ፈልግ

2018.09.10 Messa Santa Marta 2018.09.10 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ቅዱስ ወንጌል ሁለት ዓይነት ሕይወትን አይፈቅድም”።

ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ለደካሞች ሃይላቸው ሊሆን፣ ለሐጢአተኞች ምሕረትን ለማስገኘት ነውና። ነገር ግን ክርስቲያኖች የክርስትናን ሕይወት ከሐጢአት ሕይወት ጋር በማዛመድ ለመኖር የሚመርጡ ወይም የሚፈቅዱ ከሆነ እነዚህ ክርስቲያኖች ግብዝ ክርስቲያኖች ናቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ትናንት ጠዋት በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ውስጥ ባሳረጉት መስዋዕት ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ቅዱስ ወንጌል ሁለት ዓይነት ሕይወትን እንድንኖር አይፈቅድም ብለዋል። በዓለምና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ልዩነት እንዳለ አስረድተው ወንጌል ሕይወትን እንደሚለውጥ የግብዝነትንም ሕይወት ይቃወማል ብለዋል። ክርስቲያን የሚጓዝበት መንገድ የሰማዕትነት መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈውን የመጀመሪያ መልዕክ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ክርስቲያኖች ነን ብለው በሚመጻደቁት ሰዎች ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ እጅግ መቆጣቱን የሚከተለውን የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት በመጥቀስ አስረድተዋል። ወንድሞቼ ሆይ፣ በመካከላችሁ አሳፋሪ የዝሙት ሥራ መኖሩ ይወራል፣ እንዲህ ዓይነቱ የዝሙት ሥራ በአረማዊያን ዘንድ እንኳ የማይደረግ ነው።  የመጀመሪያው የሐዋ. ጳውሎስ መልዕክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ምዕ. 5፤1.

የወንጌሉ ቃል ሙሉ በሙሉ የሚለውጥ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን እንዳስጠነቀቃቸው እንደነበር ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የወንጌሉ ቃል እርሱም፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሳችንን ብቻ ሳይሆን ሁለመናችንን፣ ሥጋችንንና መንፈሳችንን ሳይቀር እንደሚለውጥ አስረድተዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ሃይል ውሃን ወደ ወይን እንደለወጠው ሁሉ የእርሱ የወንጌል ቃል ማንነታችንን፣ ውስጣዊንና ውጫዊውን ማንነታችንን፣ ዕለታዊ ሕይወታችንን ጭምር የሚለውጥ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የወንጌሉ ቃል ምኑን ያህል ጠንካራ መሆኑን እንዳልተገነዘቡ አስታውሰው፣ የወንጌሉ ቃል፣ ሰዎች ለማሕበራዊ ኑሮ አቸው በሚስማማ መልኩ፣ ወይም ለአኗኗር ዘይቤአቸው እንዲጠቅማቸው ብለው እንደሚጽፉት ደንብ እንዳልሆነ አስረድተዋል። የወንጌሉ ቃል፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ የተገለጠበት፣ በእርሱ መንፈስ እንድንመራ የተደረግንበት እንደሆነ አስረድተዋል። እኛ ክርስቲያኖች በቅዱስ ወንጌሉ አማካይነት መለወጥን ያገኘን አዲስ ፍጥረት መሆናችንን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

በዘመናችን በርካታ ክርስቲያኖች፣ ክርስትና በሚፈቅደው ወይም በሚያስተምረው አኳኋን እንኖራለን ቢሉም፣ እንደዚህ ብንኖር እንደዚያ ብንኖር በማለት የተለያዩ አስተያየታቸውን ያቀርባሉ። እነዚህ ዓለም የሚያቀርብላቸውን የሕይወት አካሄድ የሚከተሉ፣ ከቅዱስ ወንጌል የሚገኘውን አዲስ ሕይወት ለመኖር የማይፈልጉና ከዓለም ወገን እንደሆኑ አስረድተው ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኝ አዲስ ሕይወትና ዓለም በሚያቀርብልን ሕይወት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ ብለዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ የተቆጣቸውን የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እነዚያ ክርስቲያኖች ደካማ፣ ሥነ ምግባር የጎደላቸውና ግብዞች ናቸው ብለው የኢየሱስ ክርስቶስ ጥሪ ከዚህ ሁሉ ድክመት ወጥተን ወደ አዲስ ሕይወት፣ ወደ አዲስ ማንነት የሚያበቃን ጥሪ ነው ብለዋል። ሰዎች ደካማነታቸውንና ሐጢአተኛነታቸውን የሚቀበሉ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሃይልንና ምሕረትንም እንደሚቀበሉ ማመን ያስፈልጋል። ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ለደካሞች ሃይላቸው ሊሆን፣ ለሐጢአተኞች ምሕረትን ለማስገኘት ነውና። ነገር ግን ክርስቲያኖች የክርስትናን ሕይወት ከሐጢአት ሕይወት ጋር በማዛመድ ለመኖር የሚመርጡ ወይም የሚፈቅዱ ከሆነ እነዚህ ክርስቲያኖች ግብዝ ክርስቲያኖች ናቸው ብለዋል። ይህን አስመልክቶ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ ነግሮናል። ኢየሱስ ክርስቶስ እዚህ ነው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እዚያ ነው በማለት የሚያሳስቱ ሰዎች ይመጣሉ፣ እነዚህም ዓለም የሚያሳያቸውንና የሚሰጣቸውን የሚያምኑ ናቸው። ይህን በማድረጋቸው ከድነት ርቀዋል። የዘለዓለም ሕይወት የሚገኘው፣ ምህረትም የሚገኘው ከኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ የሰማዕትነት መንገድ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን የሚከተሉትን ፈጽሞ አይጥላቸውም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በአዲስ ሕይወት ኢየሱስን የሚከተሉ ሰዎች መንገዳቸው ምን ይመስላል በማለት ጥያቄን አቅርበው፣ ትናንት ከሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ 6. 6-11 የተነበበውን የወንጌል ክፍል ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ የወንጌል ክፍል የሙሴ ሕግ መምህራንና ፈሪሳዊያን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል እንደተስማሙ ሁሉ በአዲስ ሕይወት ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል የተነሱትን ስደት፣ መከራና ሞት እንደሚጠብቃቸውና ኢየሱስ ክርስቶስን የደረሰ ስቃይና ሞት ዓይነት እንደሚጠብቃቸው ገልጸው ይህ የሰማዕትነት ሕይወት ታዲያ የደም መስዋዕትነት ያለበት ሳይሆን በዕለታዊ ኑሮአችንም ሊያጋጥመን የሚችል ሰማዕትነት ነው ብለዋል። በተቃዋሚዎቻችን፣ እንቅፋት በሚሆኑብንና ዕለት በዕለት በሚከሱን ሰዎች በተጣበበች ጎዳና ላይ እንገኛለን ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእነዚህ ጋር መከራከር አስፈላጊ አይሆንም ብለው ነገር ግን ወንጌልን ለዓለም መስበክን፣ ከቅዱስ ወንጌል የሚገኘውን አዲስ ሕይወት ለዓለም መመስከርን ማቋረጥ የለብንም ብለዋል።                       

10 September 2018, 18:06
ሁሉንም ያንብቡ >