ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ ክርስቲያኖች “ወደ ዓለም እቅዶች አትመለሱ ነጻነታችሁን ይገፋሉና”
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በግንቦት 21/2010 ዓ.ም በቅድስት ማርታ የጸልሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “ወደ ዓለም እቅዶች አትመለሱ ነጻነታችሁን ይገፋሉና” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን ወደ ቅድስና ሕይወት የምናደርገውን ጉዞ አጠናክረን መቀጠል ይገባል እንጂ ወደ ዓለማዊ እቅዶች መመለስ የለብንም ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።
የዚህ ዜና አቀናባሪ መብራቱ ኃይሌጊዮርጊስ ቫቲካ
ከፍተኛ ፈተና በሚገጥማችሁ ሰዓት ዓለማዊ ወደ ሆኑ እቅዱች ውስጥ በፍጹም መግባት አይኖርባችሁም በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ዓለማዊ በሆኑ እቅዶች ውስጥ መግባት ወይም መዘፈቅ ነጻነታችሁን ይገፋል፣ በእዚህም ምክንያት ማነኛውም ዓይነት ፈተና በሚገጥመን ሰዓት ወደ ቅድስና ሕይወት የሚወስደውን መንገድ በብርታት መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
ቅዱስ መሆን ማለት ቅዱሳን ያላቸውን ዓይነት ፊት ሊኖረን ይገባል ማለት አይደለም
በእለቱ የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስቲያን ማሕበረሰቦች ዘንድ በላቲን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት በቀዳሚነት 1 ጴጥሮስ 1፡10-16 ተወስዶ በተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተመርኩዘው ቅዱስነታቸው በስብከታቸው የሚከተለውን ብለዋል. . .
ወደ ብርሃን መጓዝ
ስለእዚህ “ወደ ቅድስና መጓዝ” ተስፋችን ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ግልጽት እና ጸጋ መጓዝ” ማለት እንደ ሆነ በመጥቀስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህም በብርሃን መንገድ ላይ እንደ መጓዝ ይቆጠራል ብርሃን ባለበት መነገድ ላይ በምንጓዝበት ወቅት ሁሉ ብርሃኑ መንገዳችንን ቁልጭ አድርጎ ስለሚያሳይ አንሰናከልም ብለዋል።
ቀድሞ ወደ ነበሩን ዓለማዊ እቅዶች ተመልሰን መግባት የለብንም
በቅድስና መንገድ ላይ ለመጓዝ ነጻ እና የነጻነት ስሜት የሚሰማን ሰዎች ልንሆን እንደ ሚገባን በመጥቀስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ነገር ግን በሕይወታችን ጠፍረው ይዘውን ባሪያ የሚያደርጉን ብዙ ነገሮች እንዳሉ ጠቅሰው ይህም ልክ ሐዋሪያው ጴጥሮስ “ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ” እንደ ሚለን ሁሉ እኛም ከቀድሞ ምኞቶቻችን ተላቀን ወደ ፊት መጓዝ ይኖርብናል ብለዋል። ይህንን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል. . .
በቅድሚያ ነጻ የሆንን ሰዎች ካልሆንን በስተቀር ቅዱስ መሆን በፍጹም አንችልም
በቅድሚያ ነጻ የሆንን ሰዎች ካልሆንን ቅዱስ መሆን በፍጹም አንችልም በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሶ እንደ ምናገኘው በወቅቱ የነበሩ የእስራኤል ሕዝቦች በበረሃ ጉዞዋቸው ወደ ደኽንነት የሚወስዳቸውን የጉዞ መስመር አሻግረው መመልከት አቁመው በተቃራኒው ወደ ኃላቸው መመልከት ፈልገው እንደ ነበረ የገለጹት ቅዱስነታቸው በወቅቱ በበረሃ ይጓዙ የነበሩ የእስራኤል ልጆች በእግዚኣብሔር ላይ ያጉረመርሙ ነበር፣ በቀድሞ ጊዜ በግብፅ በባርነት ቀነበር ሥር በነበሩበት ወቅት የነበረውን ዓይነት ሕይወት፣ ለምሳሌም ሽንኩርት እና ሥጋ በመመኘት ያለፈው ጊዜያቸውን ያስቡ እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው “ፈተናዎች እና ችግሮች በሚያጋጥሙዋቸው ወቅቶች ሁሉ ሕዝቡ ወደ ኃላ ተመለሱ በእዚህም ድርጊታቸው ነጻነታቸውን አጡ፣ እውነት ነው በግብፅ በሚኖሩበት ወቅት ጥሩ የሆነ ምግብ ይመገቡ ነበር፣ ነገር ግን ምግቡ ጥሩ ይሁን እንጂ የሚመገቡት በባርነት ቀንበር ሥር ሆነው ነበር ብለዋል።
በፈተና እና በመከራ ጊዜያት ወደ ኃላ አትመልከቱ
“በፈተና እና በመከራ ጊዜያት ወደ ኃላ አትመልከቱ” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህንን በተመለከተ ደግሞ የሚከተለውን ብለዋል. . .
ወደ ቅድስና መጓዝ
ዓለማዊ እቅዶች ብዙ ነገር ቃል ይገቡልናል ነገር ግን ምንም ነገር አይሰጡንም
“ጌታ በእየለቱ ሁላችንንም ወደ ቅድስና ይጠራናል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ትክክለኛ በሆነው የቅድስና መንገድ ላይ መጓዛ አለመጓዛችንን ለማወቅ የሚረዱን ሁለት መመዘኛዎች እንዳሉ ጠቁመው በመጀመሪያ ደረጃ የጌታ ብርሃን እንደምናገኝ ተስፋ በማድረግ ወደ እዚያው አቅጣጫ አሻቅበን የምንመለከት ከሆን፣ በመቀጠልም መከራዎች ወይም ፈተናዎች በሚገጥሙን ጊዜያት ሁሉ ወደ ፊት መመልከታችንን በምንቀጥልበት ወቅት እንደ ሆነ ጠቅሰው “ብዙ ነገር ቃል የሚገቡልን ነገር ግን ምንም ነገር በማይሰጡን” ዓለማዊ አስተሳሰቦች ውስጥ አንዘፈቅም ነጻነታችንንም አናጣም ብለዋል። “እኔ ቅዱስ እንደ ሆንኩኝ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ የሚለው ቃል የእግዚኣብሔር ትዕዛዝ እንደ ሆነ በመገለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እግዚኣብሔር በነጻነት በቅድስና መንገድ ላይ መራመድ ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ፣ እንዲሁም ኢየሱስን ከመገናኘታችን በፊት በዓለማዊ እቅዶች ውስጥ ተዘፍቀን የኖርንባቸውን ጊዜያት መገንዘብ እንችል ዘንድ እንዲረዳን ጸጋውን ይሰጠን ዘንድ ልንማጸነው ይገባል ካሉ በኃላ ስብከታቸውን አጠናቀዋል።