ፈልግ

2018.09.06 Messa Santa Marta 2018.09.06 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “በክርስትና ሕይወት ለመጓዝ ከፈለጉ በራስ እንጂ በሌሎች መፍረድ የለብንም”።

ዛሬ ጠዋት በግል ጸሎት ቤታቸው ለተገኙት ምዕመናን ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት እንደተናገሩት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ውጫዊውን ሳይሆን ውስጣዊውን ሕይወት የሚለውጥ ነው ብለዋል። በመሆኑም ውስጣችንን በመፈተሽ ሐጢአተኞች መሆናችንን አውቀን ራሳችንን እንጂ ሌሎችን መውቀስ እንደማያስፈልግ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዛሬ ጠዋት በግል ጸሎት ቤታቸው ለተገኙት ምዕመናን ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት እንደተናገሩት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ውጫዊውን ሳይሆን ውስጣዊውን ሕይወት የሚለውጥ ነው ብለዋል። በመሆኑም ውስጣችንን በመፈተሽ ሐጢአተኞች መሆናችንን አውቀን ራሳችንን እንጂ ሌሎችን መውቀስ እንደማያስፈልግ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዛሬ ጠዋት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፣ አስቀድመን ራስን መውቀስ ሳንማር ክርስቲያናዊ ጉዞን ማድረግ አንችልም ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአውሮጳዊያኑ የበጋ ወራት ምክንያት ያቋረጡትን የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት የመስዋዕተ ቅዳሴን ስነ ስርዕት ያለፈው ሰኞ መጀመራቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት ያቀረቡት ቃለ ምዕዳን መሠረት ያደረገው በዕለቱ በተነበበው ከሉቃስ ወንጌል ምዕ. 5. 1-11 ላይ በተጻፈው እንደነበር ታውቋል። በዚህ የወንጌል ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለቱ ያስተላለፈውን ትምህርት ከጨረሰ በኋላ ጴጥሮስን ወደ ጀልባ ላይ እንዲወጣ አዝዞት መረቡን ወደ ባሕር እንዲጥል ሲጋብዘው አንድ አስደናቂ ዓሣ እንደያዘ የሚገልጽ ነበር። ይህ የወንጌል ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሳኤው በኋላ ሐዋርያቱን የሚበላ ካለ ብሎ ከጠየቃቸው ጥያቄ ጋር የሚገናኝ እንደሆነ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ የወንጌል መልዕክት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስን አስቀድሞ ሰዎችን የሚያጠምድ፣ ቀጥሎም ላተመዳቸው ወይም ለሰበሰባቸው ሰዎች እረኛ ወይም መሪ አድርጎት እንደሰየመው አስረድተዋል። ይህ ብቻ አይደለም፣ ኢየሱስ ስሙንም ከስምኦን ወደ ጴጥሮስ እንደቀየረውና ይህም በእስራኤላዊያን ልማድ ስም መቀየር ማለት የሥራ ወይም የአገልግሎት ዘርፍ ሳይቀር መቀየር እንደሆነ ጴጥሮስ ያውቅ ነበር። ጴጥሮስም ኢየሱስን ይወደው ስለነበር በተደረገው ሁሉ ደስታ ተስምቶት እንደነበር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

በቅድሚያ ሐጢአተኛነትን ማወቅ፣

ጴጥሮስም ወደ ባሕር ውስጥ በወረወረው መረብ እጅግ ብዙ ዓሶችን ለማጥመድ በመቻሉ ተንበርክኮ ኢየሱስን ጌታዬ ሆይ እኔ ሐጢአተኛ ነኝና ወደ እኔ አትቅረብ በማለት በልቡ ተጸጸተ። ይህ እንግዲህ ለጴጥሮስ የኢየሱስ ሐዋርያ ለመሆን እርሱንም ለመከተል ወሳኝ ምዕራፍ ነበር። ጴጥሮስ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከመሆኑ አስቀድሞ የራሱን ማንነት እንዳወቀ ሁሉ እያንዳንዳችንም መንፈሳዊ ሕይወታችንን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመጓዝ ከፈለግን፣ እርሱን ማገልገል ከፈለግን ከሁሉ በፊት ማንነታችንን መመልከት እንዳለብንና ተሳስተን እንደሆነ ራሳችንን መውቀስ እንዳለብን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቃለ ምዕዳናቸው አስረድተው ይህን ሳናደርግ ክርስቲያናዊ ጉዞን ማድረግ አይቻልም ብለዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን ውጫዊውን ሳይሆን ውስጣዊውን ማንነታችንን ነው፣

ሁላችንም ሐጢአተኞች መሆናችንን እናውቀዋለን፣ ነገር ግን አውቀንም ራሳችንን ለመውቀስ እንቸገራለን። እኔ ሐጢአተኛ ነኝ ማለትንስ እንላለን ነገር ግን በዚያው መጠን ሰው በመሆኔ ነው እያልን ራሳችንን ከጥፋት ወይም ከሐጢአት ነጻ ለማድረግ እንሞክራለን። ራስን መውቀስ ማለት በልባችን ተጸጸተን በእርግጥም የሰራነውን ሐጢ አት ተሸክመን መጥተን ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን ለመለመን በእርሱ ፊት መቆም ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዳደረገው የልብ መጸጸን እንጂ በቃል መግለጽን አይመለከትም። ይህን በማድረጉ መዳንን እንዳገኘ ተሰማው። የኢየሱስ ክርስቶስን ማዳን ለመቀበል ከልብ ተጸጽተን ምሕረትን መለመን ያስፈልጋል። በልባችን ተጸጽተን የምናገኘው ምሕረት፣ እንደ ፊት ቅባት ውጫዊ መልካችንን እንደምናሳምረው ሳይሆን ዋስጣዊ ማንነታችንን ሙሉ በሙሉ ይለውጠዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስም የሆነው እንደዚህ ነው፣ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስገንዝበዋል።

ስለ ሌሎች ክፋት ማውራት ተገቢ አይደለም፣

ቅዱስነታቸው በዕለቱ የተነበበውን የወንጌል ክፍል መሠረት በማድረግ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን እንደገለጹት የድነታችን የመጀመሪያው ደረጃ በበደላችን በመጸጸትና ራስን በመውቀስ የምናገኘው የውስጥ መለወጥ እንደሆነ አስገንዝበው ራሳችንን የግድ መለወጥ እንዳለብንና ስለ ሌሎች ክፋት ማውራት ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል። በዚህ ገለጻቸው እንዳስረዱት የራስን ክፋት ሸፍነው ስለ ሌሎች ሰዎች ክፋት የሚያወሩ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ጠቅሰው ይህን ከማድረግ ይልቅ ምን ሐጢአት ሠራሁ በማለት ራስን መፈተሽ ንስሐን መግባት እንጂ ስለ ሌላ አውርቶ መመለስ ለታይታ የሚደረግ ንስሐ ወይም ውስጣዊ ለውጥን የሚያመጣ ሳይሆን እንደ ፊት ቅባት ውጫዊ ሰውነታችንን ብቻ እንደማሳመር ይቆጠራል ብለዋል።

በእውነት ኃጢአተኞች መሆናችንን የማወቅ ጸጋ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዕለቱን ስብከተ ወንጌል በመቀጠል አንድ ክርስቲያን የራሱን በደል ለይቶ የማያውቀው ስለ ሌሎች ሐጢአት አዘወትሮ መናገር ሲጀምር እንደሆነ ገልጸው ይህም በክርስትና ሕይወት ውስጥ መጥፎ ምልክት እንደሆነ አስረድተው እያንዳንዳችን የራሳችንን በደልና ሐጢአት ለይተን የምናውቅበትን ጸጋ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንድንጠይቅና ሐጢአተኛነታችንን ካወቅን በኋላ እንድ ጴጥሮስ ጌታዬ ሆይ እኔ ሐጢአተኛ ነኝና ወደ እኔ አትቅረብ ማለትን እንድንለምድ በማሳሰብ የዕለቱን ቃለ ምዕዳናቸውን አጠቃልለዋል።      

06 September 2018, 16:47
ሁሉንም ያንብቡ >