸሎታችንን የምናቀርበው ወዳጃችን ወደ ሆነው፣ ምንም ወደ ማይጎድልበት፣ የምንፈልገውን ሊሰጠን ወይም ሊሰማን ወደ ተዘጋጀው ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ነውና። ኢየሱስ ክርስቶስም ለደቀ መዛሙርቱ እንዳለው ሳትታክቱ ያለማቋረጥ ጸልዩ፣ ጸልዩ ይሰጣችኋል ተብሏልና።         

ጸሎት አስማት አይደለም፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብከታቸው፣ ጸሎት እንደ አስማት አንድን ነገር በቅጽበት እንዲታይ ወይም እንዲመጣ የሚደረግበት መንገድ አይደለም ብለዋል። ጸሎት “አባታችን ሆይ”! ብለን በሁለት ቃል ብቻ የምንጨርሰው አይደለም ካሉ በኋል ጸሎት ከሁሉም በላይ ፍላጎትን፣ ጥረትንና ያለመታከትን የሚጠይቅ፣ ፍርሃትን በማስወገድ የሚደረግ መሆን አለበት ብለዋል። ቅዱስነታቸው ይህ የሚሆንበትን ምክንያት ሲገልጹ ጸሎታችንን የምናቀርበው ወዳጃችን ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ስለሆነ ሀፍረት ሊሰማን አይገባም ብለዋል። ቅድስት ሞኒካን እናስታውሳት፣ ልጇ አጎስጢኖስ ክርስቲያን እንዲሆን በማለት፣ ለብዙ አመታት እንባዋን በማፍሰስ ውደ እግዚ አብሔር ዘንድ ጸሎትዋን አቀረበች። በመጨረሻም እግዚአብሔር ጸሎቷን ሰምቶላት፣ ለልቧ መሻት መልስ ሰጣት።

እግዚአብሔርን በጸሎት ማስጨነቅ ያስፈልጋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአርጀንቲና ያጋጠማቸውን ታሪክ በማስታወስ ሲናገሩ፣ “አንድ የቀን ሠራተኛ የነበረ፣ ልጁ በጠና ታማበት በሞት አፋአፍ ላይ ትገኝ ነበር። ሐኪሞችም ምንም ዓይነት ተስፋ አልሰጡትም ነበር። ይህ ሰው የሚያረገውን ሲያጣ 70 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ፣ የሉያና እመቤታችን ቤተመቅደስ ተብሎ ወደሚጠራ ቤተክስቲያን ይሄዳል። እሥፍራው ሲደርስ ጊዜው መሽቶ ስለነበር የእመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ ተዘግቶ አገኘው። ቢሆንም ሰውዬው ተስፋን ሳይቆርጥ ከቤተመቅደሱ ሥር ሆኖ ሌሊቱን በሙሉ ልጄን እፈልጋለሁ! ልጄን እፈልጋለሁ! እያለ እየጸለየ አደረ። በነጋታው ወደ ሆስፒታሉ በተመለሰ ጊዜ፣ ሐኪሞቹ ልጁን ለሌላ ምርመራ እንደሚያድረጉላት ከሚስቱ ይነገረዋል። ምርመራ ካደረጉ በኋላም ምንም ዓይነት በሽታ እንዳልተገኘባትና በመልካም የጤና ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ተነገረው”። ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህ ሰው እንዴት መጸለይ እንዳለበት በትክክል ያውቅ ነበር ብለዋል።

የሕጻናት ለቅሶ ቆይቶ መልስን ያገኛል፣

የሕጻናትን ለቅሶ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሕጻናት እንኳ አከታትለው ያለቀሱ እንደሆነ የሚፈልጉት ነገር ይሰጣቸዋል ብለው፣ ምናልባትም እግዚአብሔርን ይህን ያህል ካስጨነቅነው አይቆጣም ይሆን ብለው የሚያስቡ ይኖሩ ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ “እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ነገር መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ የሚኖር አባታችሁማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!” ማለቱን አስታውሰዋል። እውነተኛ ወዳጅ ለጓኛው ሁል ጊዜ መልካምን ይመኛል። ከተጠየቀው በላይ አብዝቶ ይሰጣል። በመሆኑም እንዴት መጸለይ እንዳለብን ማሰብ ያስፈልጋል። ጸሎታችንም በእርግጥ ከሚያስፈልጉን ነገሮች ጋር ግንኙነት ያላቸው እንደሆነ መመልከት ያስፈልጋል። እንዴት መጸለይ እንዳለብን ከዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል መማር ያስፈልጋል ብለው የዕለቱን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኗቸውን አጠቃልለዋል።      

11 October 2018, 17:30
ሁሉንም ያንብቡ >