ፈልግ

2018.10.05 Messa Santa Marta 2018.10.05 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ለግብዝ ክርስቲያኖች ወየውላቸው”!

“ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር መልዕክቱን እንድንቀበል፣ ምሳሌነቱንም እንድንከተል አያስገድደንም። ልባችንን ከፍተን መዳን የሚገኝበትን የፍቅር መልዕክቱ በግል ምርጫ እንድንቀበል ቢጠይቀንም እንኳ ለዚህ ፈቃደኞች ሆነን አልተገኘንም”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት አርብ መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ፣ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት ደናግልና ምዕመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል እንዳስረዱት ኢየሱስ ክርስቶስን በቤተክርስቲያን ውስጥ ብቻ ዘግተው ለሚያስቀምጡት ግብዝ ክርስቲያኖች ወየውላቸው ብለዋል።

በክርስቲያን ማሕበረሰብ የተወለድን እኛ ክርስትናን እንደ ባሕል አድርገን የመመልከት ዝንባሌ አድሮብናል ብለው ይህን ስናደርግ ስሕተት እንኳ አይሰማንም ብለዋል። ከስብከታቸው ጋር በማያያዝ፣ የምስዋዕተ ቅዳሴን ስነ ስርዓት ከፈጸምን በኋላም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደየ ቤታችን ይዘን ከመምጣት ፈንታ እዚያው ቤተክርስቲያን ውስጥ እንተወዋለን ብለዋል። ይህን በማድረጋችንም ኢየሱስ ክርስቶስን ከልባችን ውስጥ እናወጣዋለን ብለዋል። በማከልም ክርስቲያኖች ብንሆንም፣ ነገር ግን እንደ አረማዊያን እንኖራለን ብለዋል።

ሌላውን የማያፈቅር ሰው ሲመለከት ኢየሱስ ያዝናል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት የቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ አቸው እንደገለጹት በሰዎች ልበ ደንዳናነት የተነሳ ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዘን ቆስሏል ብለው ምክንያቱን ሲገልጹ ወደ ዓለም የመጣውና ራሱን ለሞት አሳልፎ የሰጠው ሌሎችን ለማዳን ቢሆንም ይህን ያልተገነዘቡት፣ የፍቅርን ትርጉም ካለማወቃቸው ነው ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር መልዕክቱን እንድንቀበል፣ ምሳሌነቱንም እንድንከተል አያስገድደንም። ልባችንን ከፍተን መዳን የሚገኝበትን የፍቅር መልዕክቱ በግል ምርጫ እንድንቀበል ቢጠይቀንም እንኳ ለዚህ ፈቃደኞች ሆነን አልተገኘንም ብለዋል።

ክርስቲያኖች ብንሆንም ኢየሱስን እንረሳዋለን፣

ከሉቃ. ምዕ. 10. 13-16 የተነበበውን የዛሬውን የወንጌል ንባብ ያስተነተኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኢየስሱ የፍቅር መልዕክት ልብን መዝጋት ለወንጌል መልካም ዜና ትኩረትን ያለመስጠት የዘመናችን ባሕላዊ ውጤት እንጂ ክርስቲያናዊ ዝንባሌ አይደለም ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለእያንዳንዳችን የሚናገረን የመዳን መልካም ዜና አለው። የኢየሱስን መልካም ዜና ለመስማት ፍላጎትና ምኞት የሚያጥረን ከሆነ ይህ የክርስትና ሕይወት ውጤት ሳይሆን የዘመናችን ባሕል ውጤት ነው ብለዋል።

05 October 2018, 17:47
ሁሉንም ያንብቡ >