ፈልግ

2018.09.20 Messa Santa Marta 2018.09.20 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ሰይጣን ግብዞችን ይጠቀማል፣ ኢየሱስ ግን ፍቅርን ያስተምራል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብከታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረትና የይቅርታ አባት መሆኑን መዘንጋት የለብንም ብለው፣ የእርሱን ምሳሌ በመከተል እኛም ለበደሉን ይቅርታን ለማድረግ እንጂ በሌሎች ላይ ለመፍረድ አልተጠራንም ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት፣ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ መሐሪዎች እንጂ በሰዎች ላይ የምንፈርድ መሆን የለብንም ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ ለተካፈሉት ምዕመናን፣ ካህናትና ደናግል ባቀረቡት ስብከት እንደተናገሩት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በምሕረቱና በይቅርታው እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅ ብለው ቤተክርስቲያን ቅድስት ብትሆንም እኛን የመሰሉ ሐጢአተኞችን በውስጧ ይዛለች በማለት ምህረትን ከኢየሱስ ክርስቶስ መለመን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የመጀመሪያ ንባብ በሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ መልዕክት በምዕ. 15፤ 1–11፣ ቀጠሎም በተነበበው የሉቃስ ወንጌል ምዕ. 7፣ 36-55 ላይ በማስተንተን እንደተናገሩት ኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረቱን ለሚለምኑት ምሕረት እንደሚያደርግላቸው ገልጸው፣ ይህንንም በሉቃስ ወንጌል እንደተጠቀሰው ሃጢአተኛ የነበረች ሴት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በመቅረብ እርሱን በማክበር፣ በማስተናገድና በመውደድ የተነሳ “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል” ያላትን አስታውሰዋል።  

ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሽም ብትሆን የፍቅር ሥራን ይመለከታል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት በቀረቡት የቅዱስ መጽሐፍ ንባባት ላይ በማስተንተን ባሰሙት ስብከታቸው፣ ከንባባቱ ለመረዳት እንደሚቻለው ሦስት ዓይነት ሰዎችን ለይተው አስቀምጠዋል። እነርሱም ሐዋርያቱ፣ ቅዱስ ጳውሎስና ሐጢአተኛዋ ሴት፣ እንዲሁም በሦስተኛነት ደግሞ የሕግ አዋቂዎች የሆኑትን ፈሪሳዊያን ጠቅሰው ከእነዚህም መካከል ሃጢአተኛ የነበረች ሴት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በፍቅር በመቅረቧ እርሱን በማክበሯ፣ በማስተናገዷና በመውድውዷ ሐጢአቷንም ሳትደብቅ መናዘዟን አስታውሰዋል። ሐዋርያው ጳውሎስም እንደዚሁ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ መልዕክት በምዕ. 15፤ ቁጥር 3 ላይ “እኔ የተቀበልኩትን፣ በመጀመሪያ ደረጃ ያለውን ነገር ለእናንተ አስተላለፍኩላችሁ፣ ያስተላለፍኩላችሁም ነገር በቅዱሳት መጽሐፍት እንደተጻፈው ክርስቶስ ስለ ሐጢአታችን ሞተ” ያለውን አስታውሰው፣ እነዚህ ሁለቱ ሰዎች እግዚአብሔርን በፍቅር እንደፈለጉት፣ ቢሆንም ፍቅራቸው ሙሉ እንዳልነበረ፣ ምክንያቱም ጳውሎስም ቢሆን ፍቅርን እንደ ሕግ ይመለከት እንደነበረና ልቡንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ዝግ በማድረግ ክርስቲያኖችን ያሳድድና ይገድል ስለነበር እውነተኛ ፍቅር በልቡ ውስጥ ገና እንዳልገባ አስረድተዋል።

የግብዞች ውርደት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፈሪሳዊያንና የሕግ መምሕራንን የግብዝነት አቋም በማስረዳት፣ እነዚያ ግብዞች ፈሪሳዊያን የተጨነቁት በሕጋቸው መፍረስ፣ በባሕላቸው እሴት መናድ እንጂ ስለ እውነተኛ ፍቅር ምንም ዓይነት ደንታ እንዳልነበራቸው አስረድተዋል። ስለዚህ ይቅርታንና ምሕረትን በሚያደርግ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርና በእኛ ደካማ፣ ግብዞች፣ ትክክል ነን ባዮች፣ እኛ ብቻ ድነትን አግኝተናል በምንል ፍቅር መካከል ውይይት ሊኖር ይገባል ብለዋል።

ቤተክርስቲያን ከግብዞች በኩል መከራን ተቀብላለች።

ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዞችን ለይቶ ያውቃል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቤተክርስቲያን በተጓዘችባቸው ታሪኮችዋ ሁሉ፣ በውስጥም ሆነ በውጭ ከሚገኙት ግብዞች በኩል ብዙ መከራ ሲደርስባት እንደኖረ አስታውሰው በሠሩት ሐጢአት በመተጸጸት ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትንና እርዳታን ከሚለምኑት ጋር ሰይጣን ምንም ግንኙነት እንደሌለው ነገር ግን ከግብዞች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስላለው ሰዎችን፣ ሕብረተሰብንና ቤተክርስቲያንንም ለማጥቃት እንደሚጠቀምባቸው አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብከታቸው ማጠቃለያ ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረትና የይቅርታ አባት መሆኑን መዘንጋት የለብንም ብለው፣ የእርሱን ምሳሌ በመከተል እኛም ለበደሉን ይቅርታን ለማድረግ እንጂ በሌሎች ላይ ለመፍረድ አልተጠራንም ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ፍቅሩ፣ ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረው ጳውሎስን፣ እንደዚሁም ለዚያች ሃጢአተኛ ሴት ምሕረትን እንዳደረገላቸው ሁሉ ለሌሎች ምሕረትን በማድረግ ብቻ እውነተኛ ፍቅር ማግኘት ይቻላል ብለው ግብዞች ግን ልባቸው የተዘጋ በመሆኑ እውነተኛ ፍቅርን ሊያገኙ አይችሉም ብለዋል።              

20 September 2018, 16:51
ሁሉንም ያንብቡ >